በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/01/2005
ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን
መጽሐፍ ቅዱስ ማለት የፊደል ገበታ ማለት ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ሀሁ ያልቆጠረ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በተናገረው
ጊዜ ማን እንደተናገረው ለይቶ ማወቅ ይቸገራል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ዮሐንስ ጨርሶ ላነበበ ኦርቶዶክስ
ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መልእክታት አንዱን ከአንዱ ጋር እያዛመደ መልእክት የሚሰጡ ቃላትን በመመሥረት
የእርሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲረዳው ያደርገዋል፡፡ ይህን ከተረዳ በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስ ድምጹን ያሰማዋል፤ እርሱም ይሰማዋል፡፡ በእርሱም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ለመመላለስ የበቃ ይሆናል፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ሌሎች ድጋፍ ሰጪ መርጃ መሳሪያዎች አያስፈልጉትም፡፡ ምክንያቱም እውቀትን በቀጥታ ከእውቀት
ባለቤት መንፈስ ቅዱስ እየቀዳ ነውና፡፡
ክርስቶስ ሐዋርያትን በዚህ መንገድ ነበር ሲመራቸው የነበረው፡፡ አስቀድሞ "መጻሕፍት እንደሚሉት እንዲህ ሊሆን ይገባዋል" እያለ መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከክርስቶስ የተማሩት
ትምህርት ተደራጅቶና መልእክት ይዞ በውስጣቸው አልተቀመጠም ነበር፡፡ ያም ማለት ገና የፊደሉን ገበታ እያጠኑ ነበር ማለት ነው፡፡
ይህን እንዴት እንረዳዋለን? “እርሱም ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው አላቸው” በሚለው ቃሉ ልንረዳው እንችላለን፡፡ ከዚህም በኋላ መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን
ከፈተላቸው፡፡(ሉቃ.24፡44-45) ነገር ግን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ገና ስላለተሰጣቸው እንዲያም ሆነው ይዋልሉ ነበር፡፡ ስለዚህም
ጌታችን ለሐዋርያቱ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል”(ዮሐ.15፡26) ብሎ እንደተናገረው ሐዋርያት
በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ አስቀድመው በጌታችን የተማሩትን ትምህርት አደራጅቶና ትርጉም ሰጥቶ መንፈስ ቅዱስ ገለጠላቸው፡፡
እንዲህ ነው እንግዲህ የአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መንፈሳዊ ከፍታ
መሆን ያለበት፡፡ አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከሀ -ፐ ያነባል፤ በመቀጠል ግን በውስጡ ያደረው መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩትን
መልእክታት
እየገለጠለት የእግዚአብሔርን መልእክት እንዲረዳው ያደርገዋል፡፡ ቀስ በቀስም ከመጻሕፍትና ከሌሎችም አጋዝ የመማሪያ መንገዶች በመውጣት ልክ እንደ ሐዋርያት በቀጥታ በመንፈስ
ቅዱስ የሚመራ ሰው ይሆናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ዐይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው”ብሎ
የጻፈልን የእውቀት ከፍታ ይህ ነው ወገኔ፡፡(1ቆሮ.2፡9)
No comments:
Post a Comment