Wednesday, December 12, 2012

ክብርት ስለሆነችው ሥጋችንና በእርሱዋ የእግዚአብሔር ፈቃድ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/04/2005 ዓ.ም
ሥጋ ክብርት ናት፡፡ ገናም ከአፈጣጠሩዋ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረች ናት፡፡(ዘፍ.9፡6) የማይታየው የእግዚአብሔር መልክና ባሕርይ የሚታየው በሚታየው በሥጋ ተፈጥሮአችን በኩል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መልክና ክብር በክርስቶስ አይተነዋል፡፡ እኛንም ማዳኑ በሥጋው ሰውነቱ ነው፡፡ ተወለደ፣ በየጥቂቱ አደገ፣ ደከመ፣ አንቀላፋ፣ ታመመ፣ ተጨነቀ፣ ተሰቃየ፣ ሞተ መባሉ በሥጋው ነው፡፡
ሰውነታችን ከምድር አፈር መፈጠሯም በራሱ ሥጋን ቢያልቃት እንጂ የሚያሳንሳት አይደለም፡፡ ምድር በመኅፀኑዋ ሕይወትን፣ ኃይልን፣ ውበትን፣ መድኀኒትን፣ ለፍጥረት ሁሉ ምግብ የሆኑ በዓይነትና በብዛት እንዲሁም በይዘት እጅግ ብዙ ንጥረ ነገሮችን ሰውራና አቅፋ የያዘች ናት፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ከሰማይ በሚወርደው ዝናብ ምክንያት ተብላልተውና ተስማምተው በእግዚአብሔር ጥበብ ለፍጥረት ሁሉ ምግብን፣ ፈውስን፣ ውበትና ኃይልን ሲሰጡ ይኖራሉ፡፡ ይህን አስመለክቶ እግዚአብሔር “በዚያ ቀን እመልሳለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ ሰማይም ለምድር ይመልሳል ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፡፡”(ሆሴዕ.2፡23)ይለናል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ አልቋትና ሁሉ በሁሉ አድርጓት ከፈጠራት ከምድር አፈር ሥጋን ፈጠራት፡፡ ረቂቅ የሆነችውንም ነፍስ ከምንም ፈጥሮ ከሥጋ ጋር አዋሐዳት፡፡ ለነፍስም ሕይወት ይሆናት ዘንድ መንፈስ ቅዱስን እፍ ብሎ አሳደረባት፡፡ ይህም ተፈጥሮ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው፡፡(ዘፍ.2፡7)
ምድር ከሰማይ በምታገኘው ዝናብ በእርሱዋ ውስጥ ያለውን አቅም ተጠቅማ ሕያው ሆና ራሱዋን በልምላሜ እንድታስጌጥ እንዲሁ ሥጋችንም በነፍስ በኩል ከመንፈስ ቅዱስ በምታገኘው የእውቀት ዝናብ እግዚአብሔርን የመምሰልን አቅሟን ተጠቅማ ራሷንና ነፍስን በቅድስና ታስጌጣለች፡፡ ኃይል፣ ውበት፣ ሕይወት፣ ከእርሰዋ መንጭተው ነፍስን በበረከቶች ታረሰርሳለች፡፡
ስለምድሪቱ ጥቅም ገበሬውን ጠይቁት ይነገራችኋል፡፡ ስለምድሪቱ ሀብት በእርሷ ሆድ ውስጥ ተሰውረው የሚገኙትን ማዕድናት የሚፈላልጉትን አሳሾችን ጠይቋቸው ያስታውቋችሁማል፡፡ ከምድሪቱ በረከት መኖሪያችንን እንሠራለን፣ ብረቱ፣ ወርቁ፣ አልሙኒየሙ፣ ፕላስቲኩ፣ ነዳጁ፤ ወረቀቱ፣ መስታወቱ እንዲሁም በቁጥር የብዙ ብዙ ሺኽ የሆኑ መዓድናትን እናገኝባታለን፡፡ ማናቸውንም መገልገያ መሣሪያዎቻችንን ሁሉ ከምድር ሆድ ውስጥ ተሰውረው በሚገኙ መዓድናት እንሠራቸዋለን፡፡ ፍጥረት ሁሉ ምግቡንና መድኀኒቱን ከእርሷ ዘንድ ይሻል፡፡
የምድር አፈር በእኛ ዘንድ ምንም የተናቀች ብትሆንም ከሰማይ የተቀበለችውን የበረከት ዝናብ ተጠቅማ በእርሱዋ ውስጥ ያሉትን  መድኀኒታትን ቀምማና አጣፍጣ እንድንመገባቸውና እንድንጠጣቸው በማድረግ ኃይልና ፈውስን ትሰጠናለች፡፡  በፍጥረታትም ውስጥ መድኀኒቶችን ታኖራለች፡፡ እኛም የምድር ዕፅዋትንና እንሳሳትን በተመገብናቸው ጊዜ ለሰውነታችን ኃይልንና ጤንነትን ይሰጡናል፡፡
ሥጋችንም እንዲሁ ለነፍሳችን ናት፡፡ ነፍስ ከእግዚአብሔር አምላኩዋ ባገኘችው የእውቀት ዝናብ ሥጋን ታረሰርሳታለች፡፡ ሥጋም በፈንታዋ ከነፍስ ያገኘችውን ተጠቅማ ወደ ተግባር በመመለስ መልሳ ለነፍስ አጣፍጣና መድኀኒት አድርጋ ሕይወትንና ኃይል ትሰጣታለች፡፡ ምድሪቱንም በቅድስና ታስጌጣታለች፤ በእርሱዋም የማይታየው የእግዚአብሔር መልክ ለፍጥረት ሁሉ ይገለጣል፡፡ ፍጥረት ሁሉ በርቀት የሚኖረውን ግን ከእስትንፋስ ይልቅ እጅግ የቀረበውን እግዚአብሔርን በግዘፍ አካል ተገልጦ ያዩታል፡፡ ስለዚህም በደስታ ይፈካሉ፡፡ 
ለነፍስ ውበቱዋና ኃይሉዋ ጌጡዋም ይህች ሥጋችን ናት፡፡፡ መላእክት ግሩም በሆነ ተፈጥሮዋና ውበቷ በመደመም ትኩር ብለው በመደነቅ ይመለከቷታል፡፡ የሥጋ ተፈጥሮ እስከ ዘለዓለም እነርሱን ስታስደምም ትኖራለች፡፡ ሁል ጊዜም ከሥጋ የእግዚአብሔርን ዕፁብና ድንቅ የሆነን ሥራ እያዩ ያመሰግናሉ፡፡
  ሥጋ ከፅንሰት እስከ ሞት ተፈጥሮአዋ እጅግ ማራኪ ነው፡፡ ምድር ከሰማይ ከምታገኘው በረከት አስቀድማ ቡቃያን ሲቀጥል ልምላሜን ሲቀጥል አበባን ሲቀጥል ደግሞ ዛላን በመጨረሻም ፍሬን በመስጠት አንድ የሆነችው ዘር በዝታ ስታበቃ ወደ ምድር ማኅፀን ተመልሳ ትገባለች፡፡ ዘሮቹዋም በፈንታቸው አስቀድመው ቡቃያ ቡቃያው ልምላሜን፤ ልምላሜውም ዛላን፤ ዛላውም ዘርን በመስጠት በዝተው ምድሪቱን ይከድኗት ዘንድ እነርሱም ወደ ምድር መኅፀኑን ተመልሰው ይገባሉ፡፡ ይህ ምድርና ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ የሚቀጥል የሕይወት ዑደት ነው፡፡ ሁሌም ግን አዲስ ነው፡፡ 
እንዲሁ ይህ ዑደት በሥጋም ይፈጸማል፡፡ ሥጋ በማኅፀን ተጸንሳ ትወለዳለች፡፡ በጋብቻ በዝታ ልጆችን ወልዳ ወደ ወጣችበት ምድር ትመለሳለች፡፡ ከእርሱዋም የተገኙት ዘሮቹዋም ዘራቸውን አብዝተው ካበቁ በኋላ ቦታውን ለተተኪ ትውልድ ለቀው ወደ ምድሪቱ ይመለሳሉ፡፡ ቢሆንም ሰው ከምድር እንስሳትና ዕፅዋት የተለየ ነው፡፡ የሰው ሕይወቱ በምድር ላይ የምታበቃ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጥሮአልና ዘለዓለማዊ ነው፡፡
 ነፍስ ከሥጋ ስትለይ ወደ አምላኳ ትሄዳለች፡፡ ሥጋ ግን እስከ ትንሣኤ ድረስ በምድር ማኅፀን ውስጥ ታንቀላፋለች፡፡ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ግን ከነፍስ ጋር ተዋሕዳ ትነሣለች፡፡ ነገር ግን ሥጋ ከነፍስ ጋር አብራ በክርስቶስ አምና እንደ ፈቃዱ በመኖር ምድሪቱን በቅድስና አስጊጣ ከሆነ አምላካችን ክርስቶስ የራሱን ሥጋ ትመስል ዘንድ ይለውጣታል፡፡ በዚህም ከክብር ወደ ክብር ትሸጋገራለች፡፡ ይህ ክብሩዋ ሞትም ቢሆን የሚነጥቃት ክብር አይደለም፡፡ ነገር ግን በሕይወት ዘመኑዋ ምድሪቱን አጎሳቁላ ከሆነች፣ ያም ማለት በክፉ ሥራዋ ኃጢአትን አብዝታ ከሆነ ግን ፍሬ የላትምና ለእርሱዋ በወረደው ከነፍስ ባገኘችው እውቀት ከፍሬ ይልቅ እሾኅና አሜካላ በማብቀሏ ወይም ከጽድቅ ፍሬ ባዶ ስለሆነችና በእግዚአብሔር እውቀት ወደ ልምላሜ ስላልመጣች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ትጣላለች፡፡ በዚያም ትሉ ወደማያንቀላፋ እሳቱ ወደማይጠፋ ዘለዓለማዊ ኩነኔ ትገባለች፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን የመንፈሱ ቤተ መቅደስ ይላታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው እንደ እርሱ ፈቃድ ቢመላለስ  አባቱና እርሱ ሥጋን ማደሪያ ቤተመቅደሳቸው እንደሚያደርጓት አተምሮናል፡፡ በክርስቶስ ሥጋችን የእርሱ የእርሱም የሆነው ሁሉ የእኛ እንደሆነ ተገልፆልናል፡፡ ታዲያ ይህች ሥጋችን እንዴት ክብረት አትሆን!!!
 ከሥጋችንስ ብዙ የጽድቅ ፍሬ እንደሚጠበቅስ ላፍታ አስበን እናውቃለንን? ኃጢአት ከነፍስ እንጂ ከሥጋ አትመነጭም፡፡ ነፍሳችን የኃጢአት አስተሳሰቦችን በሕሊናዋ ካመላለሰች ሥጋን ታሳድፋታለች፡፡ ሥጋም የተሠጣትን መልሳ አብዝታና አልምታ የምትሰጥ ናትና ነፍስ ባመነጨችው የኃጢአት ፈቃድ መልሳ ዐሥር  እጥፍ ነፍስን ታሳድፋታለች፡፡ ሕሊና ንጽሕትና ከኃጢአት የራቀች ከሆነች ጣፋጭ የሆነውን ፍሬ በሥጋዋ እንድታፈራ ትሆናለች፡፡ ሥጋም እግዚአብሔር በውስጧ ሰውሮ ያስቀመጠውን በረከት ለነፍስ ትመግባታለች፡፡ ነፍስም በሥጋዋ ምክንያት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ታገኛለች፡፡ 
ለመሆኑ ወገኖች ሆይ! እንዲህ አልቆና አክብሮ የፈጠራትን ሥጋችንን እንዴት እየያዝናት ይሆን? በእውን ነፍሳችንን የእግዚአብሔር የእውቀቱ ቋት በማድረግ ሥጋችንን በቅደስና ልምላሜ በማስጌጥ ከበረከቱዋ እየተመገብን ይሆንን? ወይስ ላይዋን ብቻ ልክ በውስጡ እርጥበት እንደሌለባት እንጨት ነገር ግን በውጭ ስትታይ በቅባት አምራና ወዝታ እንደሚትታይ እንጨት አድርገናታልን? እንዲህ ከሆነ በእውነት እግዚአብሔር አምላክ ፍሬ እንዳላፈሩትና ደርቀው እንደተገኙት ቅርንጫፎች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ይጥለን ዘንድ አለው፡፡
 አምላክ ሆይ ለነፍስ በምትሰጣት የእውቀት ውኃ ከሥጋችን ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃ ጅረት ይሆን ዘንድ ማስተዋልን ስጠን፡፡ ፍሬን እንዳልሰጡና እንደ ደረቁ ቅርንጫፎች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት እንዳንጣል ጌታ ሆይ ነፍሳችንን የእውቀትህ ውቅያኖስ ሥጋችንን ደግሞ እርሻህ በማድረግ የአንተ መልክና ምሳሌ በሥጋችን እንዲታይና በቅድስናና በንጽሕና ምድሪቱን እንድናስጌጣት ፈቃድ ይሁን፡፡ ሥጋችንን እጅግ ግሩምና ድንቅ አድርገህ ለፈጠርካት ለአንተ ለአምላካችን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ  ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን!!!    

2 comments:

  1. ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን የመንፈሱ ቤተ መቅደስ ይላታል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው እንደ እርሱ ፈቃድ ቢመላለስ አባቱና እርሱ ሥጋን ማደሪያ ቤተመቅደሱ እንዲያደርጋት አስተምሮናል፡፡ በክርስቶስ ሥጋችን የእርሱ የእርሱም የሆነው ሁሉ የእኛ እንደሆነ ተገልፆልናል፡፡ ታዲያ ይህች ሥጋችን እንዴት ክብረትና ብዙ የጽድቅ ፍሬ እንደሚጠበቅባት ላፍታ አስበን ይሆን? ኃጢአት ከነፍስ እንጂ ከሥጋ አትመነጭም፡፡ ነፍሳችን የኃጢአት አስተሳሰቦችን በሕሊናዋ ካመላለሰች ሥጋን ታሳድፋታለች፡፡ ሥጋም የተሠጣትን መልሳ አብዝታና አልምታ የምትሰጥ ናትና ነፍስ ባመነጨችው የኃጢአት ፈቃድ መልሳ አስር እጥፍ ታሳድፋታለች፡፡

    ReplyDelete
  2. kalehiwot yasemalin idme tsegawin yadliln

    ReplyDelete