Wednesday, February 12, 2020

ቀለማት በቤተ ክርስቲያን


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/06/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ለእግዚአብሔር ምድር በምልዓ ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉእንዲል ለእግዚአብሔር ከፍጥረት ወገን የእርሱ ያልሆኑና ያለምክንያት የፈጠራቸው ፍጥረታት ከቶ ማግኘት አይቻልም፡፡ እርሱ በተለይ ለሰው ልጅ የእርሱ የሆነውን ከብር እንዲያው በከንቱ ሰጠው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛት፣ እግዚአብሔርን ማሰብ፣ እንደ መላእክትና እንደ ቅዱሳኖቹ የእርሱን ክብር ለማየት መናፈቅ ፖለቲካ አይደለም ወዳጆቼ፡፡ ፖለቲካም ከሆነ በእርሱ ሥር ሆኖ መኖር ለእርሱም መገዛት ከምንም በላይ ተመራጭ ነው፡፡ የእግዚአብሔር የሆነውንም መጠቀም ቢያስከብር እንጂ የሚያዋርድ አይደለም፡፡ ይልቅ የእርሱን ክብር ያውም አምላክ የሚከብርበትን የራሳቸው ሊያደርጉ የሚቋምጡ ግብረ ሰዶማውያን ይፈሩ እንጂ እኛስ እንደ ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ነፍሳት የእርሱን ከብር በታች በምድር በላይ በሰማይ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይህን ክብሩንም ስንመገብ እንኖር ዘንድ ተጠርተናል፡፡
ወዳጆቼ እርሱ እግዚአብሔር አምላክ ቀለማትን በሚለይ፣ ለእነርሱ ትርጉምን ሰጥቶ በሚረዳው በእርሱ አርአያ በተፈጠረው በአእምሮአችን በኩል ለእኛ የሰጠውን ክብር ከፍታ መረዳት ትችሉ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ በልቡናችን ይህን መረዳት የሰጠንና እርሱም በተግባር ያሳየን ይኼንኑ ነውና፡፡ ቀለማትን ሁሉ እግዚአብሔር በምክንያት ፈጠራቸው፡፡ በተለይ ቀስተ ደመና እርሱ በመለኰታዊ ግርማው ሲገለጥ ሁሌም በዙፋኑ ዙሪያ የማይጠፋ የክብሩ መገለጫ ነው፡፡ ይህን ባለ ብዙ ሕብር የሆነው የክብሩ መገለጫ ቀስተ ደመናን እግዚአብሔር አምላክ ምድርን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ ላለማጥፋት የቃልኪዳን ምልክት አድርጎ ለኖኅ ይስጠው እንጂ ከዘለዓለም የነበረ ወደፊትም የሚኖር በግርማው በተገለጠ ቁጥር በዙፋኑ ዙሪያ የሚታይ የቀለማት ሕብር ነው፡፡ ከጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው ምልክት አስቀድሞ ያለነበረ አይደለም፡፡ ይህንንም ያየ ሕዝቅኤል፡- “በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረበማለት ሲመሰክር፤ ወንጌላዊው ዮሐንስ ደግሞ፡- “ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ”( የዮሐ.43) በማለት ጽፎልን እናገኛለን፡፡
ከዚህቀስተ ደመና ቀለማት ውስጥ ቤተ ክርስቲያናችን በሩቅ በጉልህ የሚታዩትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማትን ለራሷ በመውሰድ ምእመናንና ምእመናት ዘወትር የአምላክን ክብር ለማየት መናፈቅ በልቡናቸው እንዲኖር ስትሰብክ ኖራለች ትኖራለችም፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ሌሎችን ቀለማት አትጠቀምም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት ይሁዳን ሲባርከውልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም”(ዘፍ.4911) በማለት ከይሁዳ ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም ስለተወለደው ስለ ጌታችን ስለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢትን ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም በክርስቶስ ስለመፈጸሙ፡- “በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአልበማለት ዮሐንስ ወንጌላዊ ትርጓሜውን ጽፎልናል፡፡(ራእይ.1913) በዚህም ደሙ በወይን ጠጅ መመሰሉን እናስተውላለን፡፡ ጌታችንምጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።”(ማቴ.2627-28) በማለት ወይኑን ደመ መለኮት እንዳደረገው መረዳት ይቻላል፡፡ የወይን ጠጅ ቀለም ደግሞ የሰማያዊና የቀይ ውሑድ ውጤት ነው፡፡ በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን፡--“ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው።እንዲል ጌታችን ውኃውን የወይን ጠጅ ሲያደርገው ውኃው ይዘቱን ወይኑም የወይን ጣዕሙን ሳያጣ የወይን ጠጅ ያደረገበትን ምሥጢር ርቀት ለማወቅ እንደማይቻለን ከሰማይ ሰማያዊ የሆነው እርሱ እግዚአብሔር ቃል በማይመረመር ተዋሕዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ከእርስዋ የነሣውን ሰውነት ባሕርይውን ሳይቀይር አምላክ ማድረጉን የሚያጠይቅ መሆኑን የወይን ጠጅ ቀለም ሲያስተምረን ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ወይን ጠጅ ቀለም በውስጡ ልዩ ምሥጢርን እንዳዘለ ይረዳል፡፡ በእርሱም ከጌታችን ጋር ያለውን ተዋሕዶ ዘወትር እያሰበ አምላኩን ያመሰግናል፡፡ እንዲሁ ነጭ ቀለም ለአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን የትንሣኤው ምልክቱ ነው፡፡ ይህንንም በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ጌታችን ግርማ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ ኣሳይቶናል፡፡ ወንጌላዊው ይህን አስመልክቶከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ”(ማቴ.172) ብሎ አስፍሮልናል፡፡ ስለ እኛምከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙእንዲል ከክርስቶስ ጋር በጥምቀት ሞተን ከእርሱ ጋር የተነሣን ነጩን ልብስ ለብሰናል ይህም መለኮታዊው ብርሃኑን ተዋሕደን ስለመነሣታችን ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ለአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ነጭ ቀለም የትንሣኤው ምልክት ነውና በቀለሙ በሰማያዊው አምላክ የተሰጠውን ታላቅ ክብር ያስብበታል፡፡ ቀይ ቀለምም እንዲሁ አንድም የቅድስና ምለክቱ ነው፤ ይህም ለሙሴ በእሳት ዐምድ በመገለጥ አሳይቶታል፡፡(ዘዳግ.423-24) አንድም በደሙ ዋጋ አኛን መዋጀቱን የሚያሳስበን ነው፡፡ ጥቁርም ቀለም ለአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን አምላክ እርቃኑን በመሰቀሉ ምክንያት ፀሐይ ብርሃኗን በመከልከሏ ጨረቃም ደም በመመስሰሏ ከዋከብትም በመርገፋቸው ምክንያት ምድር ጽኑ ጨለማ ውስጥ መውደቋን የሚያመላክት፤ የክርስቶስን ሕማም የምናስታውስበት፣ የእርሱን የማይመረመር መለኮታዊ ባሕርይ የምንዘክርበትና እርሱ በሕማሙ እኛን መውለዱን የሚያሳስበን ነው፡፡ በአጠቃላይ ነጭ ቀይ እና ጥቁር ቀለም ያላቸው ክሮች በአንድ ላይ ተገምደው አንድ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ በአንገቱ መታሠሩ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ደሙን አፍሶ ስለእኛ ሞቶ የትንሣኤው ተካፋዮች ስለማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡ ሌላውንም እንዲህ እያለን እየመሰልን ብንተረጉመው ጊዜ አይበቃንም፡፡ እናው ወገኖቼ ቤተ ክርስቲያን ከአምላክ ጋር ያላትን ተዋሕዶ እንደ ጥሩ መምህር በቀለማት እየመሰለች የምታሰተምረውን ትምህርቷን ፖለቲካዊ መልክ ባትሰጡት መልካም ነው፡፡ ምከንያቱም የምትጠቀሙበትን መለያችን ነው የምትሉትን ቀለማት ሳይቀር አስቀድማ ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀምባቸው ነበር አሁንም ትጠቀምባቸዋለች፡፡ ስለዚህ ከአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ለመለየት ስትሉ ለእናንተ መለያ ፍለጋ ስትባዝኑ እንዳትውሉ እንመክራችኋለን፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በምክንያት የፈጠራቸውን ቀለማት በሙሉ የተለያዩ መንፈሳዊ መልአክታትን ለማስተላለፍ ትጠቀምባቸዋለችና፡፡ አምላከ ቤተ ክርስቲያን ማስተዋልን ይስጣችሁ፤ የልቡናችሁን ዓይኖች ይክፈትላችሁ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment