Saturday, August 18, 2012

ደብረ ታቦር በቅዱስ ኤፍሬም



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/12/2004
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት“እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያይ ድረስ ከዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ፡፡”(ማቴ.16፡28)የማለቱ ምክንያት በትንሣኤ እርሱን ለመቀበል በሕይወት የሚቆዩ እንዳሉ ሲያስረዳቸው ነው፡፡፡ ስለዚህም ጌታችን ሞትን ሳይቀምስ ከእርሱ ዘንድ የተነጠቀውን ኤልያስንና በእርሱ ሕያው የሆነውን ሙሴን ከመቃብር በማስነሣት ከሦስት ምስክሮች ጋር በደብረ ታቦር  ተራራ ላይ ግርማ መለኮቱን ገለጠልን፡፡ እነዚህ ሦስቱ አካላት ክርስቶስ ለሚመሠርታት መንግሥት(ቤተክርስቲያን) ምስክር የሚሆኑ  አዕማድ ናቸው፡፡(ቤተክርስቲያን ማለት በሥጋ ሞት የተለዩ የጻድቃን ነፍሳትና እንደ አልያስም ሞትን ያልቀመሱ ቅዱሳን እንዲሁም በምድር ሕያዋን ሆነን የምንኖር ክርስቲያኖች ኅብረት ማለት ናትና፡፡ ይህን  ምንም እንኳ በዐይናችን ለማየት ባንበቃም በእምነት ዐይኖቻችን  እንመለከተዋለን፡፡ በዚህም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ለሐዋርያት የተገለጠው መገለጥም ለዚህ እምነታችን  እውነተኛ መረጋገጫችን ነው፡፡)

እነሆ በዚህ ተራራ ቅዱስ ጴጥሮስ አላዋቂነቱ እጅግ ታላቅ የሆነን እውቀት ተናገረ፡፡ በዚህ ተራራ “እኔም አላውቀውም ነበር”(ዮሐ.1፡31) ተብሎ እንደተጻፈ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ሲመጣ መጥምቁ ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስ በገለጠለት እውቀት ጌታችንን እንዳወቀውና እንደለየው አስቀድሞ ግን እንዳላወቀው እንዲሁ ቅዱስ ጴጥሮስም ሙሴንና ኤልያስን ፈጽሞ ባያቃቸውም በመንፈስ ቅዱስ ለማወቅና ለመለየት እንደበቃ እንመለከታለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በስምዖን አንደበት ለእነርሱ ሙሴና ኤልያስ መሆናቸውን የገለጠላቸው ከሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞም ሁለቱን ነቢያት እንደማያውቃቸው ለእኛ ግልጥ ይሆንልናል፡፡(ስለዚህም ነው አላዋቂ ሆኖ ታላቅ የሆነ እውቀትን ተናገረ መባሉ) ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ ሦስት ዳሶችን እንሠራ” ባለው ንግግሩ ውስጥ  ሦስቱ አካላት አንድ ማኅበር እንደሆኑም እናስተውላለን፡፡
 ይህ መንፈስ ቅዱስ በገዛ ምርጫው ሐዋርያትን ማደሪያው ያደርጋቸው ዘንድ መምረጡን የሚያሳየን አይደለምን ? ወይም ጌታችን ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን እንዲሁም ጴጥሮስን ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ለብቻቸው ይዞ መውጣቱ ሙሴና አልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ያዩ ዘንድ አይደለምን? (ይህ በዚህ በሥጋዊ ዐይናችን አይገለጥ እንጂ የመንፈሱ ማደሪያ በሆንን ጊዜ ከእነርሱ ጋር ማኅበርተኞች እንደሆንን እንረዳለን ነው፡፡)
ጌታችንም ሞትን ከመቀበሉ በፊት በዚህ ተራራ ላይ “ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ”(ሉቃ.9፡29) እንዲል በአንድም ወይም በሌላ መንገድ ለእነርሱ ተቀይሮ መታየቱን እናስተውላለን፡፡ እንዲያም ሆነ እንዲህ እርሱ ማን እንደሆነ በእነርሱ በፊታቸው ተቀይሮ ታያቸው፡፡ እንዲህም ማድረጉ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት በአዲስ ክብር ለእነርሱ ዳግም በታያቸው ጊዜ እርሱን እንዳይጠራጠሩት ለማዘጋጀት ነው፡፡ ይህ ከትንሣኤ በኋላ በመንግሥቱ የሚገለጥበት ክብር ስለምን በቃል ሊገልጥላቸው አልፈለገም? ስለምን ግርማ መለኮቱን ለእነርሱ መገለጥ አስፈለገው? ምክንያቱም በቃል ቢነግራቸው ኖሮ ባልተረዱት ነበርና ከዚህም በተጨማሪ እነርሱም በትንሣኤ ልክ እንደእርሱ እንደሚቀየሩም ሊያሳቸያውም በመፈለጉ እንዲህ አደረገ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ሁለት እውነታዎችን በትንሣኤው እንዲፈጸሙ ተረድተው በእምነት እንዲቀበሉ ሲል ጌታችን እነርሱን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ አንደኛው በትንሣኤው ለእነርሱ በልዩ መለኮታዊ ግርማው እንደሚገለጥላቸው ሲሆን ሌላኛው እነርሱም በትንሣኤ እርሱን መስለው እንደሚነሡ ሲያስተምራቸው ናቸው፡፡ ይህም እርሱ የሕያዋንም የሙታንም አምላክ እንደመሆኑ መጠን እንደ ሙሴ በመቃብር ያሉ እንደሚነሡ፣ ሕያዋን የሆኑት ደግሞ እርሱን ለመቀበል በአየር እንደሚነጠቁ ያሳየናል፡፡
ስለዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ በተራራው ላይ ከጌታ ጋር ሙሴና አልያስ ሲነጋገሩ በተመለከተ ሰዓት “ጌታ ሆይ ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ፡፡”(ማቴ.17፡4) ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ማለቱ ግን ይህ ተራራ ከጻፎችን ፈሪሳውያን ሴራ የሚያመልጡበት ተራራ መስሎት እንዲህ በደስታ ተውጦ ተናገረ፡፡ በዚህም ሆኖ የመንግሥተ ሰማያትን አየር በማሻተቱ ነፍሱ በደስታ ተሞላች፡፡ እንዲሁም በዚህ ቦታ ጌታችን በአይሁድ የሚቀበለውን ውርደት ሳይሆን ክብሩን ስላየና ከሙሴና ከኤልያስ ጋር አብሮ በመጓደዱ እንዲሁም ከቀያፋና ከሄሮድስ ያመለጡ መስሎ ስለታየው ደስ አለው፡፡ ስለዚህም ቀድሞ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ ይህ ከቶ አይድረስብህ” በማለት በየዋህነት ጌታችንን በአይሁድ መከራን ከመቀበል እንደተከላከለው በዚህም ተራራም “በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ፡፡” ስለዚህም ወንጌላዊው “እጅግ ስለፈራ የሚናገረውን አያቅም ነበር አለን”(ማር.9፡6)ምክንያቱም ጌታችንን መድኀኒታችንን ሊሰቀሉት ይችላሉ ብሎ በልቡናው ፈርቶአልና፡፡ 
ወይም እነዚህ ሦስቱ ዳሶች ጌታችን “የአመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘለዓለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ፡፡”(ሉቃ.16፡9)ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ምድር ላሉ ቤቶች ሳይሆን በሚመጣው ዓለም ስላሉ ቤቶች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ “የሚለውን አያቅም ነበር”(ሉቃ.9፡33) ሲልም ጌታችንን ከሙሴና ከኤልያስ ጋር አስተካክሎ በዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ በማለቱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር አብ ድምፅ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ ወጣ፡፡(ማቴ.17፡5) ይቀጥላል…. ሰውነታቸውን የመለኮት ማደሪያ ያደርጉ ዘንድ በጥምቀት ክርስቲያኖች ለሆኑት ሁሉ መልካም በዓል እንዲሆንላቸው ምኞቴ ነው፡፡          

1 comment:

  1. Amen lehulachin tiru asitemar yehon suhufi new wenidima ketayunim begugut etbikalen kale hiyiwet yasemah bedima besega yitebikih.

    ReplyDelete