Saturday, December 15, 2012

የሞቴ ማስታወሻ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/04/2005
ሰው ማለት እንደ እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱ የሆነች አንዲትም ሰከንድ የለችም፡፡ ሰውም እንዲሁ ዘመኑን ሁሉ በጥንቃቄና ያለዝንጋዔ እግዚአብሔርን መስሎ ሊኖር ተፈጠረ፡፡ የሰው ደስታው እውነት፣ ጽድቅ፣ ቅን ፈራጅነት፣ ከእውቀት ያልተለየ ፍቅር ናቸው፡፡ እነዚህን በተመለከተ አዳም አባታችን፣ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና እርሱን በቅርበት ያወቁት ሐዋርያት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ከጌታችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትም የምናስተውለው ሰው ሊጸድቅ የሚችለው ልቡን በቃሉ ሞልቶ የሥነ ምግባራችን ቁልፍ በሆነው ማስተዋል የተመላለሰ  እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ግን ምናልባት በቀን ውስጥ ሁለት ደቂቃ ግፋ ቢል አምስት ደቂቃ ሰጥተን ብናስበው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ስለእግዚአብሔር እውቀቱ ካለው ነው፡፡ የሌለው ግን ዘመኑን ሁሉ እንደ ነዌ ያሳልፈዋል፤ አንድም ሰከንድ እንኳ እግዚአብሔርን የሚያስብበት ጊዜ የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝንጋዔ ሆኖ በስሜቶቹ ፈቃድ እየተነዳ በኃጢአት ሲንቧቸር ይኖራል፡፡ ይህ የአብዛኞቻችን ሕይወት ነው፡፡

ወደ ራሴ ተመለስኩ በሞት ወደ አምላኬ ስሄድ ምን እንደሚጠብቀኝ ማስላሰል ገባሁ፡፡ ከሕጻንነቴ አሁን እስካለሁበት እድሜ ድረስ ያለውን ዘመኔን አስተዋልኩት እጅግ ከንቱ የሆኑ ዘመናት ነበሩ፡፡ ያሳለፍኳቸውን እነዚያን ክፉ ዘመኖች ሳስባቸው መፈጠሬን ጠላሁት፡፡ እነዚያ ዘመናት መንገዴን አጣመሙ፤ የአምላኬን ፈቃድ እንዳልፈጽም አቅምን ነሱኝ በከንቱና ክፉ ልማዶች ተበተቡኝ ስለዚህም አምርሬ እጠላቸዋለሁ፡፡  ቅንዉን አውቃለሁ ግን መፈጸም አልተቻለኝም፤ በዚህም የተነሣ ደስታዬ ተነጥቆአል፡፡
ለምን ብዬ ብጠይቅ ግን ወደ ወላጆቼ እጆቼን እንድቀስር ያደርገኛል፡፡ “ልጄ ሆይ ሰው ሁን” የሚለውን መርህ መርሃቸው አድርገው በእግዚአብሔራዊ እውቀት፣ በዚህ ምድር ለመኖር መሠረታዊ ነገሮችን እንዴት መጠቅም እንደምችልና በኃጢአት ቁስል ሳልላላጥ፣ ኃጢአት መልከ ጥፉ ሳታደርገኝ በቅድስና እንድመላለስ አድርገው አላሳደጉኝም፡፡ እንዲህም ብዬ እነርሱን እንዳልወቅሳቸው እነርሱም በዚህ መልክ ያደጉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ሰው ሰው ሊባል የሚችለው የተፈጠረበትን ዓላማ ከወላጆቹ ተምሮ ሰውነቱን ከኃጢአት ጠባሳ ጠብቆ የኖረ እንደሆነ ነው፡፡ ያለበለዚያ በኃጢአት መልኩ ጠፍቶአልና አንገቱን   ቀና አድርጎ መመላለስ ይሳነዋል፤ ሰውን ገንዘብ፣ ሀብት፣ ስልጣንና ክብር ሰው አያሰኙትም፡፡ ነገር ግን የሚያሳዝነው ከጥንት ጀምሮ አሁንም የሰው ትርጉሙ እነዚህን መሠረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሰውን ሰው ሳይሆን አውሬ የሚያረጉት እንደሆነ እግዚአብሔር በሰጠኝ በዚህች አጭር ዘመኔ ተመልከቼአለሁ፡፡ …. ከንቱ ከንቱ ከንቱ ከንቱ ከንቱ ………. ዘመን አቤቱ አምላኬ ምሕረትህን ብቻ እለምናለሁ ይቅር በለኝ፡፡

No comments:

Post a Comment