Saturday, March 17, 2012

"ከእባብም ክርስትናን እንማር፤ እንዴት?"

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/07/2004
ከአንድ የቅርብ ቅርብ ወዳጄ አንድ ታላቅ የሆነ ትምህርት ሰማሁ፡፡ ይህ ወዳጄ ነገር መሸፋፈን አይወድምና እንዲህ አለኝ “አንተዬ አንድ የአደባባይ ምስጢር ልንገርህ" ብሎ ይጀምርና በመቀጠል “ካበቁ ከበቃቁ ሰውነታቸውና አእምሮአቸው በኃጢአት ከድሃ ድሪቶ ይልቅ እጅግ ካደፈ በኋላ እንዲሁም ዓለሚቱን በኃጢአታቸው ከከደኗትና  ትውልዱን መንገድ አስተው የአጋንንት መጫወቻ ካደረጉ በኋላ ዓለም በቃኝ አሉ አሉ! እነ እማሆይ! እነ አባሆይ! ዋይ! ... ዋይ! .... ዋይ! ... እኒህ ጽድቅ በቆቤዎች ስለእኛ በመስቀል ላይ ስለተሠዋልን ስለአፍቃሪያችን ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳች ሳያስተምሩን እኛን ለሰይጣን  ዳርገውን ዓለም(ኃጢአት) በቃችኝ ብለው ቆብ አጠለቁ አሉ! ጉድ ነው! መቼም በኢትዮጵያችን ይህ የተለመደ የጽድቅ ማቋረጫ መንገድ ሆኗል ፤እድሜ ለምንኩስና!! መቼም ሰው ቆቡን ከየትም ያምጣው ከየት እርሱን አጥልቆ በአንዴው ጻድቅ ሆኖ ቁብ ይልብናል፡፡ እኽ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል!! ግን ግን ልጆቻቸውን በሥርዐት ቀርጸው የሚያሳድጉና ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ የሚያበቁ እንዲሁም ክርስቶስ በእርሱዋ የሰው ልጅ መባልን ያላፈረባታን ቅድስት ድንግል ማርያምን በምግባራቸው የመሰሉ አንዳንድ ቅዱሳን ወላጆችም አይጠፉም፡፡

ግን አይደንቅም ወገኖቼ! ጌታችን ሰው ያላት ቅድስት ድንግል ማርያምን እኮ ነው! ልጅ ያለውም ራሱን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ሰው መባል ከፈለገ በተግባራዊ ምልልሱ የግድ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሊመስል ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ድንቅ የሚሆንባቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ይህ እንዴት ድንቅ ሊሆን ይችላል? አይደለም ቅድስት ድንግል ማርያምን ክርስቶስን እንድንመስል አልተጠራንምን?

ቢሆንም እንዴት ብሎ ማብራሪያ ለሚፈልግ ሰው ትንታኔው እንደሚከተለው ነው፡- ይክብር ይመስገንና በእርሱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን ሰውነታችን የመንፈሱ ቤተመቅደስ ሆኖአል፡፡ እርሱም እኛን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክና ምሳሌ እንዲኖረን አድሶና አንጽቶ ይቀድሰናል፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስቶስን እንመስለዋለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የሰው ልጅ የተባለው ንጹሕ የሆነውን የድንግልን ተፈጥሮ ገንዘቡ በማድረጉ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቶስን ስንመስለው ድንግልንም እንመስላታለን ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ በሥጋ የእርሱዋን መልክና ምሳሌ ነውና ገንዘቡ ያደረገው፡፡
ቅድስት እናታችን በድንግልና ሕይወት ለሚኖሩትም በጋብቻ ሕይወት ውስጥም ላሉት ምሳሌ ናት፡፡ እርሱዋ ልቡናዋ እግዚአብሔርን በማወቅ የተሞላ፣ ሰውነቱዋንም በንጽሕናና በቅድስና ጠብቃ የኖረች ድንግል ናት፡፡ በዚህ ሕይወቱዋ ለደናግላን አብነታቸው ናት፡፡ ቅድስት እናታችን “ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል መንፈሴም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሐሴትን ታደርጋለች” እንዳለችው ሰውነቱዋን ለእግዚአብሔር አብ ያጨች ሙሽሪትም ናት፡፡ እርሱዋ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ እግዚአብሔር ወልድን በሥጋ ፀንሳ ወልዳ አሳድገዋለችና በትዳር ውስጥ ላሉትም አብነታቸው ናት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በድንግልናዋም በእናትነቱዋም ለባለትዳሮች ምሳሌአቸው ናት፡፡
 ባለትዳሮች እንደ ደናግላን ለራሳቸው የሚሰጡት የጽሙና ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ያም ማለት የጸሎት፤ የተመስጦ እንዲሁም የንባብ ጊዜ ማለት ነው፡፡ በዚህ የጽሙና ጊዜአቸውም ከእግዚአብሔር ይማራሉ፡፡ በጽሙና ሕይወታቸውም ያገኙትን መንፈሳዊ እውቀት ተጠቅመው ትዳራቸውንና ልጆቻቸውን ይመራሉ ያስተዳድራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ከባድ ሓላፊነት ነው፤ ይህን ማን ሊፈጽመው ይችላል? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ ይህ ስለሚቻለን ቅዱስ ጳውሎስ ሚስትን በቤተ ክርስቲያን ባልን በክርስቶስ መስሎ አስተማረ፡፡ እንዲህ የፈጸሙ እውነተኞች ወላጆች ነበሩ፡፡ እኒህ ወላጆች ልጆቻቸውን ለቁም ነገር ካበቁ በኋላ በሕይወታቸው ሙሉ ሲለማመዱዋት ወደ አቆዩአት የጽሙና ሕይወት ክትት ብለው በመግባት እስከ ዕረፍተ ሞታችው ድረስ በጦም በጸሎት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ቅድስናችን ይታይልን በማለት ቆብ አጥለቀው ከንቱ የሆነ ምስጋናን ከሰዎች ለመሸመት አይደክሙም፡፡ ከንቱ ውዳሴ የቅድስና ጠር እንደሆነ ስለሚገነዘቡ በስውር የሚያያቸውንና በግልጥ የሚከፍላቸውን አምላክ ተስፋ በማድረግ ከከንቱ ውዳሴ ርቀው አምላካቸውን በመማጸን እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ያገለግሉታል፡፡
ነገሬ ግን ወዲህ ነው፡፡ እኒህን ቅዱሳንን የመሰለች አንዲት እናት ነበረች፡፡ ልጇንም መጽሐፍ ቅዱስን ታስጠናው ነበር፤ አሁን ብሔረ ኦሪትን አስረጅታው ወደ ሐዲስ ኪዳኑ ዘልቃለች፡፡ ዛሬ ለልጁዋ የምታስጠናው የወንገል ክፍል ማቴዎስ ወንጌል ምዕ.10፡16 ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡- “እነሆ እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” የሚለውን ነው፡፡ እናት ለልጁዋ ንባቡን ካነበበችለት በኋላ ትተረጉምለት ገባች “በጎች የተባሉት የእግዚአብሔር በግ የተባለውን ክርስቶስን የመሰሉ ሐዋርያት ሲሆኑ፤ ተኩላዎች የተባሉት ደግሞ አላውያን ገዢዎች ናቸው” ብላ ተረጎመችለት፡፡ ነገር ግን እንደ “እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” የሚለው ኃይለቃል ስለጸነናት ለልጇ ሳትገልጥለት ወደ ቀጣዩ ምንባብ አለፈች፡፡
ልጇ ግን የዚህን ኃይለ ቃል ትርጉም ሳትተረጉምለት በማለፏ እናቱን ፋታ ነሳት፡፡ እማዬ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ” ብሎ ፈጣሪዬና አፍቃርዬ ማስተማሩ ትርጉሙ ምንድን ነው? በማለት በጥያቄ ወጠሮ ያዛት፡፡ እናትም የልጁዋ ጠያቂነቱን ትወደዋለችና ለልጁዋ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ስትል በተግባራዊ ምልልሳቸውና በመንፈሳዊ እውቀታቸው ከተመሰገኑት አንድ መምህር ዘንድ ታመራለች፡፡ ወደ እርሳቸው በደረሰችም ጊዜ ሰላምታ ሰጠቻቸው፡፡ እርሳቸው አረፍ እንድትል በመጋበዝ ምን እግር ጥሎአት ወደ እርሳቸው እንደመጣች እግረ መንገዳቸውን ጠየቁዋት፡፡ እርሱዋም ለልጁዋ ትመልስለት ዘንድ የከበዳትን ጥያቄ እንዲህ በማለት አቀረበችላቸው፡-“መምህር ሆይ የእባብ ልባምነት የርግብ የዋህነት ትርጉሙ ምንድነው” አለቻቸው፡፡ እሳቸውም ይመልሱ ጀመር “አየሽ እኅቴ” ብለው ትንሽ ካሰላሰሉ በኋላ “አየሽ እኅቴ እባብ ራሱን ከጠላቶቹ ጥቃት ለመጠበቅ ሲል ጠላቶቹ በቀላሉ በማይደርሱበት በበርሃና በቋጥኞች ሥር እንዲሁም በቁጥቋጦዎች ውስጥ መኖሪያውን ያደርጋል፡፡ ራሱንም የሰው ኮቴ ከማይረግጥበት ምድረ በዳ ውስጥ ሰውሮ ያኖራል፡፡ ስለዚህም ጠላቶቹ የሰው ልጆች በቀላሉ አግኝተውት ሊገድሉት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ለአንድ ክርስቲያን ታላቅ ትምህርትን ይሰጠዋል፡፡ አንድ ክርስቲያንም ሰይጣን እርሱን እንደ ስንዴ አባጥሮ፣ እንደ ትቢያ አብንኖ እንዳያጠፋው ለሰይጣን በማይመች አኗኗር ሊኖር ይገባዋል፡፡ ያም ማለት ለሕይወቱ መመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን በማድረግ፤ እስኪጠግብ ድረስ ባለመመገብ፤ አለባበሱ ለዝሙት ጠንቅ እንዳይሆንበት በመጠንቀቅ፣ ጾምንና ጸሎት በማዘውተር፣ ከንቱ ከሆነ ስብስብ በመራቅ፣ እግዚአብሔርን ከሚፈሩት ጋር ባልንጀርነትን በመመሥረት፤ ትሕትናንና ፍቅርን ስንቁ በማድረግ፣ እነዚህንና እነዚህን የመሰሉ ሌሎችንም የጽድቅ ትጥቆችን ታጥቆ በመገኘት ከጠላት ሰይጣን ጥቃት ሊድን ይችላል፡፡ እንዲህ የፈጸመ ክርስቲያንን ቅዱሳን መላእክት አጥር ቅጥር ይሆኑታል፡፡ በሰውነቱ እግዚአብሔር ይገለጣልና ሰይጣን ወደ እርሱ ፈጽሞ መቅረብ አይቻለውም፡፡
እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑም ሲል ክፉውን በክፉ አትቃወሙ፣ የሚረግሙአችሁን መርቁ፣ ለሚያሳደዱዋችሁም ጸልዩላቸው፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለክፉ ነገር እንደ ሕፃናት ሁኑ ማለቱ ነው” ብለው አስረዱዋት፡፡ ይህቺ ቡርክት እናትም ከእኚ መምህር የሰማችውን ለልጇ ልታወራው ተቻኮለች፡፡ ሄዳም ለልጁዋ ተንትና አስረዳችው፡፡ ልጁም ለካ እባብም በአኗኗሩ ክርስትናን ይሰብካል ብሎ ተገረመ፡፡” እኔ ግን ከዚህ ትምህርት አንድ ልዩ ትምህርትን ጨበጥኩ፡፡
ሰው  contingency theoryን (ወቅቱን ያገናዘበ የአስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን)ከሰይጣን ሊማር ይገባዋል አልኩኝ፡፡ በምድር ላይ ማንኛውም ነገር ሰይጣንም ቢሆን አስተማሪ ሆነው ተፈጥረዋል፡፡ ጠላታችን ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕግ ገልብጦ ሲጠቀምበት፤ እኛ ደግሞ ከሰይጣን ያገኘነውን ገልብጠን የተጠቀምንበት እንደሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ተስማምተን መኖር ይቻለናል፡፡ እርሱ መለያየትን ሲሰብከን ፍቅርን እንይዛለን፤ እርሱ ጠብን ሲፈጥር እኛ ሰላምን እንሰብካለን፤ ብቻ የእርሱ ተቃራኒ ሆነን ከተሰለፍን ከአምላካችን ጎን ቆመናል ማለት ነው፡፡ እኔ ይህን ተረዳሁ እናንተስ? አበቃው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለክብሩ ወራሾች ለስሙ ቀዳሾች ያድርገን ለዘለዓለሙ አሜን!!!  



5 comments:

  1. deneke tekamina asitemari yehon timihiri kale hiyiweti yasamali memihiri erjimi yageligiloti edima yisitililin

    ReplyDelete
  2. D/N Leyu Melketa Newe Amelak Yebarekeh Lebezuwech yemteterf Yaderge

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  4. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete