Monday, February 13, 2012

ለእኛስ የፍቅረኞች ቀን ይኖረን ይሆንን?(ቀጣይ ጽሑፍ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/06/2004
... ከእዚህ መንደርደሪያ አሳብ ተነሥተን ጾታዊ ፍቅር የተገለጠው መቼ ነው ብለን ብንጠይቅ ሔዋን ከአዳም የግራ ጎን ከተገኘች በኋላ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዚያን ጊዜ አባታችን አዳም እግዚአብሔር ከጎኑ አጥንት የፈጠራትን ሴት በተመለከተ ጊዜ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት” በማለት ለእርሱዋ ያለውን ፍቅር ለአምላኩ ገለጠ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በገነት በአዳምና በሔዋን መካከል ትዳርን መሠረተ፡፡እግዚአብሔርም "ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል(ይተባበራል)" አለ፡፡ ስለዚህም ለአዳምና ለሔዋን እቺ ዕለት የደስታቸው ቀን ናትና መቼም ቢሆን የሚረሱዋት ቀን አይደለችም፡፡
ይህ በሰማያት የተሠራው ሰማያዊ ሥርዐት ከውድቀትም በኋላም ቀጥሎአል፡፡ ስለዚህም በዚህ ፍቅር እርስ በእርሳችን እንሳሳባለን በትዳርም እንታሰራለን፡፡ ሥርዐቱም ሰማያዊ ነውና ፍቺ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ ፍቺ ተፈጸመ ማለት ትዳሩ ከሰማያዊው ሥርዐት ወጣ እንስሳዊ ሆነ  ቅድስናውን አጣ ማለት ነው፡፡ ያም ማለት ምን ማለት መሰላችሁ በሥላሴ ውስጥ ያለው አንድነትና ሦስትነት መልኩን አጣ ከተፈጠርንበት ዓላማ ወጣን ማለት ነው፡፡



የዚህን ፍቅር ክብር በጥልቀት እንድንረዳውና እንድንጠቀምበት የሆነው ግን ስሙ ይክበር ከፍ ከፍ ይበልና በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እኛን ለማዳን ራሱን ዝቅ በማድረግ ከቤተክርስቲያን ጋር አንድ አካል ሆነ፡፡ ይህን  ተዋሕዶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡-"መዝሙረኛው ስለቤተክርስቲያንና ስለክርስቶስ "ልጄ ሆይ ጆሮሽን አዘንብይ ወገንሽንና የአባትሽን ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዷልና"(መዝ.44፡10-11)ብሎ አስቀድሞ የተናገረው ቃል እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ክርስቶስ  "ከአባቴ ወጥቼ መጥቻለሁ" (የዮሐ.16፡18)አለ" በማለት ይገልጠዋል፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ወልድ ከአባቱ በመውጣት ከቤተክርስቲያን ጋር አንድ አካል መሆኑን ነው፡፡ ይህም አስቀድሞ ለአዳም "ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል" ተብሎ የተነገረው በዳግማዊው አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ መፈጸሙን እናስተውላለን፡፡ 
 ይህን ቅዱስ የሆነን ተዋሕዶ ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ሕዋሳት ናችሁ፡፡”(1ቆሮ.12፡27)በማለት ገልጾታል፡፡ ይህ ፍጹም የሆነ ተዋሕዶ እውን የሆነውም“አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል አንድንሆን ተጠምቀናልና”(1ቆሮ.12፡13) እንዲል በጥምቀት ነው፡፡ ስለዚህም ለእኛ ክርስቲያኖች የፍቅረኞች ቀን ልትባል የሚገባት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን የመሠረተባት ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን የሰማያዊው ሙሽራ ሚዜ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” ብሎ ክርስቶስ እንዲያው እኛን ስለወደደን የራሱ ሊያደርገን ከቅድስት እናታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት የአካሉ ሕዋሳት እንድንሆን መፍቀዱን ገለጠልን፡፡
ስለዚህም በዚህች ቀን ወንዱ አፍቃሪ ክርስቶስን አብነት አድርጎ ለፍቅረኛው እንደ ክርስቶስ ነፍሱን አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ እንደሚወዳትና እንደሚያፈቅራት ሊገልጥላት እርሱዋም ቤተክርስቲያንን አብነት አድርጋ ለእርሱ ታመና በንጽሕናና በቅድስና እንዲሁም በቅዱስ ጋብቻ ተሳስራ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ ከእርሱ ጋር ልትኖር መፍቀዱዋን ልትገልጥለት ይገባታል፡፡ በትዳር የተሳሰሩ ፍቅረኞችም ቤተክርስቲያን የጌታን ጥምቀት በየዓመቱ እንደምታስብ እነርሱም በጾታዊ ፍቅር ተቀራርበው በትዳር አንድ የሆኑባትን ያቺን ጣፋች የሆነችዋን ዕለት በፍቅር እያሰቡ አምላካቸውን የሚያመሰግኑባት ዕለት እንዲያደርጉዋት ምክሬ ነው፡፡በመጨረሻም በትዳር ውስጥ ላላችሁትም ወደ ትዳር ላልገባችሁትም ፍቅረኞች ሁሉ  በክርስቶስና በቤተክርስቲያን ስም መልካም የፍቅር ሳምንት እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ፡፡    

No comments:

Post a Comment