Wednesday, February 22, 2012

ኑ ቀረብ በሉ!


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/04/2004
ፍቅር የሆነ አምላካችን ምን ያህል እኛን እንዳከበረን እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብልን እናስበው፡፡ አፍቃሪያችን አስቀድሞ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጠረን ስለዚህም ክብራችን በመላእክት ዘንድ እጅግ ታላቅ ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር መልክ አለንና እጅግ አከበሩን፡፡ ስለዚህም እርሱን እንዳገለገሉት ቆጥረው ቅዱሳን መላእክት እኛን አገለገሉን፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለን “እግዚአብሔር አምላክን በላይ በሰማይ የሚያገለግሉት ቅዱሳን መላእክት እኛን አገለገሉን፡፡ ይህ እግዚአብሔር አምላክ እኛን ምን ያህል እንዳከበረን የሚያሳየን ነው፡፡” ይህ በእርግጥ ድንቅ ነው፡፡
አክብሮ የፈጠረውን ሰብእናችንን በኃጢአት በማዋረዳችን ምክንያት ፈጣሪያችን ተመርሮብን ለዘለዓለም ቆርጦ አልጣለንም፡፡ ነገር ግን ፍቅሩ አገብሮት እኛን እጅግ ሊያከብረንና ሰይጣን ከማይደርስበት ከፍታ ከፍ ከፍ ሊያደርገን ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ ከድንግል ቅድስት እናታችን ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ሥጋና ነፍስን ከእርሱዋ በመንሳትም ተወለደ፡፡ በዚህም ባሕርያችንን አምላክ አደረገው፡፡ ቅድስት እናታችንንም ሰማይ አደረጋት፡፡ አሁን እኛ ክርስቲያኖች “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር” ስንል እነሆ እርሱዋን ሰማይ አድርገን ነው፡፡ ምክንያቱም ወልድ ባለበት አብም መንፈስ ቅዱስም አሉና፡፡ እንዲህ አድርገህ እጅግ ያከበርከንና ያፈቀርከን ፈጣሪያችን ሆይ ላንተ ምን አንደበት ነው ምስጋናን ማቅረብ የሚቻለው? 
እርሱ በዚህ ድንቅ ቸርነቱ ብቻ አላበቃም እኛንም እንደ እናቱ ለራሱ ማደሪያ በማድረግ ሰማይ አደርጎናልና እናመሰግነዋለን፡፡ እርሱ በቃሉ“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ እርሱ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ" ”(ዮሐ.6፡56)አለን፡፡ ስለዚህም ሥጋውን ስንበላ ደሙንም ስንጠጣ ከድንግል ማኅፀን ተፀንሶ የነበረው ጌታ በእኛም ሰውነት ውስጥ ያድራል፡፡ በመሆኑም እኛም እንደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማን ሰማዩ ሆንን፡፡ ድንግል ሆይ ራስሽን ለፈጣሪያችን ሰማይ በማድረግ እኛም ለእርሱ ሰማይ እንድንሆን ስላበቃሽን እናመሰግንሻለን፡፡ አሁን “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር” ስንል የእኛን ሰውነት ሰማይ አድገህ የምትኖር አክባሪያችን ሆይ ስምህ ይቀደስ እያልነው ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ ቸርነትህ ምን ዐይነት ምስጋናን ማቅረብ ይቻለን ይሆን?

እርሱ አስቀድሞ የቅድስት እናታችንን ሰብእና ወድዶ መቅደሱ አደረጋት፤ ከእርሱዋም የነሳውን ሥጋና ነፍስ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማድረግ ተፀነሰ፡፡ እንዲሁ እኛንም በልዩ መንገድ ሥጋችንን መቅደሱ አድርጎ ነፍሳችንን ደግሞ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማድረግ በእኛ አደረ፡፡ ይህን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈሱ ቤተመቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?”(1ቆሮ.6፡20)አለን፡፡ ሥጋችን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሱ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ሆነናልና በመንፈሱ ተገጣጥመን በጋራ ክርስቶስን መስለነዋል፡፡ እንዲሁ ለሥጋው ወደሙ የዘለዓለም ማደሪያው ሆነናልና ቤተ መቅደሱ ተሰኝተናል፡፡ ልባችንም ጽላቱ ነውና በዚያ ላይ እርሱ ዙፋኑን ዘርግቶ ተቀምጦአል፡፡ ስለዚህ እርሱ በእኛ ሲሆን እኛም በእርሱ ሆነናል፡፡ ስለዚህም መቅደሱና ቅድስተ ቅዱሳኑም አደረገን፡፡
በተጨማሪም የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደሶች ሆንን ማለት የአብም የወልድም ቤተመቅደሶች ሆንን ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ድንግል ሆይ አንቺ ራስሽን መቅደስና ቅድስተ ቅዱሳን በማድረግሽ ምክንያት እኛም ለአፍቃሪያችን ሥጋችን መቅደሱ ነፍሳችን ቅድስተ ቅዱሳኑ እንዲሆን ምክንያት ሆነሽናልና እናመሰግንሻለን፤ እንወድሻለንም፡፡ እንዲህ ዳግም በሞቱ እኛን ሕያዋን አድርጎ ለፈጠረን፣ ከቀድሞ ክብራችን ይልቅ እጅግ አግንኖና አልቆ ላከበረን አምላካችን በፍጹም መገዛትና ፍቅር ሆነን ልናገለግለው በእውነት ይገባናል፡፡ እርሱ በዓለም ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ በዓለም ሁሉ ሙሉ የሆነው እርሱ በድንግል መኅፀን እንደነበረ እንዲሁ በእኛም ውስጥ አለ፡፡ ይህ ደግሞ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ እኛ በእርሱ ውስጥ መሆናችን አይደንቅም፤ ነገር ግን ዓለምን በመሐል እጁ የያዘ እርሱ በእኛው ውስጥ መሆኑ ግን ግሩም ነው፡፡ ይህም በሥጋ ወደሙ ተፈጽሞልናል፡፡
 ለአዳም አባታችን ፍቅር የሆነው ፈጣሪ ገነትን የንግሥናው ሥፍራ አደረጎ ሰጠው፡፡ ለእኛ ግን በኃይሉ ሳይሆን በፍቅሩ የሚገዛን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረታዊቱን ገነትን ሳይሆን ሰውነቱን ገነት አድርጎ አወረሰን፡፡ አፍቃሪያችን አስቀድሞ ድንግልን ገነቱ አድርጎ ሰውነቱን ገነት አደረጋት፡፡ በመቀጠልም ገነት የሆነችውን ሰውነቱን እርሱ በሠራልን ጥምቀት ከሰውነታችን ጋር አዋሐዳት፡፡ አሁን እርሱ ግንዳችን ሲሆን እኛ ቅርንጫፎቹ ነን፡፡ እርሱ አካላችን ሲሆን እኛ የአካሉ ሕዋሳት ነን፡፡ ስለዚህም እርሱ ለእኛ ገነት በመሆን እኛንም ገነት አደረገን፡፡ በገነት ውስጥ ያሉ በረከቶች ሁሉ በእርሱ ውስጥ በምላት ይገኛሉ፡፡ የሕይወት ዛፉን በጦር በተጋው ጎኑ ላይ ተከላት፤ ከእርሱዋም ሕይወትን የሚሰጡ ፍሬዎች ይፈሩባታል፡፡ የሕይወት ዛፉም በጦር የተወጋው ጎኑ ነው፤ ከእርሱ ሥጋውን በላን ደሙን ጠጥተን ሕያዋን ሆንን፡፡ የራሱን ሰውነት ገነት ያደረገ ጌታችን ከአንደበቱ ቃሉን አመንጭቶ በዐራቱ ወንጌላውያን ገነት ያደረጋትን ሰብእናችንን አረሰረሳት፡፡ በውስጡዋ ያሉትን ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ የበረከት ዛፎች ብዙ ፍሬን እንዲሰጡ መገባቸው፡፡ በገነት ውስጥ ለማየት ደስ የሚያሰኙና ለመብላት መልካም የሆኑ ልዩ ልዩ ፍሬዎች ከእርሱ ዘንድ በምላት ይገኛሉ፡፡ ድንግል ሆይ ሰውነትሽን ለእርሱ ገነቱ በማድረግ እኛን ገነቱ አድርገሽናልና እናመሰግንሻለን እናፈቅርሻለን፡፡ እነሆ የገነት አስገኚው የሆነው እርሱ በአንቺ ውስጥ እንደነበረ እንዲሁ ከአንቺ የለበሰውን ሰብእና መልሶ ለእኛም በማልበስ እኛን ገነት አሰኘን፡፡ ስለዚህም ስሙ ፍቅር የሆነው ፈጣሪያችን እንዲህ አድርጎ አልቆ አክብሮናልና በፍጹም ልባችን እናመሰግነዋለን፡፡  
ጌታችን ሆይ አንተ ስታስተምር "መንግሥተ ሰማያት በመጠባበቅ አትመጣም ደግሞም እነኋት በዚህ ወይም እነኋት በዚያ አይሉአትም እነሆ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት"አልኸን(ሉቃ.17፡20)፡፡ እንዲያ ከሆነ በመካከላችን ያለህ አንተ ነህና ከአንተ ውጪ መንግሥተ ሰማያት ማን ሊሆን ይችላል? ጌታ ሆይ አንተ መንግሥተ ሰማያታችን ነህ፡፡ እኛም በአንተ ውስጥ የምንኖር ሕዝቦችህ ነን፡፡ ልባችን የመንግሥትህ ዙፋን የተዘረጋበት መንበርህ ነው፡፡ ሰውነታችንም ግዛትህ ነን፡፡ ስለዚህም እኛም ሰማያዊው መንግሥትህ ሆንን፡፡ ይህን አንተ አደረግኸው፤ አንተ እኛን መስለህ እኛም የአንተ መልክና አርአያ እንዲኖረን አድርገኸናልና ከልባችን ሆነን ለአንተ ምስጋናን እናቀርባለን፡፡
በአዳም መተላለፍ ምክንያት ከአንተ ተለይተን በኃጢአት ምክንያት ሰይጣን እኛን ገዛን፡፡ ሰይጣንም የልጅነት ሕልሙን በእኛ ላይ እንደ አምላክ በመሆን ፈጸመብን፡፡ እርሱ ለአንተ እንደማይጠቅም ባርያ እንደሆነ እኛም እንደ እርሱ ለአንተ የማንጠቅም ባሮች ሆንን፡፡ ለእርሱ እምቢ ብለን ለአንተ እንኳ ብንገዛ ባንተና በእኛ መካከል ያለው ሥርዐት በጌታና በባሪያ መካከል እንዳለ ዓይነት ሥርዐት ስለነበረ ባርነታችን አልቀረልንም ነበር፡፡ ስለዚህም በብሉይ ኪዳን በጽድቅ የተጉ ቅዱሳን ምድራዊ በረከትን አገኙ እንጂ ከሲኦል ሞት አምልጠው ከመላእክት ጉባኤ አልታደሙም፡፡ ጌታ ሆይ አንተ ግን ከዚህ ጽኑ አገዛዝ በቸርነትህ አዳንከን፡፡ እኛንም መልሰህ በውኃና በመንፈስ በመውለድ ልጆችህ አደረግከን፡፡ በዚህም የርስትህ ወራሾች ሆንን፡፡ ስለዚህም ለአንተ ስንገዛልህ የአንተን ሀብት የራሳችን አድርገን በመቁጠር ነው፡፡ ያንተን ሕግጋት ስንፈጽም ለእኛ ጥቅም እንደሆነ ተገንዝበን በፍቅር ነው፡፡ ስለዚህም ይህን እውነት ለማወቅ አንድ ደረጃ በእውቀት ቀረብ እንበል፡፡ ምሳሌዎቹ ሁሉ ስለእኛ ተነገሩ፤ በድንግል ማርያም በኩል አማናዊው ሰማይ የተባልነው እኛ ነን፤ ገነት የተባልነውም እኛው ነን፤ መቅደሱም እኛው ነን፤ ቅድስተ ቅዱሳኑም እንዲሁ እኛው ነን፡፡ ኑ ቀረብ በሉ እግዚአብሔር እኛን ምን ያህል እንዳከበረን አይተን እናድንቅ፡፡ እኛ በእርሱ እርሱም በእኛ ሆነ፤ ክብር ይሁን ለወደደን ይህን ታላቅ ክብር ለሰጠን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!! 


No comments:

Post a Comment