Monday, February 6, 2012

ነነዌ እና ቅዱስ ኤፍሬም



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/05/2004
ከምንባብ በፊት የእኔ መልእክት
የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎችን ማስተዋወቄ ብዙዎቻችን ቅዱስ ኤፍሬምን ከውዳሴ ማርያም ውጪ በሌሎች ሥራዎቹ ስለማናቀው ነው፡፡ ስለዚህም ጥቂት የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎችን ለማቅረብ እየሞከርኩ እገኛለሁ፡፡ ወደ ፊትም እግዚአብሔር ቢፈቅድ የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎች ለማስተዋወቅ ምኞቴ ነው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በቅኔያዊ መዝሙራቱ የነቢዩ ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት መሆኑን በተለያየ መንገድ የተለያዩ አሳቦቹን ለመግለጽ ይጠቀምበታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን እነሆ ብያለሁ፡፡

v ሌጌዎን ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጠው በቁጥር 2000 የሚደርሱ የአጋንንት ሠራዊት ማለት ነው፡ እነዚህ አንድ ሰው ላይ ከትመው ይኖሩ ነበር፡፡ ጌታችንም እነዚህ አጋንንት ወደ ሰፈሩበት ሰው መንደር በመምጣት ይህን ሰው ከእነዚህ አጋንንት ቁራኛነት አላቆታል፡፡ ይህን ቅዱስ ኤፍሬም ከዮናስ ወደ ባሕር መጣል ጋር አቆራኝቶ “ክፉ የተባለው ሰይጣን እንዲህ አለ" እያለ በሰዎች መዳን የሰይጣንን ቁጭት ይገልጥልናል፡-

“ክፋት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ዛሬ ከቀደመው ይልቅ ታላቅ የሆነ ክፋትን ሠራህብኝ፡፡ እኛን ማዋረድህ ሳያንስህ በነቢዩ ዮናስ ላይ የፈጸምከውን በእኛ ላይ ልትደግም መጣህ፡፡ ሌጌዎንን ወደ ባሕር ጥልቅ በመጣልም ተበቀልከን፡፡ ዮናስ ከሦስት ቀን በኋላ ሕያው ሆኖ ከባሕር ውስጥ ቢወጣም ሌጌዎን ግን በባሕር ውስጥ ወዳለው ጥልቅ ሰጥሞ እንዲቀር አደረግህብን፡፡…


እኔን ድል የነሣኝ ይህ ሰው ማን ነው? የማንስ ልጅ ነው? ትልውዱስ ከማን ነው? የእያንዳንዱን ቤተሰብ ስም ዝርዝር የያዘው መዝገብ በእጄ ነው፡፡ እነሆ ከአዳም እስካሁን የተነሡትን ስም ዝርዝር መረመርኩ ሟች ከሆኑት መካከል ዘንግቼ ያልጻፍኩት አልነበረም፡፡ ቤተሰብ በቤተሰብ አንድ በአንድ በእጆቼ መዳፎች ላይ ስሞቻቸው ሰፍሮአል፡፡ ኢየሱስ ሆይ ባንተ ምክንያት ግን ድጋሚ የጻፍኳቸውን ሁሉ እመረምር ዘንድ ጀመረኩ፤ ነገር ግን ከአንተ በቀር ከእጆቼ ያመለጠ አንድም ሰው አላገኘሁም፡፡ እኔ የማልዋሸው አንድ ነገር ግን አለ፤ እርሱም ከሲኦል መዝገቤ ሳይሰፍሩ ያመለጡ ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱም ሄኖክና ኤልያስ ናቸው፤ እነርሱ ወደ እኔ አልመጡም፡፡ እነርሱን በዓለም ሁሉ አሰስኳቸው፡፡ ዮናስ ወደ ወረደበት ወደ ባሕሩ ጥልቅ በመውረድ ፈለግኋቸው ነገር ግን አላገኘኋቸውም፡፡ ምናልባት ወደ ገነት በመግባት ተሰውረውኝ ይሆናል አልኩኝ፡፡ ነገር ግን የገነት ደጅ የሚጠብቃት ብርቱ ኪሩብ በዚያ አለ፡፡ ምናልባትም ያዕቆብ ባያት መሠላል ወደ ሰማየ ሰማያት ወጥተው ይሆናል ብዬ ደመደምኩ፡፡ (ቅዱስ ኤፍሬም ያዕቆብ ያያትን መሰላል በቅድስት እናታችን ድንግል ማርያም ይመስላታል፡፡ በመስቀሉም ይመስላታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስም ይመስለዋል፡፡)   
ኢየሱስ ሆይ ባንተ ምክንያት ድሮ ያፈቅሩኝ የነበሩ ሁሉ ጠሉኝ፡፡ እነሆ አሁን ከማርያም በተወለድከውና የሰው ሁሉ መጠጊያ በሆንከው በአንተ ከግዛቴ ተሰደድኩ፡፡ አንተ የገነት መክፈቻ ቁልፍ አለህና አዳም ደስ አለው፡፡ ዮናስ ላይ እንደተነዋወጠቸው ባሕር እናቱ ላይ የተነዋወጠው ሄሮድስ ወዮለት፡፡ የቁጣ ማዕበላትን በማስነሣት የባሕሩ ጌታ የሆነውን ሊያሰጥም የሞከረው ሄሮድስ ወዮለት፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት
የእናትህ አምላክ የሆንክ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር እሰደድ ዘንድ ፍቀድ፡፡ ከአንተ ጋር የተሰደደኩ እንደሆነ በሁሉም ስፍራ ሕያው ሆኜ እኖራለሁ፡፡ ከአንተ ጋር የታሰረ እስረኛ እስረኛ አይባልም ምክንያቱም በአንተ ወደ ሰማየ ሰማያት ይነጠቃልና፡፡ ከአንተ ጋር በሞትህ ለተሳተፈ (ለተጠመቀ) ሰው ትንሣኤው ትሆነዋለህ፡፡      
v ከጥምቀት ጋር አቆራኝቶ ደግሞ ሲያስተምር እንዲህ ብሎ ያስተምራል፡-
የሸክላ እቃ ከሸክላ አፈር ይሠራል፤ ውበቱንም ከውኃ ያገኛል፤ ጥንካሬንም ከእሳት፡፡ ነገር ግን አንዴ ከእጅ ካመለጠ ተንኮታውኮቶ እንዳልነበረ ይሆናል፡፡ እርሱን ደግሞ መሥራት የማይቻል ነው፡፡ አንተ ግን በጸጋው የተሠራህ ምርጥ እቃ ነህ፡፡ እርሱን እንደሚገባ ሆነህ ጠብቀው፡፡ ምክንያቱም እርሱን ብታጣ ለሁለተኛ ጊዜ የሚታደስ አይደለምና፡፡ ዓሣ አንባሪው ከተፋው ነቢዩ ዮናስ ጋር አንተ በምን ትመሳሰላለህ? የዓሣ አንባሪው ጌታ በሆነው ትእዛዝ ዓሣ አንባሪው ነቢዩ ዮናስን እንደተፋው እንዲሁ ጠላትህ እርሱን በሚገዛው ጌታ ሥልጣን አንተን ከአጋዘበት ወህኒ ቤቱ ተፍቶሃል፡፡(በጥምቀት) ዮናስ ድጋሚ በዓሣ አንባሪው አለመዋጡ ለአንተ እንደ መስታወት ይሁንህ፡፡ ከእንግዲህ ድጋሚ በተቀናቃኝህ ሰይጣን እንዳትዋጥ ከዓሣ አንባሪው ሆድ ውስጥ የተተፋውን ነቢዩ ዮናስን ምሰለው፡፡ ከእንግዲህ በነቢዩ ዮናስ ላይ  የባሕሩ ውኆች እርሱን ወደጥልቅ ለማውረድ እንደተነዋወጡት ዓይነት መነዋወጥ በአንተ ላይ አይነዋወጡም፡፡ እርሱ ከአምላኩ በመኮብለሉ ምክንያት ወደ ወህኒቤት ተጣለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከወህኒቤት ወደ ጽኑ ወህኒቤት ጣለው፡፡ ወደ ባሕሩ ወህኒቤት ጣለው ከእርሱ ወደ ዓሣ አንባሪው ሆድ ውስጥ ጨመረው፡፡ ነገር ግን ጸጋው እርሱን ታደገችው እርሱዋ የእስር ቤቱን ደጅ ከፈተችለት ሰባኪውንም ከእስራቱ ፈታ ለቀቀችው፡፡   

1 comment: