Friday, March 23, 2012

ነጻ ፈቃድና ቃና ዘገሊላ(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2004
ስለእኛ መዳን ራሱን ዝቅ በማድረግ የባሪያውን መልክ ይዞ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም በሆነ ትሕትና “በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ”(ሉቃ.7፡34)ብለው ስም እስኪሰጡት ደርሶ ራሱን ዝቅ በማድረግ ከእናቱና ከደቀመዛሙርቱ ጋር በቃና ዘገሊላ በባሪያው በዶኪማስ ሰርግ ላይ በእንግድነት ተገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ ለሰርጉ የተጣለው ወይን ጠጅ አልቆ ነበርና ሙሽራው ሲጨነቅ አይታ እናታችን ቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ልጁዋን ወዳጁዋን “ወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት ልመናን አቀረበችለት፡፡ ጌታችንም “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም”ብሎ መለሰላት፡፡(ዮሐ.2፡3-4) ይህ የጌታችን መልስ ቅድስት እናታችን ለልጁዋ ለወደጁዋ ልመና ስለማቅረቡዋ ምስክር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አስመልክቶ የዮሐንስ ወንጌልን በተረጎመበት 21ኛው ድርሳኑ ለእኛ እንዲህ ብሎ ያስተምረናል፡፡
  
“ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ትልቅ አክብሮት እንዳለው ቅዱስ ሉቃስ “…ይታዘዛቸውም ነበር”(ሉቃ.2፡51) በማለት ገልጾልናል፡፡  ወንጌላዊው ዮሐንስም ጌታችን ለእናቱ ምን ያህል እንደሚጨነቅ ሲገልጥልን “አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ … ደቀ መዝሙሩን እናቱን እነኋት እናትህ አለው” ማለቱን ጽፎልናል፡፡(ዮሐ.19፡26) እንዲህ የሚጨነቅላትና የሚታዘዛት ሆኖ ሳለ እንዴት እርሱዋን “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም”በማለት ጌታ እናቱን አቀሏታል ብለን ልናገር እንችላለን? 
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲህ ማለቱ … ምክንያት ነበረው፡፡ … ጌታችን እናቱንና እናታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲህ ማለቱ እርሱ የሚፈጸመው ተአምር ተአምሩ እንዲፈጸምላቸው ከእነርሱም ፈቃድ መኖር ስላለበት ነበር፡፡ ስለዚህም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእርሱ ያቀረበችውን ልመና ዓይነት ወይኑን ከሚሹት ወገኖች እስኪቀርብ ወይም መሻታቸውን በድርጊት እስኪገለጡ ድረስ የእናቱን ልመና ከመፈጸም ዘገየ፡፡ በአንድ ሰው ጥያቄ ብቻ የሚፈጸም ተአምር በሌሎች ዘንድ ላይስተዋል ይችላል፡፡ ነገር ግን ተአምራቱ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ራሳቸው ጠይቀው የተፈጸመላቸው ከሆነ ለተአምር ፈጻሚው ተገቢውን ክብር ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህም ለጌታችን ለመድኀኒታችን የሚያቀርቡት ምስጋና ንጹሕ፣ ለእነርሱም የሚሰጠው ጥቅሙ ታላቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ወይም አንድ እውቅ ሐኪም ብዙ ሕመምተኞች ከሚገኙበት ቤት ገብቶ ሕመምተኞቹ ወይም ዘመዶቻቸው ሳይፈቅዱለት እንዲሁ የእናቱን ቃል ብቻ ሰምቶ ሊፈውሳቸው ቢሞክር ሕመምተኞቹ በጥርጣሬ ሊያዩት ከዛም አልፈው ላይቀበሉት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነርሱ ዘንድ አንዳች ታላቅ ሥራን እንደ ተሠራ ልብ ላይሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ጌታችን እናቱን “አንቺ ሴት ካንቺ ምን አለኝ” አላት፡፡ እንዲህ ሲል እናቱን ቅድስት ንጽሕት ማርያምን “ከእነርሱም ፈቃዱ ይምጣ” ማለቱ ነው እንጂ ማቃለሉ አልነበረም፡፡ እንዲህም ማድረጉ ስለብዙዎች መዳን ከመጠንቀቅ የተነሣ እንጂ የእናቱን ልመና ካለመቀበል አንጻር አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሣት መወለዱ ይህንን ሊፈጽም ነውና፡፡…ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን በዚህ የሰርግ ቀን የሚፈጽመው ተአምር በሁሉ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን ስላሻ ስለብዙሃን ጥቅም “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት፡፡እንዲህ ማለቱ ግን ለእናቱ አለመታዘዙን የሚያመላክት አይደለም፡፡ ከቃል ድርጊት ይበልጣልና መታዘዙን ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየር አሳይቶናል፡፡ ይህም እርሱ የእናቱን ልመና መስማቱን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 22ኛው ድርሳኑ ላይ ይህኑን ኃይለ ቃል ደግሞ ተርጉሞት እናገኛለን ፡፡ እርሱ ለወይን መጥመቂያዎቹ ጋኖች አይሁድ የማንጻት ሥርዐትን ፈጸሙ ብሎ ወንጌላዊው መጻፉ ለምን ዓላማ እንደሆነ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል፡-
“በዚያን ዘመን አይሁድ የወይን ጠጃቸውን የሚጠምቁት በድንጋይ ጋኖች ነበር፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው “አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፡፡ ኢየሱስም ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው” ብሎ ጻፈልን፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ ማለቱ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የወይን ጠጁ ካለቀ በኋላ የሚቀረው አተላ በውኃ ቢጠበጥ ደካማ ወይን ጠጅ ስለሚሆን (በእኛ ቅራሪ እንደምንለው ዓይነት ነው) ኢአማንያን አተላውን በውኃው በጥብጦ ተአምር አደረኩ ይለናል ብለው እርሱን ከመማን እንዳይመለሱ፤ የድንጋይ ጋኖቹ በአይሁድ የማንጻት ልማድ በውስጣቸው ያለው አተላ(Lee) ተደፍቶ ንጹሑ መሆናቸውን ለማስረዳት ሲል ወንጌላዊው እንዲህ አለ፡፡
አሁን ደግሞ ቀደም ብለን ወደ ተመለከትነው ወደ መጀመሪያ ድርሳኑ እንመለስ፡፡ በዚህ ድርሳን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡-
 “… ጌታችን በሌላ ቦታ አንዲት ሴት “የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው”(ሉቃ.11፡27) ያለችውን እንደገሠጻት እናቱን በዚህ ቦታ የገሠጻት አይደለም፡፡ ያቺ ሴት ከእርሱ በአጸፌታው ብፅዕት መባልን ሽታ ስለነበርና ስለዚህ ጌታችን “አዎን ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ብሎ መለሰላት፡፡ እንዲህም ሲል በሥጋ የወለደችውን እናቱን ክብር ማቃለሉ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ከእርሱዋ መወለዱ ንጽሕናዋንና እምነቱዋን ተመልክቶ እንደሆነ ለማስረዳት እንዲህ አለ፡፡ ይህም የቅድስት እናታችንን ንጽሕናና ቅድስና በእጅጉ የሚያጎላ ነው፡፡
ቅድስት እናታችንን ለእናትነት ያበቃት ራሱዋን በቅድስና ጠበቃ በመገኘቱዋ ነው እንጂ በሥጋ ከዳዊት ወገን በመሆኑዋ ብቻ አልነበረም፡፡ ይህ ለእኛ ልዩ ትምህርትን ይሰጠናል፡፡ እኛ በጥምቀት የእርሱ ወገኖች የተባልን ክርስቲያኖች በመልካም ሥነ-ምግባራችን ካልተመላለስን በቀር በስም ብቻ የክርስቶስ ቤተሰቦች መሰኘታችን የሚያመጣልን አንዳች ፋይዳ እንደሌለ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእናትነት የመመረጡዋ ምክንያት ይጠቁመናል፡፡ ዳዊት በሥጋ ዘመዶቻቸው ስለሚታመኑ ሲናገር “ወንድም ወንድሙን አያድንም”(መዝ.48፡7) ብሎአል፡፡ እኛም ከቅዱሳን ጋር በሥጋ ስለተዛመድን ብቻ አንድንም፡፡ ነገር ግን ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘነውን ጸጋ ተጠቅመን ራሳችንን በቅድስና ያመላለስን እንደሆነ ብቻ ልንድን እንችላለን፡፡ እንዲህ አድርገን ስንገኝ ነው ከቅዱስናው ተካፋዮች ለመሆን የምንበቃው፡፡
 አይሁድ በሥጋ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወገናቸው ስለሆነ አልዳኑም፡፡ የጌታ ወንድሞች ከተባሉት ውስጥ (ከያዕቆብና ከይሁዳ በቀር) የዳነ የለም፡፡ የእርሱ ወንድሞች መባላቸው ከዓለም ጋር ከመጥፋት አልታደጋቸውም፡፡ እርሱ ያስተማረባት ኢየሩሳሌም (በጥጦስ) ከመጥፋት አልዳነችም፡፡ በሥጋ ከጌታ ጋር የሚዛመዱ አይሁድ ክርስቶስን ባለመቀበላቸው በአሕዛብ ነገሥታት ተጨፈፍጭፈው አልቀዋል፡፡ ምክንያቱም የክርስቶስን አምላክነት በመቀበል የጽድቅ ጥሩርን  ለብሰው ባለመገኘታቸው ነበር፡፡ ሐዋርያት ግን ከአይሁድ ተለይተው ከሌሎች ይልቅ ልቀውና ከብረው ተገኙ፡፡ ምክንያቱም የሚያድናቸውንና የሚጠቅማቸውን የጽድቅ ጎዳና ተከትለው ነበረና፡፡ ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ተጠቃሚዎች ለመሆን ልክ እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእምነታችን መጽናትና በመልካም ሥነ ምግባር በመመላለስ ለዓለም ብርሃን ሆነን መገኘት ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው ልንድን የምንችለው፡፡ እነ እገሌ እና እነ እገሌ የክርስቶስ የሥጋ ዘመዶች ነበሩ የተባለላቸው ሰዎች ነበሩ፤ አሁን ግን ከነስም አጠራራቸው ጠፍተዋል፡፡ እርሱን በእምነት የተከተሉት ሐዋርያት ግን  ሥራቸውና ስማቸው በዓለም ዙሪያ ሲታወስና ሲወሳ እስካሁን አለ፡፡   
የብዙ ሺህ ታላላቅ ቅዱሳን አባቶች የሥጋ ወገኖች በመሆናችን አንመካ፤ ነገር ግን በእነርሱ የጽድቅ ሥራ ብቻ ከፍርድ እንደማናመልጥ ተረድተን እነርሱን በምግባር እንምሰላቸው፡፡ ቅዱሳን ከሆኑ ወገኖች በመወለዳችን በእኛ ላይ የባሰን ፍርድ ከማምጣት በቀር ሌላ በሥጋ በመዛመዳችን አንዳች ብቻ የምናገኘው ጥቅም የለም፡፡ ይልቁኑ ምሳሌ የሚሆኑን በሥጋ የተዛመድናቸው ቅዱሳን ከአጠገባችን እያሉ እነርሱን በምግባር መስለን አለመገኘታችን የባሰ ፍርድን ያመጣብናል፡፡ እኛ  አይደለም እነርሱን ልንመስል የመምህራኖቻችንን የሕይወት ፈለግ ልንከተል አልፈቀድንም፡፡
 እኔ እንዲህ ማለቴ ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰብከን ወደ ክርስትና እምነት ካመጣናቸው በኋላ እነርሱ በእኛ ላይ ያላቸውን ትምክህት በመስማቴ ነው፡፡ እነርሱ ወደ ክርስትና እምነት ከተመለሱ በኋላ ዘመዶቻቸውንና የሥጋ ወገኖቻቸውን እንዲሁም ቤታቸውን በመተው “የእኛ ዘመዶች፣ ወዳጆችና፣ ባልንጀሮች በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ናቸው” ብለው በድፍረት በእኛ እንደሚመኩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ለእኛ ታላቅ ውርደት ነው፡፡ ምክንያቱም ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና የተመለሱ ወገኖች በእኛ እየተመኩ እኛ ግን ከጽድቅ ሕይወት ርቀን በኃጢአት ሕይወት ውስጥ እየዳከረን መገኘታችን ነው፡፡ ሌላው የሚያስደንቀው ነገር ለክርስቲያናዊ ሥነምግባር ቦታ ሳትሰጥ ስለክርስቲያናዊ ሥነምግባራችን በተጠየቅን ጊዜ እራሳችንን ለመከላከል ስትል “የኔ አባት፣ አያቴ፣ ቅም ቅም አያቶቼ፣ እንዴት ያሉ ቅዱሳን ነበሩ” ብለን መመለሳችን ነው፡፡  እንዲህ በማለታችን ግን በራሳችን ላይ ፍርድ እንዲበረታብናል እንጂ አንዳች ጥቅምን አናገኝም፡፡ ምክንያቱም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የቅድስና ሰንሰለት በእኛ ክፉ ምግባር በመበጠሳችን ነው፡፡
ለአይሁድ ነቢያት ምን እንደሚሉዋቸው ስሙ“…እስራኤል ስለሚስት አገለገለ፡፡ ስለ ሚስትም ጠባቂ ነበር፡፡”(ሆሴ.12፡13) እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ አየም ደስም አለው” ብሎ መሰከረለት፡፡(ዮሐ.8፡56) በሁሉ ስፍራ ነቢያት ለእስራኤላውያን ሲያስተምሩዋቸው የአባቶቻቸውን የጽድቅ ሥራ በማስቀደም ነበር፡፡ እኚህ ነቢያት ቅዱሳን አባቶችን እያመሰገኑአቸው ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አይሁድ እነርሱን አብነት አድርገው በጽድቅ ሕይወት ባለመመላለሳቸው ምክንያት የባሰ ፍርድ እንደሚከተላቸው ሲያስጠነቁቋቸውም ጭምር ነበር፡፡
 እንግዲህ ይህን ልብ በሉ ራሳችሁን ታድኑ ዘንድ በጽድቅ ሥራ ትጉ፤ በሌሎች መልካም ሥራ ተደግፋችሁ የምትድኑ መስሎአችሁ ራሳችሁን አታታሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርፍን አያመጣልንም፡፡ ነቢዩ ዳዊት “በሞት የሚያስብህ የለም” ካለ በኋላ “በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው? አለ፡፡(መዝ.6፡5) ስለዚህ በእግዚአብሔር መንግሥት ከማይመጠነው በረከት ተካፋይ ለመሆን እንድንበቃ ነፍሳችን ከሥጋችን ሳትለይ በዚህች ዓለም ሳለን ንስሐ እንግባ፡፡ በአፍቃሪያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብና ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡             
.

1 comment:

  1. ምክንያቱም ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና የተመለሱ ወገኖች በእኛ እየተመኩ እኛ ግን ከጽድቅ ሕይወት ርቀን በኃጢአት ሕይወት ውስጥ እየዳከረን መገኘታችን ነው፡፡ ሌላው የሚያስደንቀው ነገር ለክርስቲያናዊ ሥነምግባር ቦታ ሳትሰጥ ስለክርስቲያናዊ ሥነምግባራችን በተጠየቅን ጊዜ እራሳችንን ለመከላከል ስትል “የኔ አባት፣ አያቴ፣ ቅም ቅም አያቶቼ፣ እንዴት ያሉ ቅዱሳን ነበሩ” ብለን መመለሳችን ነው፡፡ እንዲህ በማለታችን ግን በራሳችን ላይ ፍርድ እንዲበረታብናል እንጂ አንዳች ጥቅምን አናገኝም፡፡ ምክንያቱም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የቅድስና ሰንሰለት በእኛ ክፉ ምግባር በመበጠሳችን ነው፡፡ lalawi yemigerimewi bezi zemeni yeabbatocha yisit new tegadilewi besmaetineti ezi adersulini bilo yeminageri kirisitiyani ayala new honomi yensuni hiyiweti arineti arigo yeminori gin eytefa new enidetinatu enidetinaTI WEDIYAWI enideferisawiyani yeabirehami zeni eyalu bicha bezina menori

    ReplyDelete