Monday, September 24, 2012

መስቀል ለእኛ ኦርቶዶክሳውያን



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
14/01/2005
ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን መካነ ድር የተለቀቀ
መስቀል ለእኛ ኦርቶዶክሳውያን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ አንድምታ አለው፡፡ በመስቀሉ እነሆ አሮጌው ሰዋችንን ሰቅለን ከጐኑ በፈሰሰው ውኃ በጥምቀት በመቅበር አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሰን ተነሥተናል(ኤፌ.422-24)፡፡ 
 በመስቀሉ እርግማናችን ተወግዶ የኃጢአት ስርየትን አግኝተናል፡፡ በመስቀሉ ላይ ከተሰዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በመመገብ ከሚያፈቅረን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፍጹም የሆነ ተዋሕዶን መሥርተናል(ማቴ.2626) እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ የሆንበት ሰማያዊ ማዕዳችን በመስቀሉ ላይ የተሠዋው መሥዋዕት ነው፡፡ (ዮሐ.656) 
በመስቀሉ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በእኛ ላይ ጸንቶ የነበረው የፍርድ ትእዛዝ ተሽሯል፡፡(ቆላ.214) በብሉይ ለሙሴና ለእስራኤል ዘሥጋ እግዚአብሔር አምላክ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ባለችው የቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ  ሆኖ በደመና አምድ ይገለጥላቸው ነበር፡፡(ዘጸአ.339) ቢሆንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የምታገባዋ ጎዳና ተዘግታ ነበር፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ስለ ራሱና ስለሕዝቡ ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳየናል”(ዕብ.96-) ብሎ ተናገረ፡፡


እነሆ እግዚአብሔር በደመና አምድ የሚገለጥበት የሥርየት መክደኛው ወይም የምህረት ዙፋኑ የተባለው የቃል ኪዳኑ ታቦት የመስቀሉ ምሳሌ ነው፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር አምላክ በደመና አምድ የሚገለጥበት ሥፍራ የሥርየት መክደኛ (mercy seat ) የምህረት ዙፋን ይባል እንጂ የጌታ ምህረት ለአዳም ልጆች ገና አልተፈጸመላቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ወጣ ላለው ነገር ጥላ አለውና መስቀሉን ታቦቱ(ዙፋኑ) አድርጎ በእግዚአብሔርና በሰው እንዲሁም በቅዱሳን መላእክትና በሰዎች መካከል የነበረውን የጥል ግርግዳ አፍርሶ እርቅን ከሰው ልጆች ጋር ፈጸመ፡፡ የልዩነት መጋረጃው ተቀደደ መስቀሉንም ዙፋኑ በማድረግ በምህረት ለእኛ ታየ፡፡ (ዕብ.416)ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ይህ ቃል ከዘለዓለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፤ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱ እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያታውቅ ወደደ፤ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው"አለን፡፡(ቆላ.1፡26-28)
በመስቀሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን አገኘን፡፡(ዮሐ.112)  በመስቀሉ የርስቱ ወራሾች ቅዱስ ሕዝብና የመንግሥቱ ካህናት ተባልን፡፡(1ጴጥ.29)  በመስቀሉ አባ አባ የምንልበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበልን፡፡(ሮሜ.815) በመስቀሉ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደሶች ተሰኘን፡፡(1ቆሮ.316) በመስቀሉ አካላችን የሆነውን በጥምቀት የለበስነውን ክርስቶስን የምናገለግልበትን ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎችን ተቀበልን፡፡(ገላ.327 1ቆሮ.124-11) 
እነሆ እኛ አሁን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረታት ተሰኝተናል፤ አገራችንም በሰማያት ነውና እሳትም መንፈስም በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እሳታዊያንና መንፈሳውያን የሆኑትን መላእክትን መስለናቸዋልና፤ ለአዲሱ ተፈጥሮአችን የሚስማማ ሰማያዊ ማዕድ ተዘጋጀልን፡፡(ኤፌ.210 ፊልጵ.320 ማቴ.2231) ማዕዱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ማዕድ ለነፍሳችንም ለሥጋችንም ሕይወትና መድኃኒት ነው፡፡ በመስቀሉ ላይ በተሠዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ከመለኮታዊ ርስት ተካፋዮች ሆንን፡፡ (2ጴጥ.14) ስለዚህም ነው እኛ ኦርቶዶክሳውያን የጌታችን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለሚፈተትበት የመስቀሉ አምሳል ለሆነው  የምህረት ቃል ኪዳን ታቦቱ ልዩ አክብሮትና ፍቅር ያለን፡፡
እኛ ኦርቶዶክሳውያን መስቀሉን ከክርስቶስ ክርስቶስን ከመስቀሉ ነጣጥለን አንመለከትም፡፡ ክርስቶስንም ስናስብ በመስቀሉ ስለእኛ የተቀበለውን መከራ እናስባለን፡፡ መስቀሉንም ስንመለከት እርሱን ዙፋን አድርጎ ባሕርያችንን ያከበረውን ክርስቶስን እንመለከታለን፡፡ መስቀል ማለት ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ወንጌል ማለት ነው፡፡ ከልደቱ እስከ ትንሣኤው መስቀሉን ጠቅሰን እንሰብካለን፡፡ ይህ ነው የመስቀሉ ቃል፡፡ መስቀል ምንድን ነው? ቢሉን ክርስቶስ ስለእኛ ድኅነት ሲል የተሰቀለበት የክብር ዙፋኑ ነው እንላቸዋለን፡፡ ማን ነው እርሱ? ቢሉን የባሪያውን መልክ ይዞ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው እግዚአብሔር ቃል ነው ብለን እንመልስላቸዋለን፡፡ ስለምን በመስቀል ላይ መዋል አስፈለገው? ብለው ቢጠይቁን በአዳም መተላለፍ ምክንያት በእኛ ላይ የተፈረደውን የሞት ፍርድ በሞቱ ሽሮ ሕይወትን ሊሰጠን ስለወደደ እንላቸዋለን፡፡ ሞቶ ቀረ ወይ? ብለው ቢጠይቁን ደግሞሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ ተነሥቶአል”(ሉቃ.245)ብለን እንመልስላቸዋለን፡፡ የመስቀሉ ቃል ለእኛ ኦርቶዶክሳውያን ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው፡፡
ስለዚህም ጌታችን ሆይ እንወድሃለን፤ እናከብርሃለን፤ ከፍ ከፍም እናደርግሃለን ፤ስለእኛ መዳን በመስቀሉ መከራን ተቀብለህ እኛን አክብረኸናልና ፡፡ ምስጋና ይሁን ለአብ እኛን ልጆቹ ያደርገን ዘንድ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮልናልና፡፡ ምስጋና ይሁን ለወልድ የአብ ፈቃድ ፈቃዱ ሆኖ ስለእኛ ራሱን በመስቀሉ ላይ በመሠዋት ከጥፋት አድኖናልና፡፡ ምስጋና ይሁን ለመንፈስ ቅዱስ አካላችንን በመቀደስ የጸጋዎቹ ግምዣ ቤት እንድንሆን አብቅቶናልና፡፡ 

No comments:

Post a Comment