Wednesday, November 28, 2012

በቤተክርስቲያን የሚታየው የሥላሴ መልክ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/03/2005

እያንዳንዱ ሰው በሦስትነቱ በሚመለከው እግዚአብሔር አርዓያና አምሳል እንደተፈጠረ ቤተክርስቲያን ደግሞ በሥላሴ ውስጥ ባለ ልዩነትና አንድነት አምሳል ልጆችን በመውለዱዋ ሥላሴን ትመስለዋለች፡፡ እግዚአብሔር ምንም በአካልና በግብር ሦስት ብንለውም አንድ እግዚአብሔር ብለን እንደምንጠራውና አካለቱም በየራሳቸው ሕልዋን እንደሆኑ ቤተክርስቲያንም እያንዳንዱ አማኝ ክርስቲያን በአንድ ክርስቶስ አካል አንድ ሲሆን አንዱ ካንዱ የሚለይበት የየራሱ አካል አለው፡፡ እግዚአብሔር በሦስነቱ ሳይነጣጠል በሰው ሰውነት ውስጥ እንዲያድር እንዲሁ የቤተክርስቲያን አባላት የሆኑ ሁሉ አንዱን የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳሉ፡፡ በቤተክርስቲያን ስልጣንና ነጻ ፈቃድን በተመለከተ ምንም ጠብ እንደሌለ ሁሉ ፍጹም አንድነትም አለ፡፡ በቤተክርስቲያን አንዱ ሁሉን ጠቅልሎ መያዝ ፈጽሞ የለም፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ “ቤተክርስቲያን ዓለማቀፋዊት ናት” ሲል ብዙሃን በልዩነታቸው አንድ የሚሆኑበትን በሥላሴ የሚታየውን ታላቅ የሆነውን ምሥጢር ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ሥላሴን የምትመስለው በብዙ መልኩ ነው፡፡ አንደኛው “በልዩነት ውስጥ ባለው አንድነት” ነው፡፡ በሥላሴ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ አካል ራሱን በራሱ የሚያኖር እንደሆነ እንዲሁ በቤተክርስቲያንም እያንዳንዱ ክርስቲያን ራሱን በራሱ የሚያኖር ቤተክርስቲያን ነው፡፡ በሥላሴ አካላት መካከል መበላለጥ እንደሌለ እንዲሁ በክርስቲያኑ ማኅበረሰቡም መካከል ማለትም በሊቀ ጳጳሱና በምዕመኑ መካከል ምንም መበላለጥ የለም፡፡ ማንኛውም በቤተክርስቲያን ሥልጣን ላይ የተሾመ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ክርስቲያን ላይ የገዢነት ሚና የለውም፡፡
 ቤተክርስቲያን ሥላሴን የመምሰሉዋ ምሥጢር እንረዳ ዘንድ የቤተክርስቲያንን የሲኖዶስ ሥርዓት መመልከት ሳይጠቅመን አይቀርም፡፡ በሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ሥላሴን የምትመስለበት መልክ እናያለን፡፡ በሥላሴ ውስጥ የሚታየው ልዩነትና አንድነት በቤተክርስቲያኗ ሲኖድ ላይ በተግባር ይታያል፡፡ በሲኖዶሱ የተሰበሰቡ ሊቃነ ጳጳሳት በየራሳቸው የየራሳቸው አካላትና እኩል የሆነ ሥልጣን  ቢኖራቸውም በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና በነጻነት ወደ አንድ ውሳኔ ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ይበልጥ የተቆራኘው ከክርስቶስ አካል ጋር መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአንዱ የክርስቶስ አካል ክርስቲያኑ አንድ አካል ቢሆንም በአንዱ አካል መንፈስ ቅዱስ በተሰጡት የጸጋ ስጦታዎች እያንዳንዱ ክርስቲያን ልዩ ልዩ የሥራ ድርሻዎች አሉት፡፡ (the orthodox church, page 244) 

No comments:

Post a Comment