Tuesday, February 14, 2012

እግዚአብሔርን ከማወቅ ጋር ፆታዊ ፍቅር ጣፋጭ!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/06/2004


ፆታዊ ፍቅር ክርስቶስን በማወቅ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እጅግ ጣፋጭና ማራኪ ይሆንልናል፡፡ እንዲያ ከሆነ ባል በሚስቱ ተፈጥሮ በኩል የጌታውን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ እኛን መንፈሳዊያን ያደረገንን መንፈስ ቅዱስን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ይመለከትባታል፡፡ ሚስትም በባሎዋ መስታወትነት ለሔዋን እናትም አባትም የሆነውን ቀዳማዊ አዳምንና እርሱዋን ከጎኑ በፈሰሰው መለኮታዊ ውኃ አንጽቶ ከጎኑ በፈሰሰው ክቡር ደሙ ተቤዥቶ የወለዳትን ዳግማዊውን አዳም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትመለከተዋለች፡፡ በሚወልዱአቸው ልጆቻቸው ውስጥም በሥጋ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም እቅፍ የነበረውን፣ እንደ እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅነቱ ግን ከአባቱ እቅፍ የሆነውን ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስን በአንድነት በልጆቻቸው ይመለከቱታል፡፡

እናት ልጁዋን ስታጠባ አምላክ በአርአያ ሕጻናት ተገኝቶ ከእናቱና ከእናታችን ከቅድስት ደንግል ማርያም ጡት መጥባቱን፣ እንደ ሕፃናት መዳሁን፣ በኮልታፋና ጣፋጭ በሆነ አንደበቱ እናቱን ደስ ማሰኘቱን፤ ጠረኑን፣ መዓዛውን፣ ፍልቅልቅና ብሩህ ገጽታውን በዐይነ ሕሊናዋ ትመለከተዋለች፡፡ “በልብሽ ሰይፍ ያልፋል” የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጽሞ ድንግል ሁለት ዓመት የሞላውን ልጁዋን አዝላ ወደ ግብፅ በርሃ ስለልጁዋ መሰደዱዋን በልጁዋም ምክንያት የተቀበለቻቸውን ጽኑ ጽኑ መከራዎች ሁሉ ታስባለች፡፡ድንገትም እንባ ከዐይኖቹዋ መንጭተው በጉንጮቹዋ ኩልል ብለው ይወርዳሉ፡፡ የዐሥራ ሁለት ዓመት ብላቴና በነበረበት ወቅትም በቤተ መቅደስ የአይሁድ ሊቃውንትን በጥያቄ እንደወጠራቸው ትመለከታለች፡፡ አባትም በፈንታው እንደ ቅዱስ ዮሴፍ እነዚህን ሁሉ ያስተውላቸዋል፣ ያደንቃልም፤ ልቡ የሰዎች ፍቅር አገብሮት በተወለደው ሕፃን ፍቅር ይቃጠልበታል፡፡ ግሩም ነው!!!
ስለዚህም እናት ክርስቶስን እያሰበች ልጆቹዋ እርሱን መስለው እንዲያድጉ ትሠራቸው ዘንድ ትነሣለች፡፡ አባትም እንዲሁ ለሚስቱና ለልጆቹ በሚያሳየው እንክብካቤና ፍቅር ክርስቶስ ኢየሱስ እንዴት ያለ ርኅሩኁ አባት እንደሆነ ለልጆቹ ለማስተማር ይተጋል፡፡ ስለዚህም ልጆቹ በእናቱ ቤተክርስቲያንን፣ በእርሱ ደግሞ ክርስቶስን መስለው ያድጋሉ ይመነደጋሉ ኦ እንዴት ደስ ይላል!!!
ይህ ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለን አንጠይቅ፡፡ ለወደደን ራሱን እስከ መስጠት ደርሶ ላፈቀረን ጌታ ፍቅሩ ካለን ሁሉ ይቻለናል፡፡ አድርገውም ያሳዩን ፍቅረኞች ብዙዎች ናቸው፡፡ እኛም እንደ እነርሱ እንዳንፈጸም ምንም የሚከለክለን ነገር የለም፤ ምክንያቱም እውነትን የሚገልጸው መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለና፡፡ ብቻ እኛን እስከ መምሰል ደርሶ ያፈቀረንን እግዚአብሔርን እኛም እናፍቅረው፡፡ እንዲያ ከሆነ በክርስቶስ ፍቅር ተማርከው ቤታቸውን እንኳ ቤተክርስቲያን እስከ ማድረግ የደረሱትንና አጵሎስን በወንጌል ቀርጸው የቅዱስ ጳውሎስ ቀኝ እጅ ያደረጉትን አቂላንና ጵርስቅላን እንመስላቸዋለን፡፡(የሐዋ.18፡24-26፣ሮሜ16፡3-5) ልክ እንደ ጢሞቴዎስ ወላጆች ልጆቻችንን ከልጅነታቸው ጀምሮ ሕይወት የሚገኝባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማስተማር ማሳደግን እናቅበታለን፡፡(2ጢሞ.3፡14) እንዲህ ሆኖ እግዚአብሔርን በማወቅ ላይ የተመሠረተ ፍቅር እንዴት ውብ፣ ማራኪና ጣፋጭ ነው!!! አዎን እግዚአብሔርን በሚያውቁ ፍቅረኞች መካከል ያለ ፍቅር እጅግ ግሩምና ጣፈጭ ነው!!
ይህ ዓይነት ሕይወት ምንም እንኳ ልጆች አይውለዱ እንጂ በገነት በአዳምና በሔዋን ላይ የታየ ሕይወት ነበር፡፡ በዛን ጊዜ /ከውድቀት በፊት/ ፆታዊ ፍቅር በራሱ አንዳቸው ጉድለት የሌለበት ሙሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን በማወቅና በእርሱ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነበርና ነው፡፡
ይህ ያለንበት ዘመን ደግሞ ይክብር ይመስገንና እግዚአብሔርን ለማወቅ ሲባል ሀገር አቋርጦ መሄድን የሚጠይቅ ዘመን አይደለም፡፡ ስለእግዚአብሔር ለሚጠይቅ ሁሉ የሚመለሱለት ቅዱሳት መጽሐፍት በዙሪያችን አሉ፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችንም ብዙ እጅግ ብዙ ስለክርስትና ሕይወታችን ጽፈውልናል፡፡ ከእነዚህ ግን በእጅጉ የሚልቀው በልቡናችን ሰሌዳ ሕጉን የሚጽፈልን መንፈስ ቅዱስ ሰውነታችንን ቤተመቅደሱ አድርጎ በእኛ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ ስለዚህም የቀድሞውን የአዳምንና የሔዋንን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሕይወት ገንዘባችን ማድረግ አሁን አይሳነንም፡፡ ኦ ይህ ትውልድ እንዴት የታደለ ትውልድ ነው!!! እግዚአብሔርን ለመምሰል ምንም ያጣው ወይም የጎደለው ነገር የለም፡፡ ይህን በአግባቡ ተጠቅሞበት ጾታዊ ፍቅሩን እግዚአብሔርን በማወቅ ላይ የመሠረተ እንደሆነ ሰማያዊው በረከት ከቤቱ ፈስሶ ምድሪቱን በፍቅር ጅረት ያረሰርሳታል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞንም እግዚአብሔርን በማወቅ ላይ የተመሠረተ ሕይወትን በተመለከተ በመክብቡ “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላልና ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋል” ካለ በኋላ “አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ በሦስትም የተገመደ ገመድ አይበጠስም” መክ 4.8-12 ብሉ ጥብቀቱን ተናገረ፡፡ አንደኛው ገመድ ባል ነው ሁለተኛዋ ገመድ ደግሞ ሚስት ናት ሦስተኛው ትዳሩን እጅግ ያጠበቀው ገመድ ግን እግዚአብሔር ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ የሆነ ቤተሰብ ምን እንደሚመስል ሲናገር፡-“ከምንጭ ውኃ እንዲፈልቅ መልካም በረከቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ከሚፈራ ቤት ፈልቆ ይፈሳል፡፡ እናም ቤቱ የእልፍ እልፍ በሆኑ በረከቶች ይሞላል፤ የማያልፈውን በሻትን ጊዜ የሚያልፉትን ምድራዊ በረከቶችን ጨምረን እናገኛለን … እንዲህ ከመሰሉ ቤተሰቦች የሚገኙ ልጆች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ እስቲ እናስብ … ፍቅርን የተማሩ አንድ ዓይነት ቋንቋን ይናገራሉ ፍቅርን አስተምረዋቸዋልና የእነርሱን ፈለግ ይከተላሉ፡፡” እኔም በትዳር ውስጥ ላሉትም ወደዚህ ሕይወት እየመጡ ላሉትም ፍቅረኞች መልካም የፍቅር ሳምንት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ!!!
ምስጋና ይሁን ፍቅር ለሆነው ለአብ ለወልድ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!

No comments:

Post a Comment