Sunday, January 6, 2013

“በአፉ መሳም ይሳመኝ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/04/2005
በአፉ መሳም ይሳመኝ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና፡፡”(ማኃ.1፡1) የሚለው ቃል በይሁዳ ቤተልሔም እነሆ ተፈጸመ፡፡ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰዎች የሚሰጠውን  ሰላምና ፍቅር እንዲሁም እርቅ የሚናፍቁ የነቢያትና የቅዱሳን የናፍቆት ቃል ነበር፡፡ “በአፉ” ሲል “በእግዚአብሔር ቃል” ሲለን ሲሆን “ይሳመኝ” ሲልም የእግዚአብሔር ቃልን ሰው መሆን መናፈቃቸውን የሚናገር ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ እንዴት በአፉ ሊስመን ይቻለው ነበር? ይህ ቃል እርቅ በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል መፈጸሙ የማይቀር መሆኑን የሚያውጅ የናፍቆት ቃል ነው፡፡

 ሰሎሞን “በአፉ መሳም ይሳመኝ” ሲል በነቢያት ይወርዳል ይወለዳል የሚለው እግዚአብሔርን ከሰው፣ ሕዝብን ከአሕዛብ ፣ መላእክትን ከሰው ጋር የሚያስታርቀው እግዚአብሔር ቃል (አፉ) በሥጋ ሰውነት መወለዱን የሚናገር ኃይለ ቃል ነው፡፡ አረጋዊው ስምዖን ለእስራኤል ሰላምን የሚሰጠውን የሰሎሞንን ናፍቆት ሳያይ እንዳይሞት መንፈስ ቅዱስ ነግሮት ነበር፡፡ እርሱም በክርኑ ታቅፎ “ጌታ ሆይ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና ይህም ለአሕዛብ ሁሉ የሚገለጥ ብርሃን ለእስራኤልም ክብር ነው፡፡” ብሎ በመንፈስ ተናገረ፡፡ ለእኛም “በአፉ መሳም ይሳመኝ” የሚለው ቃል በጥምቀት ተፈጽሞልን እነሆ ክርስቶስ በመንፈሱ ሳመን ፍቅሩንም በመንፈሱ አፈሰሰልን እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፈርም፡፡(ሮሜ. 5፡5)
እነሆ የነቢያት ተስፋ የሆነ ጌታችን በአፉ ሊስመን በእንስሳት በረት ተወለደ እንስሳትም በእስትንፋሳቸው አሟሟቁት እረኞች አመሰገኑት ሰብአ ሰገልም ሰገዱለት፡፡ አቤቱ ጌታችን ሆይ ፍቅር እንዴት ታላቅ ነው!!! ጌታ ሆይ አሁንም ናፍቆታችን ይህ ነው “በአፍህ መሳንም ሳመን ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና!!!”

No comments:

Post a Comment