Sunday, February 19, 2012

ያልታወቀው የጦም ጥቅም



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
12/06/2004



ብዙዎቻችን የጦም ጥቅሙ ከምግብ ተከልክለን ራሳችንን ከእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ከእርሱ ዘንድ ሰማያዊ ጸጋን ማግኘታችን ነው፤ ብለን እናስባለን፡፡ ይህ ፍጹም ትክክል ነው፤ ነገር ግን ክብር ለእርሱ ይሁንና ሌላ እኛ የማናውቀው በጦም የኖሩ ቅዱሳን የሚያውቁት አንድ ልዩና ግሩም የሆነ ጥቅም አለው፡፡ እንዲህ ሲባል “ከእኛ ምን ተሰውሮ! በጦም ነፍሳችን ለሥጋ ከመትጋት ወጥታ ከእግዚአብሔር ጋር በተመስጦ በመኖሯ ነፍሳችንም ሥጋችም የሚጠቀሙት ጥቅም አላቸው፡፡” ብላችሁ ትመልሱልኝ ይሆናል፡፡ እንዲህ የመለሳችሁ እንደሆነ እኔ ልገልጠው ያሰብኩትን ጭብጥ አላገኛችሁትምና ሌላ ሞክሩ፡፡ ወይም "ከጤና አኳያ ሰውነታችንን ከምግብ በከለከልናት ጊዜ አካላችን በራሱ የአሠራር ሥርዐት በሰውነት የተከማቸውን ስብ ወደ መጠቀም ስለሚመጣ የስብ ክምችታችን ይቀነሳል፤ ስለዚህም በስብ ክምችት ምክንያት ከሚመጡ ሪህ፤ ደም ግፊትና ስኳር እንዲሁም እነዚህን ከመሰሉ ሕመሞች ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህም ሰውነታችንን ጤናማ በማድረግ ያለምንም የጤና መጓደል መንፈሳዊ የሆኑ ተግባራትን ለማከናወን ስለሚያገለግለን ነው” ብላችሁ ልትመልሱ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ግን መልሱን አላገኛችሁትም ነው መልሴ፡፡ “እሺ ይህ ካልሆነ እኛ ጌታችንን መስለን በመጦም ሰይጣንን ድል መንሳታችን ነው ጥቅሙ” ትሉኝ ይሆናል፡፡ እርሱም ጥሩ መልስ ነው፡፡ ምክንያቱም ጦም ነፍስን እንደ መልአክ ስለሚያደርጋት ወይም የሥጋ ሥራ ስለሚቀልላት ዐይኖቹዋ በጦም ሰዓት አጥርተው ይመለከታሉና በቀላሉ ሰይጣን ድል ሊነሳት አይቻለውምና ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ የመለሳችኋቸው ሁሉ ትክክለኛ መልሶች ቢሆኑም እኔ ልል የፈለግሁትን ግን አላገኛችሁትም፡፡ "እሺ ከእነዚህ ውጪ ምን ልዩ የሆነ መልስ ሊኖር ይችላል? ብላችሁ ጽምፃችሁን አሰምታችሁ ልትናገሩኝና የእኔንም መልስ ጆሮአችሁን አቀቅራችሁ ልትጠባበቁኝ ትችላላችሁ፡፡













ነገር ግን ጆሮ ሰጥታችሁ ለማዳመጥ ስለተዘጋጃችሁ አስቀድሜ እጅግ ላመሰግናችኋለሁ እወዳለሁ፡፡ ጥቅሙ ይህ ነው፡- እግዚአብሔር የሚወዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች ሆይ ሰው ሕሊናውን ሰብስቦ እግዚአብሔርን አስቦ የሚጦም ከሆነ ልክ እስራኤላውያን በግብጽ ምድረ በዳ መና ወርዶላቸው ለነፍሳቸውም ለሥጋቸውም ሕይወት የሚሰጥ ምግብን እንደተመገቡ እንዲሁ አንድ ጦዋሚም በማስተዋል ሆኖ የሚጦም ከሆነ ከላይ ከአምላኩ ዘንድ ረቂቅ የሆነ መንፈሳዊ ምግብን በመመገቡ ምክንያት ሥጋው ርሃቡ ጠፍቶላት ስትለመልም ይታወቀዋል፡፡ ይህ ግን በአንድ ጊዜ የሚታወቅ አይደለም ቀስ በቀስ እንጂ፡፡
እንዲህ ነው ፡- ጌታችን አፍቃሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በቃና ሰርግ ላይ ወይን ጠጁ ከድንጋይ ጋኖቹ ማለቁን ከአረጋገጠና በጋኑ ውስጥ ያለው አተላ በአይሁድ የማንጻት ልማድ ከተደፋና ንጹሕ ከሆነ በኋላ አገልጋዮቹን ውኃ ሙሉበት በማለት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት ቀየረ፡፡ እንዲሁ እኛም በሰውነታችን ውስጥ ተከማችቶ ያለው ስብ በጦም እስክናጠፋው ድረስ ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅመውን ረቂቁን ሰማያዊ ምግብ ከመስጠት እግዚአብሔር አምላክ ይከለከላል፡፡ ይህን የሚያደርገው ግን  ለእኛ ምድራዊውን ምግብ ተክቶ ኃይልና ደመግባትን የሚሰጠንን መንፈሳዊ ምግብ በአግባቡ እንድንለየውና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ይህን ሰማያዊ ምግብ ለመመገብ ፈቃዱ እንዲኖረን ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን ለእኛ ለማስተማር ሲልም ጌታችን “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም”ብሎ አስተማረን ፡፡
 እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ ምድር ከምታፈራቸው አዝርዕትና ፍራፍሬዎች አልተመገቡም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ መናን ከሰማይ እያወረደ ይመግባቸው ነበር፡፡ ይህ መና ለነፍሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሥጋቸውም ሕይወትን ሰጥቶአቸው ነበር፡፡ ይህ ግን ለአማናዊው ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር፡፡ ይህንንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ምግብ አበርክቶላቸው ለመገባቸው ሕዝቦች “እውነት እውነት እላችኋለሁ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው አንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው”(ዮሐ.6፡33)በማለት በሰጣቸው መልስ መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከሥጋ ርሃብም በመናው ምክንያት ድነዋል፡፡ ስለዚህም ይህ መና ለጌታችን ሥጋና ደም ምሳሌ ብቻ ሳይሆን ረቂቅ ለሆነው በጦም ሰዓት ለምንመገበው ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ምግብም ምሳሌ መሆኑን እንረዳለን፡፡ 
 ስሙ ይክበር ይመስገንና የጌታችን የመድኀኒታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም እንደምናውቀው ሆድን የሚሞላ አይደለም፡፡ ነገር ግን ነፍስንም ሥጋንም  የሚቀድስ ነው፡፡ ስለዚህም ለቁመተ ሥጋ ስላልሆነ ከቆረብን በኋላ ምግብን እንመገባለን፡፡ ነገር ግን ረቂቅ የሆነው መንፈሳዊው ምግብ በዐይነቱ ከክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ጋር የሚስተካከል ባይሆንም ለነፍሳችንና ለሥጋችን ኃይልን ይሰጣቸዋል፡፡ ከሥጋው ወደሙም የሚለየው ለነፍስም ለሥጋም ምግብን ተክቶ ኃይልን መስጠቱ ነው፡፡ ስለዚህም መናው ለዚህ ሰማያዊ ረቅቅ ምግብም ምሳሌው እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡  ይህን መንፈሳዊ ምግብ ከተመገብን በኋላ ለረጅም ሰዓታት ምንም ዓይነት የረሃብ ስሜት አይሰማንም፡፡ ይህን ሰማያዊ ምግብ አስቀድሞ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ተመግቦት ነበር፡፡ እርሱ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ያለአንዳች ምድራዊ ምግብና መጠጥ ለሁለት ጊዜ ጦመ፡፡ ነገር ግን በጦሙ ሰውነቱ ከመጠውለግ ይልቅ እንደ ፀሐይ ደምቆ እያበራ ወደ ወገኖቹ ተመለሰ፡፡ እኛም እንዲህ ዓይነት ብርታት ከጦምን በኋላ ሊሰማን ይችላል፡፡ ይህ የሆነው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ባገኘነው መንፈሳዊ መግቦት እንደሆነ ሕሊናችን ይመሰክርልናል፡፡ በዚያን ወቅት መንፈሳዊ መረዳታችን እጅግ ይጨምራል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ምግብ እንደበላ ሰው እንደውም የበለጠ ኃይልና ደምግባት ይኖረናል፡፡
ቢሆንም ይህ በዚህ መልክ አይቀጥልም፤ ምክንያቱም ክርስቲያን በዚህች ምድር በሕይወት መኖሩ ሌሎችንም ከጥፋት መልሶ ለእግዚአብሔር ምርኮን እንዲያመጣ ስለሆነ እግዚአብሔር ይህን መንፈሳዊ መግቦትን ከእነርሱ አቋርጦ ምድራዊውን ምግብ እንዲመገብ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ መግቦት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ከዚህ መውጣትን የማይፈልጉ ቢሆኑም እግዚአብሔር ስለብዙሃኑ ጥቅም ሲል ለሰው ሁሉ ወደ ተሠራው ሥርዐት ይመልሳቸዋል፡፡
 ይህን ለመረዳት ነቢዩ ኤልያስን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይጠቅማል ፡፡ ነቢዩ ኤልያስ እስራኤላውያን በኣል የሚባለውን ጣዖት ባመለኩ ጊዜ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሰማይ ዝናብን እንዳትሰጥ ሦስት ዓመት ለጉሟት ነበር፡፡ ለእርሱ ግን እግዚአብሔር አምላክ ቁራን አዞለት በቤተ መንግሥት የሚዘጋጀውን ምግብ ይመገብ፣ ከተሰወረበትም ዋሻ ውኃን አመንጭቶ ያጠጣው ነበር፡፡ ይህ እኛ በጦማችን ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምንመገበው ምግብን ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሌሎች በርሃብ እያለቁ እርሱ ግን እድሜ ዘመኑን ጠግቦ እንዲኖር ርኅሩኅ የሆነ አምላክ አልፈቀደምነና እግዚአብሔር አምላክ አልያስን  መመገቡን አቆመ፤ ያመነጨለትንም ምንጭ አደረቃት፡፡ እርሱም ለምን እንዲህ አደረግህ ብሎ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡ እግዚአብሔር ግን በቀጥታ መልሱን አልመለሰለትም፡፡ ነገር ግን የምትመግብህን አንዲት መበለት አዘጋጅቼልሃለሁና ወደ እርሱዋ ውረድ አለው፡፡ እንዲህ ማድረጉ የሕዝቡን መራብ አይቶ ይራራላቸውና ስለእነርሱ መዳንም ይተጋላቸው ዘንድ ለማሳሰብ ነበር፡፡ ስለዚህም ነቢዩ በመበለቱዋ መራብ ሕዝቡ በርሃብ ወደ ማለቅ እንደመጣ አስተዋለ፡፡ ስለዚህም ስለእግዚአብሔር መኖር ሕዝቡን አስተማራቸው፤ የበኣልንም አምልኮ አስቀረ፤ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መለሰ፤ በመቀጠልም እግዚአብሔር ዝናቡን ይሰጥ ዘንድ ለመነ፤ ዝናብም ዘነበ ሕዝቡም በርሃብ ከማለቅ ዳነ፡፡(1ነገሥ.ም.17 እና 18)
እንዲሁ እኛም ይህን መንፈሳዊ ምግብ እግዚአብሔር ዘወትር ቢመግበን ኖሮ እርሱ የሞተለት ሕዝብ በቃለ እግዚአብሔር ርሃብ ማለቁን አንገነዘብም ነበር፡፡ ስለዚህም ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ ከመገበን በኋላ ስለሌሎች ጥቅም ሲል ይህን ምግብ ከእኛ ዘንድ ይከለክለዋል፡፡ እኛም ተመልሰን ከማኅበራዊው ሕይወት ጋር አንቀላቀላለን፡፡ በእኛም ማኅበራዊ ተሳትፎ የእነርሱን ከእግዚአብሔር ተለይተው በአጋንንት አገዛዝ ሥር መውደቃቸውን ስለምንገነዘብ ስለእነርሱ መዳን እንተጋለን፡፡ ወይም ከእነርሱ ጋር ቃለ እግዚአብሔርን ለመነጋገር አጋጣሚውን ካገኘን በቃሉ መረብነት የጠፉትንና የባዘኑት በጎች ወደ በረታቸው እንመልሳቸዋለን፡፡
 ቢሆንም እግዚአብሔር መንፈሳዊውን መግቦት ለእኛ ማሳየቱ ለተወሰኑ የጦም ወቅቶች ብቻ እንድንገለገልበት ሳይሆን ይህ ዐይነት መንፈሳዊ መግቦት ዘወትር እንደሚያስፈልገን አውቀን በሃያ ዐራት ሰዓታት ውስጥ ጊዜ መድበን ከዚህ ሰማያዊ ማዕድ እንድንመገብ ሊያሳስበንም ጭምር ነው፡፡ እንዲያ ከሆነ ብቻ ነው “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል በትክክል ወደ መረዳት የምንመጣው፡፡(ዮሐ.4፡4)  
ምናልባትም ከነሕይወታቸው ወደ እግዚአብሔር የተወሰዱ ሄኖክና ኤልያስ የሚመገቡት ምግብ እኛ በጦም ሰዓት የምንመገበውን ይህን ረቂቅ መንፈሳዊ ምግብ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ምግብ የሚያስፈልጋትን ሥጋንም እንደያዟት ነውና ወደ እርሱ የሄዱት፡፡ እንዲህ ስል ግን ሥጋው ወደሙን የሚተካ ነው ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ እንዳለ ሆኖ ይህም ለእኛ በመንፈስ እንድንመላለስ በእጅጉ እንደሚረዳን ለማስገንዘብም ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እርሱ የጦመውን ይህንን ዐቢይ ጦም ጦመን ከዚህ መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ መንፈሳዊ ማስተዋላችን ጨምሮ በዲያብሎስ አገዛዝ ሥር ያሉትን ወገኖቻችንን ከጥፋት ለመመለስ የበቃን ያድርገን፡፡
ምስጋና ይሁን ፍቅር ለሆነው ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!    

2 comments:

  1. እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር ይስጥልን!

    ReplyDelete