Wednesday, March 14, 2012

ትምህርተ ድኅነት (ክፍል ሁለት)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/07/2004
እግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን የመልበሱ ምክንያት ምንድን ነው ?
የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን የመልበስ ምክንያትን በተመለከት ቅዱሳን አባቶች በተለይ ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል ፡-
“በፍቅር እጆቹ ያበጀውን ፍጥረት በሰይጣን ተንኮል በመሰናከሉ ጠፍቶ እንዲቀር ማድረግ ርኅሩኅ የሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ አልፈቀደም ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እርሱ ፈታሔ በጽድቅ ኰናኔ በርትዕ ነውና እርሱ ራሱ የፈረደውን ፍርድ ማስቀረት ባሕርይው አልፈቀደም፡፡ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ባላስባለው ነበር፡፡ ስለዚህም በአዳምና በሰው ልጆች ላይ የተፈደውን ፍርድ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድና ራሱ ፍርዱን በራሱ ላይ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ የፈረደውን ፍርድ በራሱ አስወገደው” ይለናል ፡፡በእርግጥ ይህን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ “ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ብሎ ይገልጠዋል፡፡(ዕብ.1፡3)

ምነው የሰው ንስሐ መግባት ብቻውን በቂ አልነበረምን? ስለምን እንዲህ ጽኑ መከራን ስለሰው ልጆች መቀበል አስፈለገው  ? ተብሎ ቢጠየቅ የሰው ንስሐ መግባት በራሱ የማይታጠፈውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ለማስቀረት አቅም የለው፡፡ስለዚህ ጉዳይ ቅዱስ አትናቴዎስ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ይላል፡-
“ንስሐ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲታጠፍ ማድረግና ወደ ቀድሞ ተፈጥሮ መልሶ ኃጢአትን ከመሥራት ሊከለክለው አይቻለውም፡፡ ሰው በኃጢአቱ ምክንያት በተፈጥሮ ላይ የመጡት ለውጦች( የውድቀት ባሕርይ (fallen nature)የሚባሉት) ባይከሰቱበት ኖሮ በእርግጥ ንስሐ ብቻዋን ባስፈለገች፡፡ እነሆ እኛ በንስሐ የሚታደስ ተፈጥሮን በጥምቀት ለብሰናል፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ ስቀለት በፊት በአዳም መተላለፍ ምክንያት የሰው ተፈጥሮአዊ ባሕርይ በመጎሳቆሉ ፣ ሞትና ተዛማች የሆኑን የውድቀት ወጤቶች በሰው ልጆች ላይ መጡ፡፡ እግዚአብሔር ቃልም ሰው የመሆኑ ዋናው ምክንያት ይህን ለማስወገድ ነወው፡፡
ስለዚህም ይህ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ቃል ሥጋ መልበስ ምክንያት ጠቅለሎ ሲያስተምር ፡-
“እኛ በምንረዳው መጠን የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን የመልበሱና በዚህ ምድር የመገለጡ ምሥጢር የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብራቸው ለመመለስ ከእርሱ በቀር ሥልጣኑም ኃይሉም ያለው ባለመኖሩ፣ በባሕርይው የእግዚአብሔር አብ አርአያና አምሳል ከሆነው ከክርስቶስ በቀር ሰውን በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የሚፈጥረው ባለመኖሩ፤ እንዲሁም ሕይወት ከተባለው ከእርሱ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሰውን ከውድቀት ባሕርይ አውጥቶ በሕይወት እንዲመላለስ ማደርግ የሚቻለው ከፍጥረት ወገን ባለመኖሩ፣ በተጨማሪም ስለአባቱ እግዚአብሔር አብ በማስተማር የሰውን ልጅ ከጣዖት አምልኮ መመለስ የሚቻለው ከፍጥረት ወገን ስለሌለ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው በመሆን በሥጋ መገለጥ አስፈለገው” ይለናል፡፡ ይህ በእርግጥ ድንቅና ጥልቅ የሆነ እይታ ነው ፡፡
ቅዱስ አትናቴዎስ “እግዚአብሔር ወልድ ከሰው የሚልቅን ተፈጥሮ በመልበስ ሰውን ለማዳን ለምን አልፈለገም ? ተብሎ ለሚጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ከባሕርይው ተጎሳቁሎ ታሞ ያለው የሰው ተፈጥሮ ነው ስለዚህም ይህን ባሕርይ ለመፈወስ የግድ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋ ማርያምን መልበስ ያስፈልገው ነበር” ይለናል፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ፍርድ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሚለውን የካቶሊካዊ አስተምህሮ ዋጋ ቢስነት የሚያሳይ አገላለጽ ነው፡፡ እንደ ቅዱሱ አስተምህሮ “ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድና በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት ተጎሳቁሎ የነበረውን የእግዚአብሔርን አርአያና አምሳል ወደ ቀድሞው ንጽሕናውና አቅሙ ለመመለስ የእግዚአብሔር ቃል ሥጋ ማርያምን መልበስ አስፈለገው”፡፡ በእርግጥ ይህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም አስተምሮ ነው፡፡
ቅዱስ ይስሐቅ ደግሞ እግዚአብሔር ቃል ሰው የመሆኑን ምሥጢር ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ እንደሆነ እንዲህ በማለት ይገልጥልናል፡-
የእግዚአብሔር ቅናት ሰውን ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ ዋናው ምክንያት ቢሆን ኖሮ ስለምን እግዚአብሔር ቃል የሰውን ሥጋ በመልበስ ፣ ዓለሙን በጥበብና በትሕትና ወደ አባቱ መመለስን ፈቀደ ? ስለምንስ ስለኃጢአተኞች እጆቹ በችንካር በመስቀል ላይ መቸንከር አስፈለጋቸው ? እኔ ግን እግዚአብሔር እንዲህ ማደረጉ እርሱ ለሰው ልጆች ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅር ለማሳየት ካልሆነ በቀር ሌላ ምክንያት የለም እላለሁ ፡፡ የእርሱ ሥጋ ማርያምን በመልበስ ሰው የመሆኑ ምክንያት እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ተገንዝበን ፣ ለፍቅሩ ተማርከን በእርሱ የመስቀል ሞት ፍቅር ከሚፈስባት መንግሥቱ እንገባ ዘንድ ነው ፡፡ይህ በሰው ልጆች ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ፍቅር የሰውን ነጻ ፈቃድ በመጣስ ለፍቅሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሰዎችን የሚያስገድዳቸው ባይሆንም በምላሹ እነርሱም ለእርሱ በፍቅር እንዲታዘዙት ግን ይሻል፡፡ በተለይ ክርስቲያን የሆንን እኛ እርሱ የሰጠንን ወሰን አልባ ፍቅር እኛም በምላሹ እንድናሳየው ይጠበቅብናል ፡፡”
በእውነትም ከእኛ ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው ይህ ነው፡፡እርሱም ስለእኛ መዳን በመስቀል ላይ የተሠዋውን አፍቃሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ሁል ጊዜ በማሰብ ራሳችንን ከኃጢአት በመጠበቅ እርሱን ደስ በሚያሰኝ ሕይወት እንመላለስ ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ይህን ለመፈጸም ይርዳን፤ ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡

1 comment:

  1. Amen!!! yiridani yemsikelu fikiri hula befitachin yisali::

    ReplyDelete