ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/06/2004
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተጻፈ

ቅዱሳን እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ማዕከላዊ አድርጎ መፍጠሩ በዐይን የማይታዩትን መናፍስትንና የሚታዩ ፍጥረታትን ሁሉ እርሱ እንደፈጠረና ግዢያቸው እንደሆነ ምስክር እንዲሆነው ነው ይላሉ፡፡ ባጠቃላይ ሰው /Human beings/ የእግዚአብሔር የገዢነቱ ምልክት ነው፡፡
ስለዚህም አዳም በነፍስ ተፈጥሮው መልአካዊ ባሕርይ ሲኖርው በሥጋው ባሕርይው ደግሞ እንስሳዊ ባሕርይ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት አዳም በሥጋው ባሕርይው ምክንያት ልክ እንደ እንስሳት ለመኖር መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮች የተባሉት ሁሉ ለእርሱ የተገቡ ሆኑ፡፡

የነፍስ ተፈጥሮ ከተዋሐደችው ሥጋ ስለሚበልጥ እግዚአብሔር ለተዋሐደችው ሥጋ ሕይወት ሰጪ በማድረግ በሥጋና ለሥጋ በሆኑት ሁሉ ላይ ገዢና መሪ አድርጎ ሾማት፡፡ እርሷን ደግሞ የመናፍስት አምላክ ይገዛታል፡፡ አዳም የሥጋ ባሕርይውን በትክክል ማስተዋል የጀመረው እግዚአብሔር አምላክ ለምድር እንስሳት ሁሉ ስም ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እርሱ ባቀረበለት ጊዜ ነበር፡፡
አዳም እንስሳት ጥንድ ጥንድ ሆነው ወደእርሱ ሲቀርቡ ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ ልቡ በከባድ ሃዘን ተመታ፣ አንዱ ጸሐፊ የአዳምን ብቸኝነት እንዲህ ይገልጸዋል “perfect
solitude would turn a paradise in to a desert, and a palace in to dungeon” ፍጹም ብቸኝነት ገነትን ጭው ወዳለ በረሃነት፤ ቤተ መንግሥትን ወደ ወህኒ ቤት ሊቀይረው ይችላል፡፡" ግሩም ነው! እውነትም ነው! ምክንያቱም በሥጋው ተፈጥሮ የተቃራኒ ጾታ ፈቃድ ነበረውና፡፡ እግዚአብሔርም ይህንን ማድረጉ ያለ ምክንያት አልነበረም፤ አዳም ባሕርይውን እንዲገነዘብ እንጂ፡፡ አዳም በነፍስ ባሕርይው መላእክትን ቢመስልም ነገር ግን በሥጋው ባሕርይው ስለሚለይ፤ በሥጋው ባሕርይው እንስሳትን ቢመስልም በነፍስ ተፈጥሮ ስለሚለይ እንደ እርሱ የሆነ ፍጥረት ባለመኖሩ በዚያች የደስታ መፍሰሻ ገነት ውስጥ ቆዘመ ተከዘ፡፡ እናቱ ምድር ምስያውን ሳታስገኝለት ለዘላለም አሸልባለችና አዘነ፣ በብቸኝነት ተብሰከሰከ፡፡ ይህን ያስተዋለ እግዚአብሔር “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸው ረዳት እንፍጠርለት”አለ፡፡

ከማሁ ይኩን ለነ በከመ ፈቃደከ አሜን!!
እንደ ፈቃድህ ለእኛም ይሁንልን ይደረግልን አሜን!!
እንደ ፈቃድህ ለእኛም ይሁንልን ይደረግልን አሜን!!
No comments:
Post a Comment