Tuesday, August 21, 2012

ጌታችን ሆይ ስማን!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/12/2004
ሞት ሞትን ስቦ እልቂትን እንዳያመጣብን አምላክ ሆይ ጠብቀን፡፡ ሥጋ ወዳዶች ለአንድ አጥንት እርሱም ሥጋ ላልተረፈው እርስ በእርሳቸው ተባልተው ይህን ምስኪን ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዳያባሉ ከላይ ከአርዓያም ያለህ አምላክ ሆይ ተቤዠን፡፡ ደምን ለተጠሙ ሞት የልብ ልብ ሰጥቶአቸው ሰይፋቸውን በልባችን ውስጥ እንዳይስጉ፣ የዘለዓለም ቤተመቅደስህ ላደረግኸው ለዚህ ሰውነትህ እና ለእናትህ ልጆች ጌታ ሆይ እራራልን፡፡ ሕዝቡን ከእልቂት ጠብቅ፤ ከውጭ እኛን ሊውጡ ከሚያገሡ ከውስጥ አጥንቶቻችንን ሊቆረጣጥሙ ካሴሩ ጌታ ሆይ ታደገን፡፡
 ለያዕቆብ በሴኬማውያን ፊት ሞገስና ፍርሃት እንደሆንከው ጌታ ሆይ ለእኛም እንዲሁ ሁነልን፡፡ እኛንና የዚህችን ሀገር ሕዝብ ከጥፋት አድን፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስማማ መሪን ስጠን፡፡ ጌታ ሆይ! ኃይላችን አንተ ነህና አንተን አርዓያ አድርገን እኛ በዚህች ምድር መጻተኞች የሆንና ሀገራችን በሰማይ ያደረግን እንደሆነ ተረድተው፣ ሞት ድል የሚነሣት የዚህች ዓለም ሰዎች በእኛ ላይ እንዳይከፉ ፈቃድህንና ፈቃዳችንን አስታውቃቸው፡፡ በላይ በአርያም ያለህ ፈጣሪያችን ሆይ! አሁን ንቃ መንጎችህንም ጠብቅ! ጊዜው ሥጋ የተጣለበት ጊዜ ነውና ሥጋ ናፋቂዎች እርስ በእርሳቸው ተባልተው ሲያበቁ በመርዘኛ ጥርሳቸው ጤናማውን ሕዝብ ነክሰው እንዳያሳብዱትና እርስ በእርሱ እንዳያነካክሱት መጠጊያችን ሆይ! ስምህን ታዛችን አድርገናልና በአንተ እንመካ እንጂ አንፈር፡፡ ክብር ላንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን!!!   

No comments:

Post a Comment