ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/07/2004
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር መብራታቸውን ከዘይታቸው ጋር አስተባብረው ይዘው የተገኙት ደናግላን ወደ ሰርጉ እንዲታደሙ እንዳደረጋቸው
ገልጦልናል፡፡ በዘይት የተመሰለው ተግባራዊ ምልልሳችን ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ስም በእኛ ይበልጥ እንዲከብርና እንዲመሰገን
ያደርገዋል፡፡ ይህም የጽድቅ ሕይወታችን ለሌሎች ብርሃን ለመሆን እንድንበቃ ያግዘናል፡፡ ስለዚህም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “የጻድቅ መንገድ
ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው” ማለቱ፡፡ (ምሳ.4፡18) መንገድ የተባለው ለክርስቶስ ፈቃድ መታዘዛችን ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ በማለት ያስተምረናል፤
“በመቅረዛችን
ውስጥ ዘይቱን በመጨመር መንፈሳዊውን መብራት ደምቆ እንዲበራ እናድርገው፡፡ መሥዋዕት አድርገን የምናቀርበውን መብራት ሰማያዊውን ሙሽራ ለመቀበል የሚያገለግል መሥዋዕት ነው፡፡ እንዲያም ስለሆነ ከመቅረዙ ውስጥ ተጨማሪ ዘይት ሊጨመርበትና እስከ ላይ ደርሶ ሊበራ ይገባዋል፡፡ እንዲህ
ካልሆነ መቅረዝ በመያዛችን ብቻ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን የምናገኝ አይደለንም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን “ምሕረትን
እወዳለሁ መሥዋዕትን አይደለም” ብሎ አስተማረን ፡፡ (ማቴ.12፡7፤ሆሴ.6፡6)
በብሉይ
የሚቀርበው መሥዋዕት ሕይወት አልባ መሥዋዕት ነበር፡፡ ምጽዋት ግን ሕያውና ቅዱስ የሆነ መሥዋዕት ነው ፡፡ በፊት በነበረው መሠዊያ ላይ
የሚቀርብ መሥዋዕት እሳት ይበላው ነበር፤ ፍጻሜውም ትቢያ መሆን ነው፡፡ እንደ አመድም ወደ ውጭ ርቆ ይደፋል ፡፡ የመሥዋዕቱም መዓዛ
ንጹሑ የሆነውን አየር ይበክላል ፡፡ ሕያው የሆነው መሠዊያ(የድሆች ሰውነት) ግን እንዲህ አይደለም ፡፡ የሚያፈራውም ፍሬ የተለየና
ሰማያዊ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለድሆች በምናደርገው የርኅራኄ ተግባር ከእግዚአብሔር
አምላካችን ዘንድ ምን እንደምናገኝ ሲገልጥ “የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና ነገር
ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፡” ብሎናል(2ቆሮ.9፡12) አንተ ከእግዚአብሔር ምህረትን ለማግኘት ስትል ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባው ባለመታዘዝህ ምክንያት ከሚመጣብህ ቁጣ ታመልጥ ዘንድ ቸርነት ያደረግህላቸው
ድሆች ስለአንተ የሚለምኑ ከሆነና ፣ በደልህ ተደምስሶ የምጽዋትህ ፍሬ እግዚአብሔር የሚመሰገንበትና የሚከብርበት ከሆነ፤ ምጽዋት አድራጊው
ነው ወይስ ምጽዋት ተቀባዩ ታላቅ የሆነ ጥቅምን የተጠቀመው? በእርግጠኝነት
ምጽዋት አድራጊው እንደተጠቀመ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! በመብራት የተመሰለው ደሃው ወገናችን ነው፡፡ ዘይቱም ምጽዋታችን ነው፡፡ ሕያው የሆነው መሠዊያ እርሱ ነው፤ መሥዋዕታችንም ምጽዋታችን ነው፡፡ ለድሃው ወገናችን ራሳችንን በንጽሕናና በቅድስና በጠብቅ ከድካማችን ያኘነው ምጽዋት አድርግን ልናቀርብለትና ከችግሩ ልናወጣው ይገባናል፡፡
ይህ መሥዋዕታችን በድካማችን ካላገኘነው ፣ በስስት ወይም በአመፃ ወይም በንጥቂያ ያላመጣነው ከሆነ ከጾምና ከጸሎት እንዲሁም
እነዚህን ከመሰሉ በጎ ምግባራት ሁሉ የበለጠ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ዋጋን ያሰጠናል፡፡ ነገር
ግን ሌሎች ሰዎችን በማስጨነቅና በመንጠቅ በአመፃ የሰበሰብነውን ገንዘብ ምጽዋት አድርገን በፊቱ የምናቀርብ ከሆነ ግን እግዚአብሔርን
ለመሸንገል በመሞከራችን ምክንያት በእኛ ላይ ቁጣው ይነድብናል፡፡ ስለዚህም ምጽዋታችን አምላካችንን እንደ መሳደብ እንዳይቆጠርብንና
አገልግሎታችን እርሱ የሚመሰገንበት አገልግሎት እንዲሆን ሁሉን በጥንቃቄ እናድርግ፡፡
ቃየል
ዋናውን ምርት ለራሱ አድርጎ የቀረውን ለእግዚአብሔር በመሠዋቱ ብቻ ጽኑ ቅጣትን ተቀበለ፤ እንዴት እኛ በንጥቂያና በአመፃ እንዲሁ
ያለድካም ሰውን በመሸንገል ያገኘነውን ሀብት ምጽዋት አድርገን በማቅረባችን ከቃየን ይልቅ የከፋ ቅጣትን እንቀበል ይሆን? ስለዚህም
ነው ጌታችን ወንድማችንን በመግፈፍ ከእርሱ የነጠቅነውን ለሌላው ቸርነት እንዳናደርግ ያስጠነቀቀን፡፡ ምጽዋታችን ከአንዱ ነጥቆ
ለሌላው በመስጠት ሊሆን አይገባውም፡፡ ይህ ቸርነትን እንደማድረግ አይቆጠርም እንደውም አረመኒያዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ የምናደርግም ከሆነ እጅግ ታላቅ የሆነ በደልን ፈጸምን፡፡
...ምጽዋታችን ከላይ የዘረዘርናቸውን ያላገናዘበ ከሆነ ቅጣትን እንጂ
በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ አያስገኝልንም ፡፡ ስለዚህም ለሌሎች ምጽዋት ማድረጋችንን ብቻ አንመልከት ነገር ግን ይህ ምጽዋት
አድርገን የምንሰጠው ገንዘብ ከሌሎች በንጥቂያ ያገኘነው እንዳልሆንም አስቀድመን ልናስበበት ይገባል፡፡
... እኛ እነዚህን ሁሉ ተጠንቅቀን በዚህ ምድር ያለንን ሕይወት በአግባቡ የመራነው ከሆነ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ የሆነ መወደድንና
ክብርን እናገኛለን፡፡ እንዲህም በማድረጋችን ታላቁን የእሳት ባሕር በምጽዋታችን መርከብ ልንሻገረው እንችላለን፡፡ በጌታችን በመድኀኒታችን
በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡
ምጽዋታችን ከአንዱ ነጥቆ ለሌላው በመስጠት ሊሆን አይገባውም፡፡ ይህ ቸርነትን እንደማድረግ አይቆጠርም እንደውም አረመኒያዊ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ የምናደርግም ከሆነ እጅግ ታላቅ የሆነ በደልን ፈጸምን፡፡እወነት እግዚአብሄር ንጽሁ ባህሪ ነውና የምናቀርበውም ንጹሁ ከበደል የነጻ መሆን አለበት ወንድማችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን እረጅም እድሜ ከጸጋ በረከተጋር ያድልልን
ReplyDeleteአምላከ ቅዱሳን ፀጋውን ያብዛልህ
ReplyDelete