በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/06/2004
ዘመኑ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ አንድ ቫላንታይን የሚባል ቅዱስ እንደሆነ የሚነገርለትና
በሰማዕትነት ያረፈ ቄስ ነበር፡፡ በእርሱ ስምም በአውሮፓ ፌብሯሪ ዐሥራ ዐራት ቀን በእኛ አቆጣጠር የካቲት ስድስት የፍቅረኞች
ቀን ተብሎ ይከበር ነበር፡፡ ነገር ግን የኋላ ኋላ ይህ በዓል በሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንዳይከበር ታገደ፡፡ ነገር ግን አንደገና
ይህ በዓል ሕይወት ዘርቶ በአውሮፓውያን ዘንድ ይከበር ያዘ ፡፡ ቀስ በቀስም በዓሉ የአውሮፓውያን መሆኑ ቀርቶ የመላው ዓለም ሆነ፡፡
በሀገራችንም የፍቅረኞች ቀን መከበር ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ይህን እስከዚህ ካልኩ ይበቃኛል፡፡ ምክንያቱም ከእኛ ትውፊት ጋር ፈጽሞ የማይዛመድ ስለሆነ ትቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን አልነቅፍም፤ ዓላማዬም ይህ አይደለም የኔ ትኩረት ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ
ክቡር ስለሆነው ጾታዊ ፍቅር አንድ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጾታዊ ፍቅር ሰማያዊ፣ ድንቅና ግሩም ነውና፡፡ጾታዊ ፍቅርን ሰማያዊ ያሰኘው ሰማያዊ ከሆነው ከሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ጋር በእጅጉ የተዛመደ መሆኑ ነው፡፡ ድንቅ መባሉም በቃላት የማይገለጥ ፍጹም ውሕደትን በፍቅረኞች መካከል መፍጠሩ ነው፤ ግሩም ማሰኘቱ ደግሞ ይህ ረቂቅ የሆነው ተዋሕዶ በአካል ገዝፎ በልጅ መገለጡ ነው፡፡ የፍቅረኞች ተዋሕዶ ፍሬ ልጅ ነው፡፡ በልጃቸው ባል የሚያፈቅራትን የሚስቱን ገጽታንና ጠባይ ሲመለከት እንዲሁ ሚስት የምታፈቅረውን የባልዋን ጠባይና ገጽታ በልጁዋ ትመለከታለች፡፡ በልጅ የተገለጠውን ተዋሕዶ በቃላት ተርጉሞ ማስረዳት እንዲያስቸግር እንዲሁ በፍቅር የተመሠተውን ረቂቅ የሆነው ተዋሕዶ በቃል ማስረዳት የማይሞከር ነው፡፡ በጾታዊ ፍቅር የተፈጸመውን ተዋሕዶ ማስረዳት ካልተቻለን እንዴት ያዋሐዳቸውን ፍቅር በሰዎች ቋንቋ መግለጽ ይቻለናል?
ይህ ተዋሕዶ በእግዚአብሔር ቃልና ከእመቤታችን በነሣው ሥጋና ነፍስ መካከል የሆነውን ተዋሕዶን ይመስላል፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ከነሣው ሥጋና ነፍስ ጋር ያለ መቀየጥና ያለመጠፋፋት አንድ ሆኖአል፡፡ ውሕደቱም እጅግ ጠሊቅና ከመረዳት ያለፈ ነው፤ እንዴት እንዲህ ሆነ? ብሎ ለሚጠይቅ ግን እንዲህ ያደረገ እርሱ ያውቃል ነው መልሳችን”ብሎ ይመልሳል፡፡ ተዋሕዶዉን እርሱ ብቻ የሚያውቀው ለእኛ ግን ከመረዳት ያለፈ ከሆነ እንዴት እኛን የወደደበትን የፍቅሩን ከፍታ በቃላት ማስረዳት ይቻለናል?
ይህ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተባልነው በእኛና በክርስቶስ መካከል በጥምቀት የተፈጸመውን ተዋሕዶንም ይመስላል፡፡ ለተዋሕዶውም ምክንያት የሆነውም የባሕርይው ፍቅሩ ነው፡፡ ወልድን ከመንበሩ ስቦ ለሞት ያበቃውም ይኸው ፍቅሩ ነው፤ ይህ ፍቅር ለጾታዊ ፍቅር አማናዊው ምሳሌ ነው፡፡ ሰለዚህም ከክርስቶስ እንደተማርነው ከትዳር በፊት የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነው ጸታዊ ፍቅር ሊቀድም ይገባዋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ጾታዊ ፍቅርን መሥራቱ ለዚህ ተዋሕዶ እንዲረዳ ነው፡፡ ስለዚህም ይህን ፍቅር ድንቅ ብንለው ቢያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይደለም፡፡ ምክንያቱም መሠረቱ ሰማያዊው ነውና፡፡ ይህ እንደሆነ እንረዳውም ዘንድ በጌታችን በመድኀኒታችን ሰው መሆን አሳየን፡፡ እርሱ በሥጋ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ ሲሆን ረቀቂ የሆነው ፍቅር በእርሱ ሰው መሆን በአካል ተገልጠ፡፡ ስለዚህም በክርስቶስ እኛ የአባቱን መልክ ስንመለከት አባቱ እግዚአብሔር አብ ደግሞ ምንም እንኳ በእርሱ ዘንድ የኛ ተፈጥሮ የተሰወረ ባይሆንም በልጁ በክርስቶስ ውስጥ እኛን ይመለከተናል፡፡ ይህ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ ግሩም መሰኘቱም ለዚህ ነው፡፡
እስቲ የዚህን ፍቅር ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር ያለውን ተዛምዶ እንመልከት፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
አስተምህሮ ሰው በእግዚአብሔር ውስጥ ያለው ሥሉስትነት እንዲታይበት ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ (ሥሉስትነት የሚለውን ቃል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን (Communion) የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ለማስረዳት ተጠቅሜበታለሁ፡፡ በጥሬ ትርጉሙ ማኅበራዊነት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ጽንሰ ሃሳቡን የሚያስረዳ ቃል ሆኖ ስላላገኘሁት ለዚህ ጽንሰ ሃሳብ ይህን ቃል ሰጥቼዋለሁ)
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው” የሚለውን ትርጉም በጽኑ የሚቃወም አባት ነው፡፡ እንደ እርሱ
አስተምሮ የሰው ማኅበራዊነት መሠረቱ በእግዚአብሔር ውስጥ የሚታየው አንድነትና ሦስትነት ነው፡፡ በእርግጥም ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው ብለን የምንረዳ ከሆነ ለጾታዊ ፍቅር የምንሰጠው ትርጉምና ዋጋ በእጅጉ ያነሰና የተዋረደ ይሆንብናል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ውስጥ
ያለው ሥሉስትነት በሰዎች ውስጥ እንዲታይ እግዚአብሔር አምላክ ፍቅርን በሰዎች ውስጥ ተከላት ብለን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የምንረዳ ከሆነ
ስለጾታዊ ፍቅር የሚኖረን ግንዛቤ እጅግ ጥልቅና ፍጹም መንፈሳዊ ይሆንልናል፡፡ ስለዚህም አቃልለንና አንኳሰን ከመረዳት ተከልክለን
ወደዚህ ፍቅር ከመግባታችን በፊት የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ ምን እንደሆነ? ምን ብናደርግ በእግዚአብሔር ውስጥ የሚታየው ሥሉስትነት
በእኛው ውስጥ ተተግብሮ እርሱን ደስ ልናሰኝ እንችላለን? የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮአችን ውስጥ እንዲፈጠሩና ለዚህ ፍቅር ትልቅ ቦታ እንድንሰጥ ያደርገናል፡፡ በእርግጥም የክርስቶስና የቤተክርስቲያን ፍቅር ምሳሌ የሆነው ይህ ፍቅር እጅግ ታላቅ ነው፡፡
በእግዚአብሔር ዘንድ አባትና እናት እንዲሁም ልጅ አለ፡፡
አባት እግዚአብሔር አብ፣ እናት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ልጅ ደግሞ እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ በስምና በአካል እንዲሁም በግብር
ሦስት የሆነው እግዚአብሔር በመለኮት ግን አንድ ነው፡፡ እንዲሁ ይህ ሥሉስትነት በሰውም ዘንድ ይታያል፡፡ በሰው ዘንድ አባት፣ እናት፣ ልጅ አሉ፡፡ በስም በግብርና በአካል ሦስት ቢባሉም በመገኛቸው በአዳም ተፈጥሮ አንድ ናቸው፡፡
ይህ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር ሔዋንን ከአዳም የግራ ጎን ከፈጠራት በኋላ “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል
ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል” ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህ ቦታ ሰው የተባለው አዳም ነው አባትና እናት የተባሉት እነማን ናቸው? በአባት ቦታ
እግዚአብሔር አብ አለ ፤ በእናት ቦታ ማን ሊሆን ነው? መቼም እግዚአብሔር ወልድ አንልም፤ ምክንያቱም
ስሙ በራሱ ይህን እንድንል አይፈቅድልንምና፡፡ ከዚህ ተነሥተን በዚህ ቦታ እናት የተባለው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ቢሆንም መንፈስ ቅዱስን እናት ብሎ መጥራት በኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በሶርያ ቅዱሳን አባቶች ዘንድ በጣም
የታወቀ ነው፡፡
የሶርያ ቅዱሳን
አባቶች በተለይ ያዕቆብ ዘንጽቢን(አፍርሃት) ዘፍ.2፡25ን በመጥቀስ እናት የተባለው መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በዚህ ጉዳይ
ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ “ይህ ምሥጢር(በእውነት) ታላቅ ነው” የሚለውን ጽሑፌን ይመልከቱት፡፡ ስለዚህም ወደ ቃሉ ትርጉም
ስንመጣ "ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል" ሲል አዳም እግዚአብሔር አብ አባቱን፣ እግዚአብሔር
መንፈስ ቅዱስ እናቱን ይተዋል ከሔዋን ጋርም አንድ ይሆናል እያለን ሳይሆን በሥላሴ ውስጥ ያለውን ሥሉስትነት ምሳሌ አድረጎ አዳም ቤተሰብን ይመሠርታል፤ ሙሉ ሰው ሆኖአልና ሲለን ነው፡፡ ስለዚህም ነው ጾታዊ ፍቅር ሰማያዊ ነው ስንል መሠረቱ ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር በእጅጉ
የተዛመደ ነው ማለታችን፡፡ ይቀጥላል….
kale hiwot yasemaln wedmachin tsegawn yabzalh ye agelgulot zemenhn yrzmlh Egziabhier !!!
ReplyDeletekale hiwoten yasemalen EGIZABEHER AMELAK tsegawn yabzaleh yagelgeloten zemenhen yarezemelen !!!
ReplyDelete