Tuesday, January 29, 2019

አማልክት ዘበጸጋ



ክብር ለእርሱ ለወደደን ይሁንና እርሱ እግዚአብሔር በእርሱ አርአያና አምሳል የፈጠረውን ሰውን ሊያልቀው በወደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ ሞት የሚስማማውን የእኛን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ከእርሷ የነሣውንም ሥጋና ነፍስ ባሕርይውን ሳይቀይር አምላክ አደረገው፡፡ በእርሱም በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዌ  በጸጋ እኛ የእግዚአብሔር አብ ልጆች፣ የእርሱ የጌታችን ወንድሞች የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕፃናት ሆንን፡፡ በእርሱ በጌታችንም አማልክት ተሰኘን፡፡ ይህን ክብራችንን በትሩፋት ሥራዎች ከደከምን በዓይናችን ለማየት እንበቃለን፡፡ አረጋዊ መንፈሳዊ ከጌታ ጋር መዋሐዷ ስለተገለጠላት ትጉህ ነፍስ ሲጽፍልን፡-
“… ለፍቅረ እግዚአብሔር ጽምድት የሆነሽ ነፍስ ሆይ እንደምን ካለ ማዕረግ ደረሽ፡፡ እነሆ ከፈጣሪዋ ብርሃን ጋር ተዋሐደች፡፡ ፈጣሪዋን መሰለች፡፡ የዚህ ዓለም አነዋወሯን አታስብም፡፡ ባሕርይዋ ፍጡር እንደሆነ አታውቅም አለ፡፡ ፈጣሪ ነኝ ይመስላታል እንጂ ፍጡር ነኝ አይመስላትም፡፡ የማይመረመር እግዚአብሐርን ታውቀዋለች እንጂ ከእርሱ በቀር ሌላ አታውቅም፡፡…..” እንዲሁም… "በብረትና በእሳት ተዋሕዶ ጊዜ ይህ ብረት ነው ይህ እሳት ነው ብለህ ለይተህ አታየውም አንድ ሆነው ታያለህ እንጂ፡፡ እንደዚህም በጌታና በነፍስ ተዋሕዶ ጊዜ የነፍስና የፈጣሪን መልክ ለይተህ የምታየው አይደለም፡፡ አንድ ሁነው ታያለህ እንጂ፡፡... ባሕርይዋን ከፍጡራን ባሕርይ የለየች የከበረች ነፍስ እነሆ መልክዐ እግዚአብሔርን መሰለች … በፈጣሪያቸው ቸርነት ሁሉም አማልክት ዘበጸጋ ይባላሉ” ብሎ ገልጾልናል፡፡
ታዲያ በዚህ ተዋሕዶ ውስጥ ያለ ክርስቲያን የጌታችን እናት የቅድስት ድንግል ማርያም መውደድ እንዴት የበዛለት አይሆን! ምክንያቱም ልጇን መስሎአልና በእርሱ ፍቅር ውስጥ ስላለ ጌታው ድንግል እናቱን በሚወድድ መጠን መውደድን ገንዘቡ ያደርጋልና፡፡ ለእርሷም ያለው መውደድ እጅግ ታላቅ ይሆንለታልና፡፡ በእውነት ጌታውን ተዋሕዶ ጌታችን ለእናቱ ያለውን መውደድ የተረዳ ሰው ብፁዕ ነው፡
    

1 comment:

  1. በእውነት ጌታውን ተዋሕዶ ጌታችን ለእናቱ ያለውን መውደድ የተረዳ ሰው ብፁዕ ነው፡

    ReplyDelete