ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
9/02/2007
ተወዳጆች ሆይ ዓይኖቻችሁ ከወዴት ናቸው?ዓይንን ስናነሣ ግን ሰው ሁለት የነፍሰ ዓይኖች እንዳሉት ቅዱስ ይስሐቅ ወይም ማር ይስሐቅ ይናገራል፡፡ አንዱዋ የነፍሳችን ዐይን ፍጥረትን አፍ እንደተገጠመ ጆሮም ከመስማት እንደተከለከለ ሀሳብም ጌታ ጸጥ እንዳሰኘው የባሕር ማዕበል ከምድራዊ ፍላጎቶች ጸጥ ብላ የፍጥረታዊውን ዓለም ጥንተ ተፈጥሮውን ተመልክታ ፈጣሪዋን ስታደንቅና ግሩም ግብሩ ለእግዚአብሔር ብላ ስታመሰግን ሌላኛይቱ ዓይን ደግሞ በርቀት(በረቂቅነት) በሁሉ ሙሉ ሆኖ የሚኖረውን አምላክ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን በእምነት ተመልክታ ብርሃናዊውን የመላእክትን ምግብ እርሱም ፍቅሩን እየተመገበች ቅዱስ ዳዊት ዓይኖቼ አንተን በማየት ፈዘዙ እንዳለው በትንግርትና በመደመም ስትመለከተው ትኖራለች፡፡ ያልታደለችው ዓይን ግን ራሱዋን ሳትመለከት የሰውን ጉድለት እያየች ለአእምሮ ሐሜትን እየመገበች ሰውነትን ስታሳድፍ ትኖራለች፡፡
ወገኖች እኛስ የትኛውን ዓይናችንን እየተጠቀምንበት ይሆን? አቤቱ አምላካችን እባክህን የምትሰማዋን፣ የምትዳስሰዋን፣ የምትረዳዋን ሰውነትን በብርሃን ፍቅርህ የምትመግበዋን የነፍሳችንን ዓይን አብራልን እኛም እንደ መላእክቱ ሳናቋርጥ ያለ እረፍት እናመስግንህና ሥጋዊ ዓይኖቻችን በነፍሳችን ዓይኖች በርተው የሰው ክፋቱን ሳይሆን መልካምነቱን ጭካኔውን ሳይሆን ደግነቱን ድከመቱን ሳይሆን ጥንካሬው እንድንመከትበት እርዳን፡፡ ይህም ለሰውነታችን ፍጹም እረፍትን ይሰጠናል፡፡ምክንያቱም በልቡናችን ውስጥ የክፋት ሃሳብ አይጸነስምና፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን “አንተ ግብዝ አስቀድመህ በዓይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ ያኔ የወንድምህን ጉድፍ መመልከት ትችላለህ ማለቱ፡፡ የጌታን ንጽጽርን ተመልከቱ ግንድ የተባለው እንደ ጉድፍ ቅንጣት የምታህለውን የሰውን ክፋትና ውድቀት ለማየት መጓጓት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው የሰውን እንደጉድፍ እጅግ ትንሽ የሆነችን ጉድለት ለማየት የሚተጋ ሰው ነው፡፡ አቤቱ አምላካችን ሆይ አንተ ሰውን የምትወድበትን ልብ ስጠን ያኔ ከወንድማችንና ከእኅታችን ውድቀት ይልቅ ትንሣኤአቸውን እንፈላልጋለን፡፡ ፍቅራችንም የእነርሱን ነውር ይከድነዋል፡፡
No comments:
Post a Comment