Thursday, November 29, 2012

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ታቦተ ጽዮን



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ኅዳር 20/2004 በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፍ

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል አዝዞአቸው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለመመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል  እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)

ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡ ታቦቷን አራት  ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ አራት ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣  ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም “የምስራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ  እጅግ ያማሩ ናቸው” የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡  እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤል  የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡
የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡  ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡
ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ  ላይ መሆን እንዳለበት  ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ”(ሚል.1፡11) እንዳለው  የስርየት መክደኛው  በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡
የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም “ የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን ፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡” ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡  ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡
ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር ፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡
ቅዱሳን የቤተክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡” (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ “ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡” ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች” በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡
አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ  ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት “ጽዮን” ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡
ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- “እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ አለት አኖራለሁ”(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል  መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ አለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም “እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡”(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን“መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል”(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት  ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን “መድኃኒት” የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ “መልአኩም እንዲህ አላቸው፡-እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ” (ሉቃ.2፡10)በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት “መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል” ሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ “ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች”(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ ስለጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡  ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17) ፡፡ ፍልስጥዬማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)
በዚህ መልክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን መንጎቹዋን ስለቅድስት ድንግል ማርያምና ስለልጁዋ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በእርሱ ስለተሰጠን ሰማያዊ የአገልግሎት ሥርዐት፣ ስለታቦት ጥቅምና  አገልግሎት፤ ታቦተ ጽዮንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር በሰፊው እንደምታስተምር መረዳት እንችላለን ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን!!                           

No comments:

Post a Comment