ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/06/2004
ውስጣዊ የሆነችው የነፍሳችን ዐይን
መመልከት የምትችለው በእምነት ነው፡፡ በእምነት ዐይናችን እግዚአብሔር በመጽሐፍ እና በዐይን በሚታየው በዚህ ዓለም ሰውሮ ያስቀመጣቸውን
ምሳሌዎችን መረዳት እንችላለን፡፡ ውጫዊዋ ዐይናችን በፀሐይ ብርሃን ታግዛ መመልከት እንድትችል ውስጣዊዋ የነፍስ ዐይናችንም በእምነት ብርሃን ታግዛ መንፈሳዊውን ዓለም ትመረምራለች ትመለከታለች፡፡ ነገር ግን ይህች
የነፍስ ዐይናችን በኃጢአት ምክንያት ልትታወር ትችላለች፡፡ ውስጣዊዋ ዐይናችን በደንብ መመልከት እንድትችል ለማድረግ ንጽሕትና ጥርት ያለች መሆን አለባት፤ እርሱም ከኃጢአት ነው፡፡ ውስጣዊዋ ዐይናችን ንጽሕትና ጥርት ያለች ስትሆን ቅዱስ ኤፍሬም እንደሚለው “ብርህት ዐይን” ተብላ ትጠራለች፡፡
ይህች ቃል በቅዱስ ኤፍሬምና በሌሎችም የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ዘንድ የምትዘወተር ቃል ናት፡፡
ውስጣዊው የነፍሳችን ዐይኖች የበሩ
እንደሆነ ብቻ ነው የእግዚአብሔርን ሥራና ፈቃድ ማስተዋልና በሥነፍጥረትና በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን ምሳሌዎችን መረዳት
የምንችለው፡፡ “ቅዱሳት መጻሕፍት ፊታችንን እንደምንመለከትባቸው
መስታወቶች ናቸው፡፡ ዐይኖቹ ብሩሃን የሆኑለት ሰው በእነርሱ ውስጥ እርሱ በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል እንደተፈጠረ ይረዳባችኋል፡፡” (ቅዱስ ኤፍሬም)
የማየት ብቃታችንም ሊያድግ የሚችለው እምነታችን ያደገና የጨመረ እንደሆነ ነው፡፡ የነፍስ
ዐይናችን በጣም ብርህት በሆነች ቁጥር እግዚአብሔራዊ እውነታዎችን በይበልጥ እየተረዳን እንመጣለን፡፡ አንዲት ነፍስ አንድን
እግዚአብሔራዊ እውነት በተለያየ አቅጣጫ መረዳት የቻለች እንደሆነ የዚህች ነፍስ ዐይኖች ብሩሃን ናቸው ማለት ነው፡፡
ከሰው ልጆች መካከል
ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በላይ እጅግ ብሩሃን ዐይኖች ያሉት ሰው የለም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሔዋንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን ለዓለም ሁለቱ
ውስጣዊ ዐይኖች ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ አንደኛው የታወረና አጥርቶ ማየት የተሳነው ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ዘመን ይወክላል ሁለተኛው ግን ብሩህና አጥርቶ
የሚያይ ዐይን ነው፡፡ ይህም በአዲስ ኪዳን ያለውን ዘመን ይወክላል፡፡
“ቅድስት ድንግል ማርያምና ሔዋን በአንድ አካል ላይ ያሉትን ሁለት ዐይኖችን ይመስላሉ፡፡
አንደኛው እውርና በጨለማ የተዋጠ ሲሆን ሁለተኛው ግን ንጹሕና ብሩህ ስለሆነ ለዓለም ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን ለማየት የሚያበቃ ነው፡፡
የምትታየው ዓለም ሁለት ዐይኖች ያሏት ዓለም ናት፡፡ ሔዋን ለብሉዩ ዘመን ዐይኑ ስትሆን እርሱዋም የታወረች ነበረች፡፡ የአዲስ ኪዳኗ ዐይን ግን ብርህት ናት ፤ እርሱዋም ቅድስት ድንግል ማርያም
ናት፡፡ ጨለማ ወርሶት በነበረው በብሉዩ ዘመን ዐይን (በሔዋን) ምክንያት ዓለሙ ሁሉ በጨለማ ተውጦ ነበር፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ ከድንጋይና
ከእንጨት የተሠሩትን ጣዖታትን ሁሉ አምላክ ብሎ ተሰነካከለባቸው፡፡ ነገር ግን በአዲስ ኪዳኗ ዐይን(በድንግል ማርያም) ለማየት ሲበቃ ክርስቶስ ኢየሱስን በእምነት ለማየት ቻለ፡፡ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ፡፡ በክርስቶስ ያመኑቱ አስቀድመው እነርሱ የተሰናከሉባቸውን የድንጋይና የእንጨት
ጣዖታትን በቅድስት ድንግል ማርያም የእምነት ዐይን ሲመለከቱአቸው ከአምላካቸው አርቀው እንዳጠፏቸው ተገነዘቡ፡፡”(ቅዱስ ኤፍሬም)
አዎ ድንግል ሆይ ባንቺ ክርስቶስን ተመልክተናልና እናመሰግንሻለን፣ እናከብርሻለን፣ እንወድሻለን!! በእርግጥም አንቺን በእምነት ስንመስል ለአንቺ እውነት፣ ለእኛም እምነት የሆነውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተመለከትነው፡፡ ድንግል ሆይ አንቺን በእምነት ያልመሰሉ እንዴት ክርስቶስን ሊያዩት፣ በእጃቸውም ሊዳስሱት፣ መዓዛውን ሊያሸቱት፣
ሊያፈቅሩት፣ ሊያከብሩትና ፈቃዱን ሊረዱ ይችላሉ?
No comments:
Post a Comment