Thursday, August 16, 2012

አሁን ደግሞ ሹመቱ የካህናት ተራ ቢሆን!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/12/2004
ጭንቅ የሆነው የቤተ ክርስቲያን የስደት ዘመን በንጉሥ ቆስጠንጥኖስ እስካበቃበት እስከ3ኛው ክ/ዘመን ድረስ ክርስቲያኖች ፍጹም በሆነ የቅድስና ሕይወት ውስጥ ይመላለሱ ነበር፡፡ በውጭ በአላውያን ነገሥታትና በጣዖት አምልኮ በታወሩ ሕዝቦች እንዲሁም በአይሁድ የሚቀበሉት መከራ እርስ በእርስ ያላቸው ፍቅር እንዲጠብቅና እንዲተዛዘኑ እንጂ ከቅድስና ሕይወታቸው እንዲወጡ አላደረጋቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ከ3ኛ ክ/ ዘመን ጀምሮ በንጉሥ ቆስጠንጥኖስ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት ስትሆንና ነገሥታት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ሲገቡ ፍጹም የተባለው ክርስቲያናዊ ሥነምግባር እየጎደፈ ሕዝቡም መረን እየለቀቀ ውሻ ወደ ትፋቱ እንዲመለስ ብዙዎች ወደ ቀድሞ ግብራቸው ተመለሱ፡፡
በዚህን ጊዜ ነው ክርስትናዊ ሕይወታቸውን ላለማጣት ሲሉ ንጹሐን ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ በቤታቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ በመንደር አንድነት በመሰባሰብ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ ከሰው በመራቅ በዋሻ ውስጥ የብሕትውናን ሕይወት የጀመሩት፡፡ እነዚህ ወገኖች ልክ እንደሎጥ ሰውነታቸውን ከኃጢአት ለመጠበቅና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ክርስቶስ በመረቀልን ጎዳና እርሱን ወደመምሰል ሊያድጉ ፈቅደው ይህን ሕይወት ጀመሩ፡፡ ,እንዲህ የተጀመረው የብሕትውና ሕይወት በ4ኛ ክ/ዘመን ቅርጽና መልክ ይዞ በእነ እንጦስና መቃርስ ከሰው ተነጥሎ በአንድነት ወደሚኖርበት ገዳማዊ ሕይወት ተለወጠ፡፡ እስከዚህ ዘመን ድረስ ግን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት የሚሾሙት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው ከክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የተገኙ፣ የራሳቸውን ትንሿን ቤተክርስቲያን(ቤተሰብ) በአግባቡና በሥርዐቱ የሚመሩ፣ ነውርና ነቀፋ የሌለባቸው፣ በመንፈሳዊ እውቀታቸው የበሰሉ፣ ራሳቸውን ገዝተው የሚኖሩ ልከኞች፣ ለሰው ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ያላቸው፣ በአንዲት ሚስት ተወስነው የሚኖሩ ጳጳሳት ነበሩ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም ምንም እንኳ የድንግልና ሕይወትን መርጦ የሚኖር ቢሆንም በቅዱስ ጋብቻ ተወስኖ ያለና ቤተ ክርስቲያንን በቤቱ ባለች ቤተ ክርስቲያን ያወቃት ሰው ቤተ ክርስቲያንን ቢመራት መልካም ሆኖ ስላገኘው ይህን ሥርዐት ጻፈልን፡፡(1ጢሞ.3፡1-16) ነገር ግን በዘመኑ ሥልጣኑን ይዘው የነበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕዝቡን መምራት ሲሳናቸውና በኃጢአት አረቋ ውስጥ ሲዘፈቁ፣ የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ራሳቸውን በድንግልና ሕይወት የወሰኑ፣ በፍጹም ልባቸው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ፤ በመንፈሳዊ እውቀታቸው የበሰሉ፣ ማኅበረሰቡን በቅርበት የሚያውቁትና ነውርና ነቀፋ የሌለባቸው ደናግላን ላይ ዐይኖቻቸው ያረፈው፡፡

 በዚህን ጊዜ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ቤተ ክርስቲያንን ይመሯት ዘንድ ወደ ጵጵስና አመጧቸው፡፡ በእርግጥም እነዚህ ደናግላን ጳጳሳት በጊዜው ታላላቅ የሆኑ ተግባራትን በመፈጸማቸው የክርስቲያኑን ማኅበረሰብ በመንፈሳዊውም በማበኅራዊውም ሕይወቱ ታላላቅ የሆኑ ለውጦችን እንዲያመጣ አድርገውት ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ደናግላን ጳጳሳት ራሳቸውን ልክ እንደ ጌታቸው ስለመንጎቻቸው ጽኑ የሆነ መከራን የተቀበሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ሊከፋፍሉ የተነሡትን ግኖስቲኮችንና አንዳንድ ፈላስፎችን በትምህርታቸውና በጽሑፋቸው ያሳፈሩ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥና ከውጪ ጠላቶቹዋ ያጸዷት፣ የእግዚአብሔርን መንጋ በመንፈሳዊ ሕይወት ያበረቱ፣ በበጎም ሥራ ያጸኑ ነበሩ፡፡ ከዚህ የተነሣ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ በእነርሱ ትጋትና የቅድስና ሕይወት በብዙ ስለተጠቀመ ደናግላን(ያላገቡ)ቤተ ክርስቲያንን ይመሩዋትና ያስተዳደሩዋት ዘንድ ሥርዐት ሠራ፡፡ የእኛዋም ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ለመሆን ለሚታጩ ባወጣችው መሥፈርት ላይ “ያገባ የአንድ ሚስት ባል የሆነ” የሚል መመዘኛ ሰፍሮ አይገኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ በድንግልና ሕይወት ያለ …እና ሌሎችም ላገቡት ሳይሆን ላላገቡት የወጡ መሥፈርቶች ብቻ ናቸው ሠፍረው የሚገኙት፡፡
ቢሆንም ይህም መንገድ ብዙም ሳይቆይ ከማኅበረሰቡ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውና በቤታቸው ወይም በመንደር ወይም በየዋሻው የብሕትውናን ሕይወት ይመሩ የነበሩ ቅኖቹ ደናግላን ጳጳሳት በተመላለሱበት ሕይወት ባልሄዱ፣ ለመንጋው ግድ በሌላቸው፣ ዝቅ ብለው ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ የት ነህ በማይሉ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ትውውቅ በሌላቸው፣ ለመንጋው ሳይሆን ነፍጥ አንግቶ ሀገሪቱን ለሚመራው መንግሥት ቀኝ እጅ ሆነው በሚያገለግሉ ደናግላን ጳጳሳት ተተካ፡፡
የቀደሙት ቅዱሳን ጳጳሳት በመንፈሳዊው እውቀታቸው እጅግ የበሰሉ ስለነበሩ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው መረዳት የክርስቲያኑን ማኅበረሰብ ሥሪትን ስለሚያቁ ለመንጋቸው የሚገባውን ሲከውኑ ነበር፡፡ እነርሱ ተከትለው ሥልጣኑን የተረከቡት አብዛኞቹ ጳጳሳት ግን የእነርሱን ተቃራኒ ሲፈጽሙ የነበሩና ያሉ ሆነው ተገኙ፡፡ 
 በመንፈሳዊ ብስለትና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ካልሆነ በቀር በድንግልና ሕይወት የሚመላለስ ሰው በጋብቻ ከማኅበረሰቡ ጋር ስላልተዋሐደና መንጋውን በቅርበት ስለማያውቀው ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ እንደሚጠበቅበት በአግባቡ ሊመራው አይችልም፡፡ ነገር ግን በጋብቻ ከማኅበረሰቡ ጋር አጥንትና ሥጋ ሆኖ ለተቆራኘው ለእውነተኛው ካህን ግን የማኅበረሰቡ ሕመም ሕመሙ፤ ደስታው ደስታው፤ ስኬቱ ስኬቱ፤ ውድቀቱ ውድቀቱ፤ ትንሣኤው ትንሣኤው ስለሆነ በመንፈሳዊ እውቀት ካልበሰለው ድንግል ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ብቁ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማለት መንፈሳዊም ሥጋዊም መግቦት የሚያስፈልጋቸው በአካልም በመንፈስም ልጆች የሆኑ ያሉባት፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋዊያን አንድነት የሚገኙበት የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ እንዲህ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ መረዳቱ እጅግ የበሰለ ድንግል ካልሆነ ወይም ከማኅበረሰቡ ጋር በጋብቻ የተቆራኘ ካህን ካልሆነ በቀር ማን ሊመራት ይችላል? 
እንዲህ የሆነችዋን ቤተ ክርስቲያን ስለቤተሳባዊ ሕይወት የማያውቅ ወይም በመንፈሳዊ እውቀቱ ያልበሰለና የክርስቶስን አርዓያ ያልተከተለ ድንግል እንዴት ሊመራትና ሊያስተዳድራት ይችላል? ስለዚህም እንዲህ ያሉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን ቢመሩዋት ይበልጥ መንጋውን በተኩሎች እንዲነጠቅ ከማድረግ የዘለለ የሚፈይዱት አንዳች ፋይዳ የለምና እንደኔ እንደኔ  አሁን ቤተ ክርስቲያንን የመምራት ተራው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “የማይነቀፍ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልከኛ፣ ራሱን የሚገዛ፣እንደሚገባው የሚሠራ፣ አንግዳ ተቀባይ፣ ለማስተማር የሚበቃ፣ የማይሰክር፣ የማይጨቃጨቅ፣ ነገር ግን ገር የሆነ፣ የማይከራከር፣ ገንዘብን የማይወድ፣ልጆቹን በጭምትነት እየገዛ የሚመራ ነገር ግን አዲስ ክርስቲያን ያልሆነ ካህን ቢሆንና እርሱ ቢመራን መልካም ነው እላለሁ፡፡(1ጢሞ.3፡1-16፤ ቲቶ.1፡7-10)ቅዱስ ጳውሎስም ያለምክንያት አይደለም እንዲህ ብሎ ሥርዐት ማውጣቱ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚበጅ አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነው እንጂ፡፡ ስለሆነም በዚህ መመዘኛ ብቁ የሆነ ካህን ተገኝቶ የቤተ ክርስቲያንን አመራር ቢይዝ ምናልባት የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ በመንፈሳዊም ሆነ በምድራዊው ሕይወቱ ታላቅ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡  እግዚአብሔር አምላክ እርሱ ያወቀውን ለእኛ የሚበጀውን ሰው መሪ አድርጎ ይሹምልን፤ አሜን ይሁን ይደረግልን፡፡               

3 comments:

  1. dear shimles bekedem endawetahew aynet aweyay tshufochen bitaweta hassaben lemestet zigju negh beziwum betekrstyanachin weste yaldaberwen bemerja bewyiyet negrochen yalmftat bahil enkerfalen kale hiwot yasemalgh

    ReplyDelete
  2. thank you a lot my dear brother, I will try,but you can rise any discussion topic, and I will write on it or you write on it then we will discuss. God be with you.

    ReplyDelete