Sunday, February 10, 2019

እግዚአብሔርን ማወቅ ራስን ለማወቅ


በመ/ር ሽመልስ መርጊያ

ቀን 03/06/2011 ዓ.ም

እውነቱን እንናገር ካልን ሰው ራሱን ወደ ማወቅ የሚደርሰው እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ሲደርስ ብቻ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ሳያውቅ የሚኖረው ኑሮ ከእንስሳት በእጅጉ በተዋረደና ባለማስተዋል እንደ ሰይጣን ፈቃድና ሐሳብ በሆነ አኗኗር ውስጥ  ነው፡፡ ሰው ንጹሕ የሆነውን ባሕርይውን ተረድቶ ክፉ ፈቃዱን ገቶ በመልካም ሰብእና መመላለስ የሚችለው አስቀድሞ እግዚብአብሔርን ሲያውቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር እየተማረ ሲያድግ ራሱን ወደ ማወቅ ይደርሳል፡፡ እግዚአብሔርን ሳያወቁ ራስን ማወቅ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሰው በተፈጥሮው እግዚአብሔርን እንዲመስል ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነውና፡፡ ስለዚህ ሰው እግዚአብሔርን ሲያውቅ ንጹሕ የሆነውን እግዚአብሔርን የሚመስልበትን ባሕርይውን ወደ ማወቅ በእርሱም ወደ መመላለስ ይመጣል፡፡ እግዚአብሔርን በማወቅ ውስጥ ሆነን ራሳችንን ወደ ማወቅ ስንመጣ በውስጥም በውጪም ሥራ የሚሠራውን እግዚአብሔርንና ፈቃዱን እንረዳለን፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመሻት ራስን ለማወቅ ፈቃዱ እንደሌለን ማሳያ ነው፡፡  በራስ ጥረት ራስን ለማወቅ የሚደረግ ድካም  እንደው ደንዝዞ በስሜት መንሆለል፤ በሐሳብ መጋለብ፤ በምናብ መንጎድ ቢሆን እንጂ የትም አያደርሰንም፡፡ ይህም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደመዳከር ነው፡፡

እግዚአብሔር ሥራዎቹን በምክንያትና በማስተዋል እንዲሁም በጥበብ የሠራና የሚሠራ አምላክ ነው፡፡ በተለይ የሰው ልጆችንና መላእክትን ያለምክንያት አልፈጠራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እኛን ሰዎችን ረቂቅ ከሆነችው ነፍሳችን እስከ ግዙፏ አካላችን ድረስ በምክንያት ፈጥሮናል፡፡ ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን በመሆን የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳት የሆነው እኛ አንዱን የክርስቶስን አካል ለማገልግል ሌሊትና ቀን የምንፈጽመው የየራሳችን ግብር እንዳለን እንዲሁ ነፍሳችንና እያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል  አንድ አካል የሆነውን ሰብእናችንን እግዚአብሔርን እንዲመስል ሌሊትና ቀን የሚተጉ ሊሆኑ ይገባዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶታችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ”(ሮሜ.6፡13) በማለት አስተማረን፡፡
ቢሆንም ግን እግዚአብሔር አምላክን በራሱ ፈቃድና ጊዜ እንጂ በራሳችን ጥረት የምናውቀው አይደለም፡፡ እርሱን ማወቅ የምንችለው እርሱ ራሱን በገለጠልን መጠን ነው እንጂ በራሳችን ምርምርና ጥናት አይደለም፡፡ እርሱ በባሕርይው የማይመረመር ነውና፡፡ ነገር ግን እርሱን ለማወቅ መሻታችንን በእጅጉ ይሻዋል፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ነው፡፡  አንድ ሰው እርሱን መረዳት የሚችለው እኔ ማን ነኝ? ማን ፈጠረኝ? ለምን ፈጠረኝ? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ከጌታችን አግኝቶ በእርሱ እንደሚገባ ሲመላለስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እግዚአብሔር ራሱን በተለያየ መንገድ ይገልጥልናል እርሱንም እናውቀዋለን፡፡
እግዚአብሔር የሰው ልጆች የማይካፈሏቸው ለእርሱ ብቻ የሆኑ ባሕርያትና የሰው ልጆች የሚካፈሉዋቸው ባሕርያት አሉት፡፡ እግዚአብሔር ለሀልዎቱ ጥንትና ፍጻሜ የለውም፤ ሁሉን ቻይ ነው፤ ራሱን በራሱ የሚያኖር ነው፣ ሁሉን አዋቂ ነው፣ እነዚህ የእግዚአብሔር ባሕርያት ሰውና መላእክት የማይጋሩአቸው የእግዚአብሔር ብቻ የሆኑ ባሕርያት ናቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነውና እነዚህ ሁሉ ገንዘቡ ናቸው፡፡ ስለዚህም ስለ እርሱ በምንናገራቸው ንግግሮች ሁሉ እነዚህን ነገሮች ልብ ማለት ይገባናል፡፡ አንዳንዶች ሰው ሆኖ በሰዎች መካከል በመመላለሱ ምክንያት እንደ አይሁድ ከፍጡር ወገን ቆጥረውታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከድንግል እናታችን የተካፈለውን ሰብእናችንን ብቻ በመመልከት አምላክነቱን  ለብቻው ሰውነቱን ለብቻው በማቆም አንዱን ፍጡር ሌላውን ፈጣሪ በማድረግ ሁለት አካል በመስጠት ልዩ ትምህርትን ሲያስተምሩ እናገኛቸዋለን፡፡ ክርስቶስን ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እርሱ ለሰማያዊው አባቱም ለድንግል እናቱም አንድያ ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አብ ልጅ ለብቻው የድንግል ማርያም ልጅ ለብቻው አይደለም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ ጌታችን በድንግል እናታችን በነሣው ሰውነቱ የእግዚአብሔር ልጅ ባልተባለ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በፊት በሰው ምሳሌና መልክ በመላእክት ይመለክ የነበረው ጌታችን አሁን ከእኛ በነሣው ሰውነት በመላእክት ዘንድ ይመለካል እንዲህም በመሆኑ “በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ”(ዕብ.1፡6) ተብሎ ተጻፈልን፡፡ አሁን በሰማያት ያሉ መላእክት የእኛን ሰውነት ገንዘቡ ባደረገው በጌታችን ፊት ወድቀው ይሰግዱለታል፡፡ ይህም ይበልጥ እርሱን እንድንመስል ፈቃዱ መሆኑን የሚያስገንዘበን ነው፡፡ እኛ ክርስቶስን ከመሰልን እግዚአብሔርን አንመስለዋለን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነውና፡፡ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ግን እርሱን የምንመስለው በሁሉ ሳይሆን እርሱን በምንመስለበት ባሕርያት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ 
እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነው፣ እግዚአብሔር ርኅሩኅ ነው፣ ትሑት ነው፤ ቅዱስ እና ነገሮችን በምክንያት የሚያደርግ አምላክ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት በሰዎችና በመላእክት ውስጥም የሚታዩ ባሕርያት ናቸው፡፡ ከመላእክት የበለጠ ግን ሰዎች እግዚአብሔርን ይመስሉታል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከምንም አምጥቶ ፈጠራቸው፡፡ ለሰው እንዲህ ማድረግ አይቻለውም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሌሎች ፍጥረታትን በምክንያትና በማስተዋል ፈጠረ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ለሰው ልጅ የተሰጠ ነው፡፡ የሰው ልጅ በአፈር ውስጥ ተሰውረው ያሉትን ማዕድናት ለይቶ በማውጣት በምክንያትና በማስተዋል እንዲሁም በጥበብ ለኑሮው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ሠርቶን ይጠቀምባቸዋል፡፡ በዚህም ከመላእክት በተለየ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ይመሰለዋል፡፡ እንዲሁም ይክበር ይመስገንና ጌታችን ሰው በመሆን በሚዳሰስ አካል በመገለጡ ባሕርያችን በመላእክት ዘንድ ወደ መመለክ መጥቶአል፡፡ በዚህ በሚዳሰሰውና በሚታየው አካላችን ከመላእክት ይልቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን እንድንመስል አብቅቶናል፡፡
እነዚህ ብቻ ግን አይደሉም “ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር” በሚለው ቃሉ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ከጥንት ከዘለዓለም የራሱ መልክና ምሳሌ አለው፡፡ በዚህ መልክና ምሳሌ ለመላእክት ተገልጦ ይመለካል፡፡ ይህን አስመልክቶ ነቢዩ “በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።… የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።” (ሕዝ.1፡26-28) ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ ይህም በግዘፍ የምትታየው ሰውነታችን አምሳል ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን በሁለንተናዊ ማንነታችን የምንመስል ከሆን ጌታችን “አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን እሹ” ብሎ እንዳስተማረን ሙሉ ለሙሉ ራሳችንን ለእርሱ በመስጠት እርሱን ለማወቅና ለመምሰል ልንተጋ ይገባናል፡፡ ያኔ ራሳችንን እናውቃለን በማስተዋል ለመመላለስም እንበቃለን፡፡  
አንድ ሰው ጤናማ ወደ ሆነው ራስን መውደድ ሲመጣ ለራሱ እነዚህን ጥያቄዎች ይጠይቃል እንዲህ ይላል፡- እኔ ማን ነኝ? ወደዚህ ዓለም በፈቃዴ አልመጣሁም ታዲያ ከእናቴ ማኅፀን ያበጀኝ እርሱ ማን ነው? ራሴ በገዛ ስልጣኔ እያኖርኩ ነውን? ነገ በእርግጠኛ የእኔ ናት ብዬ መናገር ይቻለኛልን? ታዲያ ማን ነው የሚያኖረኝ? እርሱ ጠንቅቆ የሚያውቀኝ እኔ ግን የማላውቀው እርሱ ማን ነው? ይላል፡፡ ነገር ግን ይህን ጥያቄ ሊመልስልን የሚችለው ከፍጡር ወገን አንዳችም እንደሌለ ሕሊናው ይነግረዋል፡፡
አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን ጥያቄ ሊመልሱ ይቻላቸዋል ብንል እንኳ አባት አይደለም ስለእኛ አፈጣጠር ሊያውቅ በእናታችን ማኅፀን ምን እየተከናወነ እንደነበረ እንኳ አንዳች የሚያውቀው ነገር የለውም፡፡ እናታችንም እንዲሁ ናት፤ ከአባታችን ግን ትሻላለች፡፡ እናታችን በማኅፀኗ ውስጥ እለቱን የሚከወነውን ዘግይታ እንጂ ወዲያው አታውቀውም፡፡ ታዲያ ይህን ባላወቀችበት እንዴት እርሷ ስለአፈጣጠራችን ጠንቅቃ ልታውቅ ይቻላታል? በዚህም ወላጆቻችን እኛን ልጆቻቸውን ፈጥረው ወደዚህ ዓለም እንዳላመጡን ነገር ግን በርቀት የሚኖር እርሱ ሁሉን ማድረግ የማይሳነው አካል እንዳለ እርሱም እግዚአብሔር እንደሆነ መስክሮች ናቸው፡፡ በተለይ እናታችን ለዚህ እውነተኛ ምስክር ናት፡፡ ለእርሷ እግዚአብሔር ማለት ሁሉን ቻይ የሆነ በባሕርይው የማይመረመር መንፈስ የሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ልጇን በማኅፀኗ ሢሠራው አታየውም ግን በውስጧ ጽንሱ ሲያደግና ሲላወስ ይታወቃታል፡፡  በዚህም ግዙፉንና ረቂቁን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረው ይህ በማኅፀኗ ያለአንዳች እርዳታ ልጅን ፈጥሮ የሰጣት እንደሆነ ትረዳለች፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን”(ዕብ.11፡3) እንዳለው በእኛ ዘንድ የሚታዩና የማይታዩ በራሳቸው ላይ እንኳ ስልጣን የሌላቸው ፍጥረታት(ይህ በእኛ ዘንድ እንጂ የማይታዩ የምንላቸው ፍጥረታት በእርሱ የሚታዩና ግዙፋን ናቸው)  መንፈስ በሆነውና ከማኅፀን ባበጀን  በባሕርይው ሁሉን ቻይ በሆነ በእርሱ እንደተፈጠሩ እናት ትረዳለች፡፡ ያንንም አምላክ አጥብቃ ትሻዋለች፡፡ አባትም በባለቤቱ በተከወነው ነገር በእጅጉ ከመደነቅና ከመገረም ባለፈ ምንም ሊል አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህን ሥራውን ተመልክቶ ግሩምና ድንቅ የሆነውን በሁሉ ላይ ሰልጥኖ የሚኖረውን ፈጣሪ ይሻል፡፡ ያለ እርሱ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም አልመጣምና፡፡ 
እርሱ አንድ አካል አድርጎ የሠራቸው የአካሌ ሕዋሳት ፍጹም ተስማምተው ሥራቸውን የሚከውኑ አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ እጅግ ውስብስ የሆነውን የሰውነት ሥርዓትን ሲሠራ እርሱ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር አልተማከረም፡፡ ከእኔም ሰወራቸው፤ ልወቃቸውም ብል እጅግ ይረቁብኛል፡፡ ፈጽሜም ላቃቸውም አይቻለኝም፡፡ የሚገርመው ይህን በቃሉ ብቻ የሠራውን አካሌን መንፈስ በሆነች ነፍስ እርስ በእርሱ አገጣጥሞታል፡፡ እርሱ ሁሉን ፈጣሪ አምላክ መንፈስ የሆነችውን ነፍሴን ወደ ራሱ ሲወስዳት  ከምድር አፈር ያበጃት ሥጋዬ በድን በመሆን ትፈራርሳለች፤ ትሸታለች፤ ትበሰብሳለች፤ ወደ አፈርነቱዋ ትመለሳለች፡፡ ይህ ድንቅ የሆነው ሥራው ነው፡፡ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment