ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/12/2004
ክብር ለእርሱ ለወደደን ይሁንና ስለፍቅሩ የእኛን ሥጋ በመልበሱ ምክንያት እኛ የሰው ልጆች
የክብሩን ብርሃን ለማየትና ድምፁንም ለመስማት በቃን፡፡ ስለዚህም ከእናታችን በነሣው ሰውነት በኩል ግርማ መለኮቱን ለደቀመዛሙርቱ ባሳያቸው ጊዜ ሕሊናቸውን ስተው ወድቀው አልተጎዱም ነበር፡፡
ነገር ግን እያዩት እንቅልፍ ይዞአቸው ሄደ፡፡ በዚህም ስለምን ምክንያት በመለኮታዊው ግርማ ለእኛ እንዳልተገለጠልንና ስለምን ሥጋችንን
መልበስ እንዳስፈለገው አስተማረን፡፡
ሦስቱ ዋነኞቹ ሐዋርያት የእርሱ ብርሃነ መለኮቱን ሳይሆን ግርማውን ባዩ ጊዜ እንቅልፍ
የጣላቸውና ምን እንዳዩና ምን እንደሰሙ ያላስተዋሉ ከሆነ እንዲሁም ስምዖን ጴጥሮስ እንኳ የሚናገረውን ለይቶ እስከማያውቅ ድረስ ደርሶ መረዳታቸው የተወሰደ ከሆነ እንዴት
እኛ የእኛን ሥጋ ሳይለብስ መለኮትን ልናይ ከእርሱ በቀጥታ ልንማር ይቻለን ነበር? እኔስ ለእኛ በመለኮታዊው ብርሃን ተገለጠልን
ልል እንዴት ይቻለኝ ነበር? የእኛን ሥጋ ገንዘቡ ባያደርግ ኖሮ በምን መንገድ ራሱን ለእኛ ይገልጥልን ነበር? በእኛው አንደበት ባይናገረን ኖሮ እንዴት ከመለኮት በቀጥታ ልንማር ይቻለን
ነበር? በሚታይ አካል ለእኛ ባይገለጥልን ኖሮ እንዴት ተአምራቱን ሲፈጸም እርሱ እንደፈጸመው
ተረድተን ልናምነው ይቻለን ነበር?
ስለምን ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር መገለጥ አስፈለጋቸው? ለዚህ ጥያቄ መልሱ “የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል ብሎ”ሲጠይቃቸው “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎቹ ኤልያስ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው” ብለው በመመለሳቸው ነው፡፡ስለዚህም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር እንዲገለጡ በማድረግ እርሱ የነቢያት ጌታ መሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ከመሞቱ በፊት ገጽታውን ቀይሮ በግርማ መለኮቱ የመታየቱ ምክንያትም ከሞቱ በኋላ የለበሰውን ደካማ የሆነውን የሰውን ባሕርይ አክብሮ በመለኮታዊው ግርማ ወደ ላይ በክብር ከፍ ከፍ ማድረግ ለእርሱ እንደማይሳነው ሊያስገነዘባቸው ነው፡፡ እንዲሁም ሥጋችንን ገንዘቡ አድርጎ ካከበረው ከእርሱ ውጪ ማንም ሙታንን ሕያዋን አድርጎ ማስነሣት እንደማይቻለው ሊያሳውቃቸውም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህም ግርማ መለኮቱን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ገለጠላቸው፡፡
ስለምን ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር መገለጥ አስፈለጋቸው? ለዚህ ጥያቄ መልሱ “የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል ብሎ”ሲጠይቃቸው “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎቹ ኤልያስ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው” ብለው በመመለሳቸው ነው፡፡ስለዚህም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር እንዲገለጡ በማድረግ እርሱ የነቢያት ጌታ መሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ከመሞቱ በፊት ገጽታውን ቀይሮ በግርማ መለኮቱ የመታየቱ ምክንያትም ከሞቱ በኋላ የለበሰውን ደካማ የሆነውን የሰውን ባሕርይ አክብሮ በመለኮታዊው ግርማ ወደ ላይ በክብር ከፍ ከፍ ማድረግ ለእርሱ እንደማይሳነው ሊያስገነዘባቸው ነው፡፡ እንዲሁም ሥጋችንን ገንዘቡ አድርጎ ካከበረው ከእርሱ ውጪ ማንም ሙታንን ሕያዋን አድርጎ ማስነሣት እንደማይቻለው ሊያሳውቃቸውም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህም ግርማ መለኮቱን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ገለጠላቸው፡፡
ነገር ግን አይሁድ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ተቋዋሚ አድርገው ይቆጥሩት ነበር፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር ተቋዋሚ ከሆነ
እንዴት ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሊነጋገሩ ይመጡ ነበር? ስለዚህም
ከስቅለቱ በፊት ብቻውን ቅዱስ ከሆነው ከእርሱ ይነጋገሩ ዘንድ ወደ እርሱ ቀረቡ፡፡
ጌታችን ኤልያስን በኃይሉ ተጠቅሞ ከነበረበት ሥፍራ ወደ እርሱ ያቀረበው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር አብ
እቅፍ ኤልያስን ወደ እርሱ ያቀረበው ነውና፡፡ አስገድዶ ያቀረበው ቢሆን ኖሮ የእግዚአብሔር ተቃዋሚ በተባለ ነበር፡፡ ሙሴንም ያለ
እግዚአብሔር አብ ፈቃድ እንደሌባ ካለበት ቦታ በማሰስ ወደ ራሱ ነጥቆ ያቀረበው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳን ነፍሳት ካሉበት
በእግዚአብሔር ብቻ ከሚታወቅ ለሌሎች ከተሰወረ ሥፍራ ወጥቶ ነውና ወደ እርሱ የመጣው፡፡
ስለዚህም “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ወጣ፡፡”(ማር.9፡7)ለመሆኑ እስከ አሁን እግዚአብሔር
አብ የት ነበር? እርሱን ፈርቶ ተሸሽጎ ነውን? ለሰጠው ምስክርነት ቃል ሊያስረዳ በአካል ስለምን አልተገለጠም? ወይስ እርሱ ሳይሰማ
የእግዚአብሔር ተቃዋሚ የሆነው ድምፁን አሰምቶ ይሆን? ወይስ አንዳንዶች እንደሚሉት የእርሱ ተቃዋሚ ያለው በሦስተኛው ሰማይ ነው፤
እግዚአብሔር አብ ደግሞ ከሁለተኛይቱ ሰማይ ነው ያለው፡፡ እንዲያ ከሆነ እንዴት እርሱ ሳይሰማ የተቃዋሚው ድምፅ ሊሰማ ቻለ?(ቅዱስ
ኤፍሬም እንዲህ ማለቱ በዘመኑ የተነሡ ግኖስቲኮች እርስ በእርሳቸው የማይስማሙ ሁለት አምልክት አሉ ብለው ስለሚያስተምሩ ነበር፤ ክርስቶስን
ታላቁ አምላክ(ደጉ አምላክ) ሲሉ እግዚአብሔርን ደግሞ ታናሹ አምላክ( ክፉው አምላክም) ብለው ያምኑ ነበር፤ ሎቱ ስብሐት፡፡
ስለዚህም እነዚህን ለማሳፈር ሲል ቅዱስ ኤፍሬም ይህን መስቀለኛ ጥያቄን አመጣ፡፡ በዚህ ትምህርታቸው ከሚታወቁት ውስጥ የማኒ እምነት
አራማጆች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህች የምትታየው ዓለም የተፈጠረችው በታናሹ አምላክ ነው ብለው የሚያምኑ ናት ስለዚህም ምድርና
በምድር ያሉት ሥርዐቶች ሁሉ ርኩሳን ናቸው፤ በእነርሱ እምነት) ነገር ግን እግዚአብሔር አብ “እርሱን ስሙት በሕይወት ትኖራላችሁ” በሚለው
ቃሉ በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ መካከል ፍጹም የሆነ የፈቃድ አንድነት እንዳለ አሳየን፡፡
ነገር ግን እንዲህም በማለት
ስለልጁ በሚያስፈራ ጽምፀት ከተናገረ በኋላ ስለምን ዝምታን መረጠ? አንድ ቃልን ብቻ አውጥቶ ዝምታን መምረጡ ከልጁ ቃል ውጪ ሌላን
የሚሰማ ሁሉ ያለጥርጥር ይጠፋል ማለቱ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ወይም እርስ በእርሳቸው በመፈራረቅ አንድ ጊዜ አንዱ“አልፋና
ዖሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡”(ራእይ.22፡13) በማለት ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ “የምወደው ልጄ ይህ
ነው እርሱን ስሙት” (ማር.9፡7) በማለት እንደሚናገሩና በመለኮት
አንድ መሆናቸውን ለማስረዳት ነው፡፡
“ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ፡- የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ ብሎ አዘዛቸው፡፡”ስለምን
እንዲህ አላቸው? ምክንያቱም ልክ እንዳዩ ወዲያው ወደ ስብከት ቢወጡ ሌሎች “ኤልያስ ከየት እንደመጣ፣ የሙሴ መቃብር የት እንዳለ
በዐይናችሁ ተመልክታችኋልን? እስካሁን ድረስ መቃብሩ የት እንዳለ ያወቀ ሰው የለም፤ ለእናንተ ይህን ማወቅ በየት በኩል
አልፎ ተሰጣችሁ በማለት እንደሞኝ ቆጥረው ስለሚሳለቁባቸውና በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በእነርሱ ምክንያት ስለሚሰደብ
እንዲህ ከማለት እንዲቆጠቡ አዘዛቸው፡፡
ስለዚህም “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ ወርዶ ኃይልን እስክትቀበሉ ድረስ ቆዩ” አላቸው፡፡(የሐዋ.1፡4፣8) የዚያን ጊዜ ስለዚህ ነገር ስትነግሩዋቸው መጀመሪያ ላይ አይቀበሉዋችሁም ነገር ግን ሙት በማስነሣታችሁ ለእነርሱ ግራ መጋባትን ሲፈጥር ለእናንተ
ግን ክብር ይሆንላችኋል፡፡ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ” እስከዛው ጊዜ ድረስ ግን ቆዩ የማለቱ
ሌላኛው ምክንያት ሲኦል ሙርኮዎቹዋን ተገዳ እስክትለቅና በቅርብና አስቀድመው የሞቱ ቅዱሳን ከሞት ተነሥተው የንጉሥ ከተማ ወደ ሆነችው
ኢየሩሳሌም እስኪገቡ ድረስ ቆዩ ሲላቸው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አይሁድ እነርሱን በተመለከቱ ጊዜ ስለሙሴ ብትነግሩዋቸው እነዚህን
በሞቱ ያስነሣ ሙሴንም ሊያስነሣው ይችላል ብለው ሊያምኑዋችሁና “ተው ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደሆነ እንይ”(ማር15፡36) ያሉ
ሁሉ ቃላችሁን ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡
በእርሱ ቃል በሲኦል ጥልቅ ያሉ ነፍሳት ሁሉ በመውጣት
ሥጋን ለብሰዋት በመነሣታቸው ቅዱስ የሆነው እርሱ ባለበት ቦታ ሁሉ ቅዱሳን እንደሚሰባሰቡ ሁሉም ያምናሉ፡፡ ሙታን
ድምፁን ሰምተው ወደ እርሱ ከመጡ በሕይወት ያለው ኤልያስ ድምፁን ሰምቶ እንዴት ወደ እርሱ አይቀርብ? ስለዚህም ቅዱሳን ከመቃብር
በመነሣታቸው ምክንያት ስለሙሴና ስለኤልያስ የምትናገሩአቸውን ያምናሉ፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ
ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ ብሎ አዘዛቸው፡፡”….
እግዚአብሔር አምላክ ልቡናችንን ታቦር ተራራ አድርጎ በመለኮታዊ ብርሃኑ ልክ እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አእምሮአችንንና
ማደሪያ ቤተመቅደሱ የሆነውን ሰውነታችንን ያብራ፡፡ መለኮታዊው ብርሃኑም ለአእምሮአችን ማስተዋልን በመጨመር በጽድቅ እንድንመላለስ
ያብቃን ለዘለዓለሙ አሜን!!!
ይህን የቅዱስ ኤፍሬምን በደብረ ታቦር ላይ የጻፈውን ያነበበ በእውነት ተጠቀመ በጣም አስተማሪና ከዚህ በፊት ሰምቻቸው የማላቃቸውን እውነታዎች ነው አካቶ የያዘው፡፡
ReplyDelete