Thursday, March 29, 2012

ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-(በቅዱስ ኤፍሬም)




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/07/2004
“ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-  እኔ የተሸከምኩት ሕፃን እርሱ እኔን የተሸከመኝ ነው ፡፡ እርሱ ክንፎቹን ዝቅ አድርጎ በእቅፎቹ ውስጥ አኖረኝ ፡፡ ከእርሱም ጋር ወደ ሰማየ ሰማያትም ተነጠቅኩ ፡፡ በዚያም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ ለልጄ እንዲሆን ቃል ኪዳን ተገባልኝ ፡፡
ልጄን መልአኩ ገብርኤል ጌታዬ ብሎ ሲጠራው ሰማሁ ፣ ሊቀ ካህኑና አገልጋዩም (ስምዖን አረጋዊ) እርሱን በእቅፉ ይዞ ስለእርሱ ትንቢትን ተናገረ ፡፡ ሰብአ ሰገል በፊቱ ወድቀው ሲሰግዱለት፤ ሄሮድስም ንግሥናዬን የሚቀማ ሌላ ንጉሥ ተነሣብኝ ብሎ ሲርድ ተመለከትኩ ፡፡
ሙሴን አገኘዋለሁ ብሎ የዕብራዊያንን ሕፃናት ያስፈጀ ሰይጣን እርሱን በመስቀሉ ጠርቆ የሚያስወግደውን ሕፃን ለመግደል ሽቶ ሄሮድስን መሳፈሪያው አድርጎ ሕፃናትን ለመግደል ተፋጠነ፡፡ ነገር ግን ጠላቶቹ የሆኑትን ሊያድናቸው የመጣው ጌታ ወደ ግብፅ ተሰደደ ፡፡
ቀዳማይቱ ሔዋን በድንግናዋ የእፍረት ልብስ ለበሰች፡፡ ያንተ እናት ግን በድንግልናዋ ለሁሉ የሚበቃውን የክብርን ልብስ ደረበች ፡፡ እርሱዋ ሁሉን የሚያለብሰውን ጌታ ውሱን የሆነውን ሥጋዋን አለበሰችው ፡፡
 
ስለዚህም ድንግል እንዲህ አለች፡- ከእንግዲህ ትውልዱ ሁሉ አምላኬን በሥጋ የፀነስኩትን በሕሊናዬም ያሳደርጉትን እኔን ብፅዕት ይሉኛል፡፡ የንጉሥ ልጅ የሆንከው ጌታ ሆይ! እኔ በአንተ ምክንያት የንጉሥ ቤተ መንግሥት ተሰኘኹ፡፡ በአንተም ምክንያት ቅድስተ ቅዱሳን ተባልኹኝ፡፡ …
ቀዳማይቱ ሔዋን በድንግልናዋ ወራት ለተረገመው እባብ ጎጆና ጉድጓድ ሆነችው፡፡ እርሱም ወደ እርሱዋ ገብቶ ማደሪያውን አደረገ ፡፡ የእርሱ ምክርም ወደ አፈርነቱዋ ትመለስ ዘንድ እንደ እንጀራ ሆናት፡፡ ጌታ ሆይ! በእኔ በእናትህ  ምክንያት ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ሕብስታችን ሆንኽ፡፡ አንተን ተመግበውም ሕያዋን ሆኑ፡፡ አንተ ለሰው ልጆች ሁሉ ዘመድና የክብር ልብሳቸው ሆንክ፡፡
… ኃጢአትን የፈጸመ ሰው ቢኖር እነሆ ይቅርታ የሚያደርግለት ጌታ ከዚህ አለ፡፡ ሰይጣን ያደረበት ሰው ቢኖር እነሆ ሰይጣንን አውጥቶ የሚሰደው ጌታ ከዚህ አለ፡፡ በሕመም ለተሰቃዩትም እነሆ ሕማማቸውን የሚፈውስ መድኅኒት ከዚህ አለ ፡፡(ቅዱስ ሥጋው ቅዱስ ደሙ)
ልጅ ያለው ሰው ቢኖር ልጁን ወደ ልጄ በማምጣት ለልጄ ለወዳጄ ወንድም ያድርገው፡፡ ሴት ልጅም ያለችው ወይም የደረሰች ልጃገረድ ያለችው ሰው ቢኖር ልጁን ወደ ልጄ በማምጣት ለልጄ ለወዳጄ እኅቱና ሙሽራ ያድርጋት፡፡ አገልጋይ ሠራተኛ ያለውም ቢኖር አገልጋዩን ነፃ ያውጣው ፤ ወደ ልጄም በማምጣት ለልጄ ለወዳጄ አገልጋዩ ያድርገው፡፡
ልጄ ሆይ ነጻ የወጡ ልጆች ለአንተ ባሮች ይሆኑ ዘንድ ቀንበርህን ተሸከሙ፡፡ ባሮችም ለጌቶቾቻቸው ጌታ ለሆነከው ለአንተና ከአንተ በታች ለሆኑት ጌቶች ተገዙ፡፡ ባሮች ለሁለት ጌቶች በመገዛታቸው ሁለት ዐይነት በረከቶችን ተቀበሉ፡፡
ነጻ የሆነች ሴት ለልጄ አገልጋይ  ትሁነው፡፡ በባርነት ያለች ሴት ባንተ መጽናናትን ታገኛለችና አንተን በማገልገሉዋ ነጻ ትወጣለች፡፡ በእቅፍህ ተሰውረው የተቀመጡ የሚበሉ ፍሬዎች  ያሉህ ጌታ ሆይ እርሱዋ አንተን በማፍቀሩዋ እና በማገልገሉዋ ምክንያት ትጠቀማለች፡፡
አንቺ ድንግል ሴት ሆይ እርሱ ሰውነትሽን ማደሪያው ያደረግ ዘንድ ወደ ልጄ ቅረቢ ፣ ንጽሕናሽን ያጎደፍሽውም ሴት ሆይ  አንቺን ይቀድስሽ ዘንድ ልጄን ወዳጄን ደጅ ጥኚው፤  እናንተ ቤተ ክርስቲያን የተሰኛችሁ ክርስቲያኖች ሆይ የፈጣሪ የባሕርይ ልጁ የሆነው እርሱ እናንተን ቀድሶአችሁ በቅድስናው ያስጌጣችሁ ዘንድ ልጄን ወዳጄን ናፍቁት ፡፡
 እርሱ ልጄ ማስተዋል የጎደላቸውን ከዋክብትን የሚያመልኩትን ሰብአ ሰገልን የእርሱ ይሆኑ ዘንድ ተቀበላቸው ፡፡ በአዳም መተላለፍ ምክንያት እሾኽና አሜካላ ስለበቀለባት ተጎሳቁላና አርጅታ የነበረችውን ምድር አደሳት፡፡
መዛግብቶቹን ሁሉ በጠቃሚ ስጦታዎች የሞላ ልጄ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ነው ፡፡ ስለዚህም አንተ እውር ሆይ ጭቃውን ወደ ዐይንነት ወደቀየረው ጌታ ቀርበህ የዐይን ኳስዎችህን አግኝተህ በብርሃን ተመላለስ ፡፡ …
  ሰውነታችሁ በለምጽ ደዌ የነደደባችሁ ኑ ወደ እርሱ በመቅረብ ያለድካም ንጹሐን ሁኑ ፡፡ እርሱ እንደ ኤልሳዕ እናንተን በውኃ ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያላችሁ እንድትጠመቁ በማድረግ ሥጋችሁን ብቻ የሚያነጻችሁ አይደለም ፡፡ እንደ ሌዋውያን ካህናት የተቀደሰ ውኃን በመርጨት ሥጋችሁን ብቻ የሚቀድስ አይደለም ፡፡ እንግዶችና መጻተኞች ራሳቸውን ከእርሱ ከባለመድኀኒቱ ዘንድ አስጠጉ ፡፡ የሥጋም የነፍስም ፈውስን ሰጣቸው ፡፡….
ጻድቅ የሆንኽ አንተ ይህን ሰውን ያልፈጠርከው ከሆነ እንዴት መፈወስ ይቻልህ ነበር ?... በዚህ ሰውነቱ ላይ ሕማምን በማምጣትና  መልሰህ ከሕመሙ በመፈወስህ አንተ በእውነት የፈጣሪ የባሕርይ ልጁ እንደሆንክ ታወቀ ፡፡ 
ምስጋና ይሁን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡   

No comments:

Post a Comment