Tuesday, November 27, 2012

መስቀሉን ባሰብኩ ቁጥር



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/03/2005
የመስቀሉን ነገር ሳስብ እጅግ ድንቅ ግርምም ይለኛል፡፡ በጥምቀት በዚህ መስቀል ላይ ከክርስቶስ ጋር ተሰቀልን፡፡ በዚሁ መስቀል ላይ እርሱን ለበስነው፡፡ በዚሁ መስቀል ላይ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆን አባ አባ የምንልበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበልን፡፡ ስለዚህ ዲያቆን እስጢፋኖስ ክርስቶስን መስሎ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ ጸለየ፡፡ በመስቀሉ ገነት ወደ ተባለው ክርስቶስ ገባን፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አማናዊው ዕፀ ሕይወት ወደ ተባለው ጎኑ በመቅረብ  ከፈሰሰው ክቡር ደሙ ጠጣን፤ መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበው ሥጋውም በልተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን አገኘንበት፡፡
 ትንሣኤአችንም የሚፈጸመው በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡(ዮሐ.6፡54) በዚህም ወደ መንግሥቱ ለዘለዓለም እንኖር ዘንድ ገባን፡፡ ቢሆንም አሁን ወደ መንግሥቱ መግባታችን ላይታወቀን ይችላል አልተገለጠምና፡፡ ሲገለጥ ግን ሕይወታችን ከእርሱ ጋር እንደሆነች እናስተውላለን፡፡(2ቆላ.3፡3) በተጠመቅንና ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ በበላን ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደተነሣን ያኔ እንረዳለን፡፡ ሕይወታችን እርሱ አብ ነው፣ ሕይወታችን እርሱ ክርስቶስ ነው፣ ሕይወታችን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡እርሱን እኛ ስናመልከው እርሱ ደግሞ በእኛ ላይ ያድራል፡፡(ራእ.7፡15)

በመስቀሉ የእኛ መገኛ ከሆኑት አዳምና ሔዋን ጋር እንገናኛለን፡፡ ምን ይመስሉ ይሆን? እርሱን በትንሣኤ ወይም በዚህ ምድር እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በቅድስና በቅተን ስንገኝ እንረዳዋለን፡፡ በመስቀሉ ከአእላፍት መላእክት፣ ከኖህ፣ ከሄኖክ፣ ከአብርሃም፣ ከሙሴ፣ ከኤልያስ፣ ከነቢዩ ኢሳይያስና ከኤርምያስ፣ ከንጉሥ ዳዊት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከሐዋርያት፣ ከእስጢፋኖስ፣ ከፊልጶስ፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከጢሞቴዎስና የክርስቶስ ቤተሰብ ከሆኑት ሁሉ ጋር አንድ ቤተሰብ ሆነን ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ በመስቀሉ ተወልደው ወደ ቅዱሳን ኅብረት የሚደምሩትን እንኳን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በፍጹም ደኅንነት መጣችሁ ብለን እንቀበላቸዋለን፡፡ እንዲህም እንላቸዋለን፡- እነሆ አባታችሁ እናንተን ከማፍቀሩ የተነሣ እጅግ ክቡር የሆነውን ሰውነቱን ማዕድ አድርጎ አቀረበላችሁ፡፡ የክብሩን ብርሃን ለብሳችሁ እንድትኖሩም ራሱን ልብስ አድርጎ ሰጣችሁ፡፡ በእርሱ አማልክት ትሰኙ ዘንድ የአካሉ ሕዋሳት አደረጋችሁ፡፡ ፍጹም ዘለዓለማዊያን እንድትሆኑም መንፈስ ቅዱስን በነፍሳችሁ ቦታ ነፍስ አድርጎ ሰጣችሁ፡፡ ሞትንም እንዳትሰቀቁ ምንም ሥጋችሁን ቢገድሉ በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ሆናችሁ ትኖሩ ዘንድ የርሱን ማኅተብ በግምባራችሁ አተመ፡፡ በትንሣኤም የሚያስነሣችሁ እርሱም ነው፡፡ በሥራ አብም ወልድም መንፈስ ቅዱስም አንድ ናቸውና አእነንለላቸወዋለነን፡፡ እንዲህም ብለን ፍጹም በሚያጽናና ቃል እንናገራቸዋለን፡፡ ማጽናናታችንም እውነት ነው፡፡ በእኛ ተፈጽሞ አይተነዋልና፡፡ ይህ ሁሉ ግን በመስቀሉ ላይ የተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሎ ተቀኘ፡-

“ንጉሥ ሰሎሞን መሸከሚያውን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ፡፡ ምሰሶዎቹን የብር መደገፊያዎቹን የወርቅ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ ውስጡም በኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው፡፡ እናንተ የጽዮን ቆነጃጅት ውጡ እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ፡፡”(ማኃ.3፡9-10)
ንጉሥ ሰሎሞን የተመሰለው በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መሸከሚያውም የተባለው መስቀሉ ነው፡፡ ምሰሶውና መቀመጫው የተበላው የመስቀሉ የመሃለኛው ክፍል ነው፡፡ መደገፊያዎቹ የተባሉትም በግራና በቀኝ ያሉት የመስቀሉ ክፍል ነው፡፡ ብሩ ቃሉ ነው፤ ወርቁም ንግሥናው ነው፤ ሐምራዊውም ግምጃ የተባለውም የገዛ ደሙ ነው፡፡ ደሙ ሰውነቱን ሁሉ ከድኖት ነበርና(ዘፍ.49፡11) በመስቀሉ ውስጥ ያሉትና ለእርሱ ለክርስቶስ የታጩት ቆነጃጅቶችም ከአዳም እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሡ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ እናንተ በእርሱ የድንግል ማርያም ልጆች የተሰኛችሁ ውጡ፡፡ እናቱ የዓለሙ ቤዛ ይሆን ዘንድ የወለደችውን ንጉሥ ክርስቶስን ተመልከቱ፡፡ ራሱን ፍሪዳ አድርጎ በመስቀሉ ካቀረበው ከንጉሥ ክርስቶስ ሠርግ ተገኝታችሁ ከማዕዱ ተካፈሉ፡፡ ከሥጋው በልታችሁ ከደሙም ጠጥታችሁ ትድኑ ዘንድ ይህቺ ለእርሱ የልቡ ደስታ ቀን ናትና፡፡(ኢሳ.53፡11)በዚያም የሾኽ አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ክርስቶስን ታዩታላችሁ፡፡  ኦ ኦ  ኦ ጌታዬ ሆይ ፍቅርህ እንዴት እጅግ ግሩም ነው፡፡ ይህን ባሰብኩ ጊዜ እንባዬ በጉንጮቼ ላይ መንታ ሆኖ  ኩልል ብሎ ይወርዳል፤ ጌታ ሆይ ፍቅርህ እንዴት ጥልቅ ነው!!!! 
    

1 comment: