Sunday, January 22, 2017

"ሥጋን ለበሰ" ማለት ትርጉሙና ምንጩ?


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
14/05/2009
በአበው ሊቃውንት ዘንድ የቃል ሥጋ መሆን ወይም የሥጋ አምላክ መሆን ለማስረዳት ሲሉ “ሥጋ ለበሰ” የሚለውን ቃል መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “ለበሰ” የሚለው ቃል እንደ አገባቡ የራሱ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ልብስ ለበሰ፣ ኤፉዱን ለበሰ፤ ኃይልን ለበሰ ወዘተ የሚሉ ዐረፍተ ነገሮችን በተለይ በኦሪቱ በስፋት ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን ይህን በምንረዳበት መንገድ ከታች ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መረዳት አንችልም፡፡ ለምሳሌ፡- “እግዚአብሔርም ምድርን እነሆ ተበላሸች ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሸቶ ነበርና”(ዘፍ.6፡12) የሚል ቃል አለ፡፡ በዚህ ሥፍራ “ሥጋን የለበሰ ሁሉ” ሲል ሥጋን እንደ ልብስ የለበሰ ማለት ሳይሆን “ሰው የሆነ ሁሉ” ማለቱ እንደሆነ ለሁሉ ግልጽ ነው፡፡

በወንጌል ደግሞ “እነዚህ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበረ”(ማቴ.24፡22) ብሎ ይገልጥልናል፡፡ በዚህም “ሥጋን የለበሰ” ሲል ሥጋን እንደ ካባ የደረበ ማለት ሳይሆን “ሰው የሆነ ሁሉ” ማለቱ ነው፡፡ እንዲሁ “ሥጋ የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ”(ሉቃ.3፡3-6)ሲል “ሰው የሆነ ሁሉ የእግዚአብሐርን ማዳን ይይ” ማለቱ እንጂ ሳንፈልግ እንደምናወልቀው ስንፈልግ አንደምንለብሰው ልብስ “ሥጋን የለበሱ” ማለት እንዳልሆነ ማንም ግልጽ ነው፡፡ እንደተጨማሪም እነዚህን ጥቅሶ ይመልከቱ  “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አይመካ”(1ቆሮ.3፡20) “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ”(ገላ.2፡16) “ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ” (የሐዋ.2፡17) “ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው”(ሮሜ.3፡20) በእነዚህ ጥቅሶች ሁሉ “ሥጋን የለበሰ” የሚል ቃልን ስናነብ ሰው የሆነ ማለታቸው እንደሆነ እንጂ ሥጋ እንደ በአካላችን ላይ እንደምንደርበው ልብስ የምንለብሰውና የምናወልቀው እንዳልሆነ ያስረዱናል፡፡
እንግዲህ ይህንን መሠረት አድርገው ሊቃውንት አባቶች ክርስቶስ የድንግል እናታችንን ሥጋ ለበሰ ብለው ጽፈውልን እናገኛለን፡፡ እንዲህ ሲሉ ሰው ሆነ ማለታቸው እንጂ ሥጋን እንደሚለበስና እንደሚወለቅ ልብስ ለበሳት እያሉን አይደለም፡፡ እንዲህ እያሉ አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋን የለበሰ ሲል ሰው የሆነ ማለቱ እንደሆነ በግልጽ አረጋግጦልናል፡፡
ስለዚህም ነው እነ ቅዱስ ያሬድ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ በተለይ ቅዱስ ኤፍሬም ቃሉን በብዛት ሲጠቀሙበት የሚስተዋሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድ በደረሰው በአንቀጸ ብርሃን ላይ “… ወኢየሱስ ለብሰ ሥጋ ዚአኪ” ሲል በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ ደግሞ እንዲህ ዓይነት አገላለጾች በስፋት ሰፍረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኢንዚናዙ “እግዚአብሔር ላደረገው ለዚህ እንግዳ ሥራ አንክሮ ይገባል፤ መቀላቀል ለሌለበት ድንቅ ለሚሆን ለዚህ ተዋሕዶ አንክሮ ይገባል ፤ ጥንት የሌለው ጥንት ያለው ሆነ ያልተፈጠረ እርሱ የተፈጠረ ሥጋን ለብሶ ዛሬ ተገለጠ ሊቀ ካህናትና ሐዋርያ በአደረገው በአብ ዘንድ የታመነ የምናምንበት ኢየሱስ ክርስቶስን ዕወቁ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡( ዕብ.3፡1-3፡፡ ምዕ.61፡3፡፡ ገጽ.218)ሲል ቅዱስ አጢፎስ “እንደ ወደደ ከድንግል ነፍስን ሥጋን ፈጥሮ ለበሰ፤ እርሱንም ተዋሕዶ ዛሬ ተወለደ ሕጸጽ ያለበት ነው ብሎ ባሕርያችንን አልተወውም ሥጋን በተዋሕደ ጊዜ ቃል ከምላቱ አልተወሰነም ሥጋ የፈጣሪ አካል ባሕርይ በሆነ ጊዜ ፍጹም አምላክነትን አገኘ እንጂ፡፡ (ምዕ.66፡ 15፡፡ ገጽ.236) ብሎ ጻፈልን ፡፡
ቅዱስ ቄርሎስ ደግሞ “ንእመን ቦቱ ከመዝ ወንበል ፩ዱ ውእቱ ለሊሁ ከመ እምቅድመ ይልበስ ሥጋ” ….. ሥጋን ከመልበሱ እርሱንም በእውነት ከመዋሐዱ አስቀድሞ እርሱ አንድ ብቻ ነው፡፡ …..(ቄርሎስ ም.79፡3) በሌላም ሥፍራ “ሥጋን ለለበሰ ለመለኮት… እንደሚገባ የባሕርይ አድርጎ የአምላክነት ክብር በእርሱ አለ እንጂ፡፡ ሥጋን የተዋሐደው ቃል አምላክ ነውና እግዚአብሔርም ነውና”(ሃ.አ. ምዕ.74፡ቁ.29 ገጽ 322.) ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ ይህን የመሰሉ አገላለጾች በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ በስፋት ሠፍረው እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የዕብራውያንን መልእክት በተረጎመበት ድርሳኑ “መጽአ ኀቤነ በልብሰተ ሥጋ” (ገጽ.68፡16) ብሎ ጽፎልናል፡፡ እንዲሁ ቅዱስ ኤፍሬም አንድ ወጥ ሆኖ የተዘጋጀውን ወንጌላት በተረጎመበት መጽሐፉ፣ በደረሳቸው መዝሙራቱ፣ በትርጓሜ ሥራዎቹ ሁሉ ላይ ሥጋ ለበሰ ብሎ መጻፉ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ በዴያቴሳን(ወንጌላት) ትርጓሜ ላይ “ስለምን ጌታችን ሥጋን መልበስ አስፈለገው? ምክንያቱም ይህ ሥጋ ድል መንሳትን ገንዘቡ ያደርግና የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታዎች ይረዳ ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሥጋን ሳይለብስ ዲያብሎስን ድል ቢነሣው ምን ይደንቃል? አምላክነቱን ድል የሚነሣ የለምና፡፡ ሥጋን የመልበሱ ሁለተኛው ምክንያት ግን አዳም አምላክነትን መሻቱ እግዚአብሔርን በእርሱ ላይ በቅናት እንዳላነሳሳው ያሳየው ዘንድ ነው፡፡”ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡

ስለዚህም “ሥጋን ለበሰ” የሚለው ቃል “ቃል ሥጋ ሆነ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር ፍጹም አንድ የሆነ ትርጉም ያለው ተዋሕዶን የሚያስረዳ ቃል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን ሥጋ ለበሰ ማለት እንደሚለበስ ልብስ ሲፈለግ ይወልቃል ሲፈለግ ይለበሳል የሚል ትርጉምን የሚሰጠን ከሆነ ከላይ ያስቀመጥናቸው ኃይለ ቃላት ሁሉ ሥጋ እንደ ልብስ ይለበሳል ሲያስፈልግ ይወለቃል የሚል ትርጉምን በሰጡን ነበር፡፡ 

No comments:

Post a Comment