Friday, February 10, 2012

ነፍስ ለሥጋ ያቀረበችው ምስጋና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/06/2004 

ነፍስ እንዲህ ብላ ሥጋን አመሰገነቻት፡፡ ሥጋዬ ሆይ እኔ ብቻ ሳልሆን መላእክትም አንቺን እጅግ ያከብሩሻል ያፈቅሩሻል፡፡ ምክንያቱም ባንቺ ነውና እነርሱ እርሱን መመልከታቸው፡፡ አስቀድሞ ግን ምንም እንኳ እነርሱ ረቂቃን ቢሆኑ ረቂቅ የሆነውን  እግዚአብሔርን ለማየት  አልተቻላቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም በሰው አምሳል ተገልጦ ይታያቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ከእናታችን የነሳውን ሰውነት ገንዘቡ አድርጎአልና እርሱን ለማየት በቁ፡፡ ስለዚህም ሥጋዬ ሆይ መላእክት አንቺን ያፈቅሩሻል ያመሰግኑሻል፡፡ እንደዲያማ ባይሆን እግዚአብሔርን እንዴት ሊያዩት ይችሉ ነበር? እኛም በእርሱ አባቱን ልንመለከት፣ መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችን ሊሆን እንዴት ይችል ነበር? ሕመምተኞችስ እንዴት ወደ እርሱ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመዳሰስ  ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር? እኛስ እንዴት የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ልንሆን እንችል ነበር? እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልተፈጸመልን ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ እሳት ልብሱም እሳት ነውና፡፡ እርሱ የማይጨበጥና የማይዳሰስ ረቂቅ እንዲሁም ማንም በማይደርስበት ብርሃን ውስጥ የሚኖር ነውና፡፡ ወደ እርሱስ መቅረብ የሚቻለው ማን ነበር? እርሱ  የሚባላ እሳት ነውና፡፡ 


ኪሩቤል ከመለኮቱ ከሚፈልቀው ብርሃን እንዳይጎዱ ገጻቸውን በክንፎቻቸው ይጋርዱት ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድመው በዐይኖቻቸው አይተውት የማያውቁትን ፈጣሪያቸውን በግርግም በሥጋ ልደት ተወልዶ ከእናቱ እቅፍ ሆኖ ለማየት በመብቃታቸው  እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡
እኔ ነፍስ ደግሞ ከአንቺ የነሳውን ሥጋ አንቺው በመመገብ ባንቺ ምክንያት ሕያው ሆንኩበት፡፡ሥጋው መለኮት የተዋሐደው እኔ ነፍስ የተለየሁት ነው፡፡ ይህም የአንቺን ጠቃሚነት በእጅጉ የሚያጎላ ነው፡፡ እርሱ በእኔ እኔም በእርሱ እንድኖር ምክንያቱ አንቺ ነሽና ሥጋዬ ሆይ አመሰግንሻለሁ፡፡ በእውነት አንቺ ሥጋዬ ባትኖሪ ኖሮ የኃጢአት ፈቃድ ከእኔ መንጭቶ ተጎሳቁዬ በዚህች ኃጢአት በሠለጠነባት ዓለም በሰይጣን እየተጠቀጠቁሁ ለዘለዓለም በኖርኩ ነበር፡፡ አምላክ ግን እድንብሽ ዘንድ አንቺን ሰጠኝ እርሱም አፈቀረሽ፡፡ ቤተመቅደሱም አደረገሽ፡፡ ለዘለዓለም መመለኪያውም ሆንሽ፡፡ አንቺን በመልበሱ ምክንያት ፍጥረት ሁሉ ፈጣሪያቸውን ለማየት በቁ፤ ስለዚህም እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ እኔም በአንቺ ሕይወትን አገኘሁ፡፡ ሚስቴ የሆንሽ ሥጋዬ ሆይ!! አንቺን የሰጠኝን አምላክ ስለዚህ በጎ ቸርነቱ ሁሌም ላመሰግነው ይገባኛል፡፡ ዘወትር በአንቺ ያገኘሁትን መዳን እያሰብኩ እባርክሻለሁ፡፡ እኔም አንቺ ጌታሽን ትመስዬው ዘንድ ስላንቺ ቀንና ሌሊት እተጋለሁ ምክንያቱም ለመዳኔ ባለውለታዬ ነሽና፡፡ አለች ነፍስ!!  

No comments:

Post a Comment