Tuesday, February 7, 2012

“ራስን የመግዛት ጥበብ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
30/04/2004
ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ “ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ማለት ነው፤ ጥበብ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም ፍልስፍና ማለት እግዚአብሔርን ማፍቀር ማለት ነው”ብሎ ያስተምራል፡፡ እኛም በበኩላችን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ሰውም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ እንላለን፡፡ አንድ ጸሐፊ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር፡- “እግዚአብሔር ሰውን ከፍቅር አፈር አበጀው፡፡ ስለዚህም ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ፤ ስለዚህም ሰው ፍቅር ሲያጣ እንደ በድን ሬሳ ሲቆጠር በፍቅር ውስጥ ካለ ሕያው ነው፡፡ ሕይወቱም እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔርም ፍቅር ነው፡፡” ስለዚህም ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ፍቅርን መሠረት ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለፍልስፍና ትምህርታችን መንደርደሪያ የሚሆነን ፍቅር የሆነውን ተፈጥሮአችንን በሚገባ ማወቃችንና መረዳታችን ነው፡፡
  ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረውን ሰውን ትንሹ ዓለም ይለዋል፡፡ እንዲህም ያለበት ምክንያት ሰማያዊና ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ረቂቅ በሆነችው የነፍስ ተፈጥሮው በኩል ረቂቃን ከሆኑ መናፍስት ጋር አኗኗሩን ሲያደርግ፤ ግዙፍ በሆነችው ሥጋዊ ተፈጥሮው በኩል ደግሞ በምድር ፍጥረታት ላይ ገዢ ሆኖ ጠቅሟቸውም ተጠቅሞባቸውም ይኖራል፡፡ ስለዚህም ነው ሰው በሁለት ዓለማት እኩል የሚኖር ፍጥረት ነው መባሉ፡፡ ወይም ሰው የሁለት አካላት ውሕደት ውጤት ነው፡፡
 ነፍስ የራሱዋ የሆነ አካል ያላት ስትሆን በዚህ ተፈጥሮአዋ መላእክትን ትመስላቸዋለች፣ እንደ ምግባሩዋ ከቅዱሳን ወይም ከርኩሳን መናፍስት ጋር ኅብረትን ትፈጥራለች፡፡ በነፍስ ሕያው ሆና የምትኖር ሥጋችንም ከዚህ ዓለም ጋር ተመጋግባና ተግባብታ ለመኖር የሚረዳት የራሱዋ የሆነ አካላዊ ተፈጥሮ ያላት ናት፡፡ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ለመንፈሳዊያንና(በእርሱ ዘንድ ረቂቃን አይደሉም) ለምድራዊያን ፍጥረታት ሕይወትን ሰጥቶ እንደሚያኖራቸው እንዲሁ ነፍስም ለሥጋ ሕይወትን ሰጥታ ታኖራታለች፡፡ በዚህም ተፈጥሮአችን አምላክን እንመስለዋለን፡፡ “ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ የራሱን መልክ እንዲሥል እንዲሁ እግዚአብሔር ነፍስና ሥጋን በማዋሐድ የራሱን መልክ በመሳል ሰው አድርጎ ፈጠረው፡፡”(ቅዱስ ኤፍሬም)  
ነፍስ ከሥጋ ተፈጥሮአዋ ሳትለይ ከመንፈሳዊያን ፍጥረታት ጋር ኅብረትን መፍጠር ይቻላታል፡፡ ሥጋም ከነፍስ ሳትለይ ነፍስ ሕይወት ሆናት ለራሷ ሕልውና ጠቃሚ የሆኑትን ተግባራት በምድር ላይ ታከናውናለች፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አድርጎ ሰውን ከፈጠረው በኋላ የሕይወት እስትንፋስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ በአፍንጫው እፍ አለበት፡፡ (አክሲማሮስ ገጽ.156) መንፈስ ቅዱስም ለነፍሳችን እውነተኛን እውቀት በመግለጥ፤ ነፍስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሥጋዋን እንድትመራት ይረዳታል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዲህ አድርጎ ፈጠረው፡፡ ስለዚህም ሰው ማለት ሥጋው ለነፍሱ፣ ነፍሱም ለመንፈስ ቅዱስ የሚገዙለት ፍጥረት ማለት ነው፡፡
 አንድ ሰው ይልቁኑ አንድ ክርስቲያን ይህ ሰብአዊ ተዋቅሮውን ካወቀ እግዚአብሔር እርሱን ለምን ዓላማ እንደፈጠረው ይረዳል፡፡ ስለዚህም ነው የትምህርት መጀመሪያው ራስን ማወቅ ነው ብለው ቅዱሳን አባቶች ማስተማራቸው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም “ማንነትህን የማታውቅ ከሆነ የፈጣሪህን ቃል መስማት እንዴት ይቻልሃል?”ሲል፣ ቅዱስ ባሲልዮስ ዘቂሳርያ ደግሞ “ከትምህርቶች ሁሉ ታላቁ ትምህርት ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ከአወቀ እግዚአብሔርን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ከአወቀ ደግሞ እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል” ብሎ ያስተማረው፡፡ ራስን ማወቅ የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት ነው፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን ራስን የማወቅ ጥበብን በሦስት የእውቀት እርከኖች ከፋፍለው ያስቀምጡታል፡፡ የመጀመሪያው እርከን ማንነትን መረዳት ነው፡፡ ይህ እርከን ተፈጥሮአዊ መዋቅርን የመረዳት እርከን(carnal stage)ተብሎ ይታወቃል፡፡ ያም ማለት የራስን ተፈጥሮዊ ጠባይ ማወቅ ማለት ነው፡፡ ሰው ራሱን ካወቀ ራሱን ለመግዛትና እንደ ፈጠሪው ፈቃድ ለመመላለስ መሠረት ይጥላል፡፡ ራሳችንን ካወቅን በኋላ የሚቀጥለው የእውቀት እርከን መንፈሳዊያኑንና ምድራዊያኑን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ተጠቅመን አካባቢያችንን መረዳት ነው፡፡ በዚህ እርከን ውስጥ ስንገኝ በዙሪያችን ያሉትን ረቂቃን መናፍስትንና ግዙፋን ፍጥረታትን ወደ መረዳትና ከእነርሱ ጋር ግንኙትን ወደ መጀመር እንመጣለን፡፡ ይህም የለብዎ እርከን(sensual stage)ይባላል፡፡  ሦስተኛውና የመጨረሻው እርከን መንፈሳዊያን ሆነን የምንመላለስበት እርከን ሲሆን መንፈሳዊ እርከን ተብሎ ይታወቃል(spiritual stage)፡፡ ይህ የቅዱሳን መላእክትንና የአጋንንትን ንግግር የምንለይበትና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የምንመላለስበት የእውቀት ወይም የቅድስና እርከን ነው፡፡ ይህን እርከን ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም፡፡ እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን”በማለት የገለጸው ነው፡፡(1ቆሮ.2፡15-16)
አንድ ሰው መንፈሳዊ ነው የምንለውም እነዚህ የእውቀት እርከኖችን አልፎ የመንፈስ ቅዱስን መልእክት ማዳመጥና መለየት ወደሚችልበት እርከን ሲሸጋገር ነው፡፡ ይህን ለማስረዳት ቅዱሳን “በክርስቶስ ያመነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ዘመኑ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፤ እግዚአብሔር ያውቃል ያ ሰው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ነጥቀው ወሰዱት”(2ቆሮ.12፡2)ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ይጠቀማሉ፡፡ እንደ ቅዱሳኑ አስተምህሮ ሦስቱ ሰማያት የተባሉት ቅዱሱ ያለፈባፋቸውን ሁለቱን የእውቀት እርከኖችንና በስተመጨረሻ የደረሰበትን የእርሱን የእውቀት ከፍታን ነው፡፡ በዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ የሚገኝ ቅዱስ በዚህ ምድር ሳለ የትንሣኤን ሕይወት ጣዕም መቅመስ ይጀምራል፡፡ ይህም ማለት  ከአምላክ ጋር፣ ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር ለመነጋገር የበቃ ይሆናል፣ የአጋንንትንም ምክርና አሳብ ይለያል፣ በሰው ልቡና የሚመላለሰውን ክፉም ይሁን በጎ አሳብ ማወቅና መረዳት ይችላል፣ መጪውን ያውቃል፡፡ እነኝህን ሁሉ ግን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ነው፡፡
 ነፍስ ለሥጋ ብርሃኗ እንደሆነች ለነፍስም ብርሃኗ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ረቂቁን መንፈሳዊ ዓለም መረዳት አይቻለንም፡፡ በዚህም ላይ ጨምረን ነፍሳችንን ከኃጢአት ንጹሕ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ያለበለዚያ እውር ድንብራቸውን እንደሚመላለሱ ወገኖች እንሆናለን፡፡ ይህን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው” ብሎ የገለጸው ዓይነት ሕይወት ነው፡፡ (ዮሐ.፭፥፳፭)ወንድሜ ሆይ በዚህ ቦታ ሙታን ያላቸው ነፍሳቸው የተለየቻቸውንና ወደ መቃብር የወረዱትን ወገኖችን ነውን ? ስለሰማያዊው አኗኗራቸው ፈጽመው የማያቁትን አይደለምን ? ይህ ኃይለ ቃል ምን አልባት ግልጽ ላይሆን ይችላል፤ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን እርሱን ለሚከተል ደቀመዝሙር የተናገረውን እስቲ እናስተውለው፤ “ኢየሱስም፡- ተከተለኝ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው”(ማቴ.፰፥፳፪) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ከምድራዊ ሕይወት ጋር የተጣበቁት እነዚህ ወገኖች በቁም ሳሉ ሙታን እንደሆኑ ለዚህ ደቀመዝሙሩ  አስታወቀው፡፡ የሞተ ሰው በዚህ ዓለም ምን ይፈጸም ምን አንዳች እንደማያቅ እንዲሁ እነዚህም ወገኖችም ለሰማያዊው ዓለም እንደምውት ናቸውና ስለሰማያዊ አኗኗራቸው የሚያቁት አንዳች ነገር የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሕያዋን እንደተባሉት በሁለቱም ዓለማት ታውረው እየኖሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሙታን አላቸው እንጂ በሥጋማ መሰሎቻቸውን ሊቀብሩ ተፍ ተፍ እያሉ እኮ ነው!
  ቅዱሳን “አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አደረጉ” ሲባልም ምድራዊ አኗኗራቸውን ትተው ከረቂቃኑ ፍጥረታት ጋር ኖሩ ማለት እኮ አይደለም፡፡ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ ሲባል አኗኗሩን ከምድራዊው አኗኗር ለየ ማለት ሳይሆን ሁለቱንም ዓለማት በአግባቡ ኖረባቸው ሲለን ነው፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ቤተሰብ መሥርቶ ልጆችንም ወልዶ ይኖር ነበር፡፡ በኋላም አምላኩ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወሰደው፡፡ ኖህ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ የተባለለት ቅዱስ ነው፡፡ በምድራዊ ሕይወቱም በቅድስና ተመላለሰ፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያዋን የተባሉ ቅዱሳን አባቶች ናቸው(ማቴ.፳፪፥፴፩-፴፪)በምድራዊውም አኗኗራቸው በቅድስና ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ሲመሩ የነበሩ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ይህም የሚያሳየው  ቅዱሳን በረቂቁም በግዙፉም ዓለም እኩል ሕያዋን ሆነው ይኖሩ እንደነበር ነው፡፡
በእዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ ያሉ የቅዱሳን ሕይወት ምን እንደሚመስል ሶርያዊ ቅዱስ ዮሴፍ(ባለራእይው ዮሴፍም ይባላል) እንዲህ ይገልጸዋል፡- “መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምንረዳው አእምሮአችን ፍም ብሩህ በሆነ የማስተዋል ብርሃን ሲሞላ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ በልባችን ጠፈር ላይ የሰንር ድንጋይን የመሰለ ሰማይ ተዘርግቶ ከልባችን ጠፈር ልዩ ልዩ ሕብረ ቀለማት ያሉዋቸው ብርሃ(እውቀቶች) ሲፍለቀለቁ ይታየናል፡፡ እንደነዚህ ይነት ማራኪ የሆኑ ብርሃናት በልቡናችን የሚፍለቀለቁት ሥላሴ ልቡናችን ውስጥ የባሕርይ የሆነውን ብርሃን ሲያበራልን ነው፡፡ በሥላሴ ብርሃን እገዛ የሚኖረን እውቀት ፍጥረታዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀውና እንድንረዳው የሚያደርገን ሲሆን ከዚህ አልፈን መንፈሳዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀው ያበቃናል፡፡ በመቀጠልም ስለእግዚአብሔር ቅን ፍርድና መግቦት ወደማወቅ እንመጣለን፡፡  በዚህ መልክ ከፍ ከፍ በማለት ከክርስቶስ የክብሩ ብርሃን ተካፋዮች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ከዚህ ቅዱስና ግሩም ከሆነው እይታ ስንደርስ እጅግ ውብ አድርጎ በፈጠራቸው ዓለማት በእጅጉ እንደነቃለን፡፡ ከእነርሱ የምናገኘው ማስተዋል እጅግ ታላቅ ነው፡፡ በዚህ ድንቅ በሆነ የእውቀት ከፍታ ውስጥ ስንገኝ ስለ ሁለቱ ዓለማት ያለን እውቀት እንደ ጅረት ውኃ ከአንደበታችን ሞልቶ ይፈሳል፡፡ የሚመጣውን ዓለም በዚህ ዓለም ሳለን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ እጅግ ውብ የሆነውን የመላክትን ማስተዋል ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ ደስታቸውን፣ ምስጋናቸውን፣ ክብራቸውን፣ ዝማሬአቸውን ቅኔአቸውን እንሰማለን፡፡ መላእክትን ከእነ ማዕረጋቸውና ከእነ ክብራቸው እንመለከታቸዋለን፣ እርስ በእርሳቸው  ቸውን አንድነት እንረዳለን፣ ቅዱሳን ነፍሳትን ለመመልከት እንበቃለን፣ ገነትን ማየት ከሕይወት ዛፍ መመገብን(መላእክት የሚመግቡትን የፍቅር ማዕድ ማለቱ ነው)፣ ከቅዱሳን ነፍሳትና መላእክት ጋር መነጋገርና ከዚህም ባለፈ ልዩ ልዩ በረከቶችን ለማግኘት የበቃህ እንሆናለን፡፡” ወደዚህ የቅድስና ወይም የእውቀት ከፍታ ለመወጣጣት ግን አስቀድመን እንደጻፍንላችሁ የራስን ማንነትን ማወቅ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
ከላይ ነፍሳችን በሁለቱም ዓለማት አኩል ተሳትፎ እንዳላት ተመለክተናል፡፡ ይህች ረቂቅ የሆነች ተፈጥሮአችን ሥራዎቹዋን የምታጠናቅርበት አካል አላት፡፡ ይህን ረቂቅ አካል እኛ አእምሮ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ይህች ነፍስ ሁለት ወገን የሆኑ የስሜት ሕዋሳት ሲኖሩዋት አንደኛው ወገን ረቂቁን ዓለም የምናስተውልበት ሲሆን ሁለተኛው ወገን ግን ግዙፉዋን ዓለም የምንረዳበት ነው፡፡ ነፍስ ረቂቁን ዓለም እና ግዙፉን ዓለም በምትረዳባቸው የስሜት ሕዋሳት በኩል መረጃዎችን ረቂቅ ወደሆነው የአእምሮዋ ክፍል ታስገባለች፡፡ አእምሮም በስሜት ሕዋሳቱ በኩል ያገኛቸውን  ጠቃሚ መረጃዎች ወደ ውስጠኛው የአእምሮ ክፍሉ አስገብቶ ያኖራቸዋል፡፡
እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ አእምሮአችን ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ አንደኛው ልዩ ልዩ አሳቦችን የሚያኖርበት ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል እንለዋለን፡፡ ሌላኛው ክፍል ደግሞ አእምሮአችን በላይኛው የአእምሮ ክፍላችን ከሚመላለሱት አሳቦች ይጠቅሙኛል ያላቸውን አሳቦች የሚያኖርበት ክፍል ነው፡፡ አንድ አሳብ ወደ ታችኛው የአእምሮ ክፍላችን ከመግባቱ በፊት በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ረዘም ያሉ ሂደቶችን ያሳልፋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች አንድን ሰው ከስህተት ጠብቀው በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ መልካም ሆኖ እንዲመላለስ ይረዱታል፡፡
ሰው ሁለት ወገን ከሆኑት የስሜት ሕዋሳቱ ከመንፈሳዊው ዓለምና ከግዙፉ ዓለም መረጃን ወደ ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባል፡፡ አእምሮም ለሁለቱ አካላት ማለትም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም መስለው ወደ ታዩት ይሳባል ወይም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እነርሱ ያዘነብላል፡፡ ይህ ዝንባሌ አጥብቆ መሻት(passion) ይባላል፡፡ አእምሮአችን በአንድ ነገር በመሳቡ ብቻ አሳቡን ወደ ተግባር ይመልሰዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ በካሜራ ምስልን እንደምናስቀር እንዲሁ ለበለጠ መረዳት የተሳበበትን ነገር ምስል በውስጡ ያስቀረዋል፡፡ ይህ ምሥልን በልቡና ውስጥ ማስቀመጥ “ምናብ”(imagination)ተብሎ እንጠራዋለን፡፡ በምናብ መልክ በአእምሮአችን ውስጥ ያስቀመጠውን አሳብ አእመሮአችን ደግሞ ደጋግሞ ጠቀሜታውንና ጉዳቱን እንዲሁም እውነተኝነቱን ይመረምራል፤ ያሰላስለዋል፡፡ በዚህም አንድ አቋምን ወደ መያዝ ይመጣል፡፡ ይህ ወደ አንዱ ማድላት አቋም(opinion)ይባላል፡፡ ከዚህም በኋላ አእምሮአችን አሳቡ ለሰብእናችን የሚጠቅም ሆኖ ሲያገኘው ሊተገብሮ ፍላጎት ያድርበታል፡፡ ይህ ፍላጎቱ ፈቃድ(will) ይባላል፡፡ በመጨረሻም ወደ ትግበራ ይመጣል፡፡
 አእምሮአችን ወደ ተግባር ሊመልሰው የመረጠውንም አሳብ ለአተገባበር  እንዲመች ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እግዚአብሔር ወደ ተግባር ለማምጣት በፈቀድነው ፈቃዳችን የሚፈርድብን ወይም የሚባርከን፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳኗ ታቦት መቅደስ ለመሥራት አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረም ወደ ተግባር ለመግባት ነቢዩ ናታንን አማከረው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳዊት ቤቱን እንዲሠራለት ፈቃዱ አልነበረም፤ ቢሆንም ቅን ስለሆነው አሳቡ እግዚአብሔር ባረከው እንዲህም አለው “እግዚአብሔር ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና፡፡ ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ፡፡ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል ዙፋኑን ለዘለዓለም አጸናለሁ”ብሎ ባረከው፡፡(2ሳሙ.7፡) ይህ ከእርሱ ወገን ክርስቶስ እንዲወለድ የሚያሳይ ዘለዓለማዊ በረከት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጁ ሰሎሞን ለዘለዓለም ነግሦ አላየነውምና፡፡ ለዘለዓለም በዳዊት ዙፋን ላይ የነገሠው ከዳዊት ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡(ሉቃ.1፡31) ክፉን አሳብ አስቦ እርሱን ለመተግበር ፈቃዱ ያለው ሰው ምንም እንኳ ድንጊቱን በተግባር አይፈጽመው እንጂ ልክ ድርጊቱን እንደፈጸመው ተደርጎ ይፈረድበታል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ አመነዝሮአል”ብሎ አስተማረን፡፡(ማቴ.5፡28)
ከላይ የዘረዘርናቸውን ሂደቶች የሚፈጸሙት በሕሊናችን መሣሪያነት ነው፡፡ ሕሊናችን ውስጥ እውነትን ከሐሰት የምንለይበት ሚዛን አለ፡፡ እርሱም እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በሕሊናችን ያኖረው ሕጉ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “… አሕዛብ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ … ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው ሕሊናቸው እርስ በእርስ ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግን ሥራ ያሳያሉ፡፡”(ሮሜ.2፡15) ብሎናል፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ወገን የስሜት ሕዋሳቶቻችን ወደ አእምሮአችን የሚገቡ አሳቦች ሁሉ እኛን በደለኞች አያሰኙንም፡፡ ነገር ግን እነርሱን በአእምሮአችን ውስጥ አልምተን ወደ መተግበር ፈቃድ ስንመጣ ፍርዱ የዛን ሰዓት በእኛ ላይ ይፈጸማል፡፡
 ዲያብሎስ ክፉ አሳቦችን ከእኛ የመነጩ አድርጎ በአእምሮአችን ውስጥ ሊዘራብን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ስጋት ሊፈጠርብን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የመነጨውን ክፉ አሳብ በጽኑ በመቃወም የእግዚአብሔር ወገን ከሆኑት ቅዱሳን መላእክት ጋር ልንወግን ይገባናል፡፡ ይህን ትምህርት የምንቋቸው ባሕታዊው ዮሐንስ የሚባለው ሶርያዊ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የጻፈልንን ድንቅ የሆነ ጽሑፍ በመመልከት ይሆናል ፡፡ እንዲህ ይለናል፡- በልቡናህ የሚመላለሱትን አሳቦችን በጥንቃቄ ተከታተላቸው፡፡ ክፉ አሳብ በልቡናህ ዘልቆ ቢገባ አትረበሽ ይህ አሳብ ከአእምሮህ የመነጨ እንዳልሆነ ከአእምሮህ በላይ ያለውን የሚውቅ ጌታህ ይረዳዋል፡፡ እርሱ የሚመለከተው ጥልቅ ከሆነው የአእምሮህ ክፍል በመነጨ ክፉ አሳብ ደስተኛ የሆንክ እንደሆነ ነው፡፡ የሚጠሉ ክፉ አሳቦች በላይኛው የአእምሮህ ክፍል ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡
ቢሆንም እግዚአብሔር የሚመረምረው የተጠሉ ክፉ አሳቦችን ለይቶ ማስወገድ የሚችለውን ጥልቁን የአእምሮአችንን ክፍል ነው፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል በሚመላለሱት በተጠሉ ክፉ አሳቦች የተነሣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አይፈርድብንም፡፡ ነገር ግን ከጥልቁ  የአእምሮአችን ክፍል የሚመነጩ የተጠሉ አሳቦች ስውር በሆኑ እጆቹ የማስወገድ ችሎታው ካለው  እእምሮ ክፍል የሚመነጩ ከሆኑ ግን ፍርድ ይጠብቀናል፡፡ ከጥልቁ የአእምሮችን ክፍል አመንጭተን ለምናመላልሳቸው ክፉ አሳቦች እግዚአብሔር በእኛ ላይ ከመፍረድ አይመለስም፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል የሚመላለሰው አሳብም ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል እንዳይገባ መከላከል ስንችል ወደ ውስጥ እንዲገባ ከፈቅድንለት እግዚአብሔር ፍርዱን ከዚህ የተነሣ ይሰጣል፡፡ እንዳውም ክፉ አሳብ በውስጥህ ጎጆውን ቢሠራና ብዙ ቀንም በአእምሮህ ቢሰነብት ከእዛም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ቢገባ ነገር ግን ውስጠኛው የአእምሮው ክፍል ያለማቋረጥ ላለመቀበል የሚሟገተውና ከአንተም ትእዛዝ የማይወጣ ከሆነ አትረበሽ ይህ ክፉ የሆነው አሳብ ተነቅሎ መወገዱ አይቀርም፡፡ በዚህም ከእግዚአበሔር ዘንድ የምትቀበለው አንዳች ፍርድ የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከጥልቁ አእምሮህ የመነጨው መልካሙ አስተሳሰብህ ከእግዚአብሔር አምላክህ ዘንድ ታላቅ ዋጋን ያሰጥሃል፡፡ ክፉ አስተሳሰብን የሚቃወም የለመደ አእምሮንም ገንዘብህ ታደርጋለህ፡፡”
እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ እንዴት እጹብና ድንቅ አድርጎ እንደፈጠረን እናስተውል፡፡ ነገሮችን በአግባቡ እንድናከናውን እግዚአብሔር በአእምሮአችን ውስጥ ልዩ የሆነ ሥርዓትን ዘርግቶልናል፡፡ በእነዚህም የአእምሮ ሥርዐታት አምላክንና ሰውን ሳንበድል ፍቅርን አንግሠናት በዚህ ዓለም በአግባቡ ያለስህተት መመላለስን በሚመጣው ዓለም ከቅዱሳን ጋር የርስቱ ወራሾች ለመሆን እንበቃለን፡፡ እግዚአብሔር ይህን በመረዳት ወደ ተግባር መልሰነው ለመመላለስ ማስተዋል ያድለን፡፡ 

No comments:

Post a Comment