Thursday, November 29, 2012

በድንግል ማርያም እናትነት ወንድምነትና እኅትነት ለእኛም



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/03/2005

አንዳንዶች ባይረዱት ነው እንጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ለምድራዊቱ ቤተክርስቲያን ወይም ቤተክርስቲያን ለተሰኘነው ለእኛ አብነት የሆነች አማናዊቱ ቤተክርስቲያን ናት፡፡እኛም በእርሱዋ ተመስለን ለክርስቶስ ሙሽሪትም፣ እናቱም፣ ወንድምና እኅቱም፣ አገልጋዩም፣ ልጁም ተብለናል፡፡(ማቴ.12፡50) በእርሱዋም ለጌታ የታጨን እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም አገልጋዮችና ልጆች ስለሆንን ጠላት ዲያብሎስ ሁሌም ያሳድደናል፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለክርስቶስ እንዲሁ ናት፡፡እርሱዋ ለእርሱ እናቱ ብቻ አልነበረችም ሰውነቱዋን ለእርሱ ማደሪያነት ያጭች እኅቱም፣ አገልጋዩም፣ ልጁም ነበረች፡፡ እርሱዋ የቤተክርስቲያን አማናይቱ ምሳሌ ናት፡፡ እኛም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተሰኝተናል፡፡ ስለዚህም ሰይጣን “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘሩዋና በዘርህ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ”(ዘፍ.3፡15) የሚለው ቃል በእኛ ላይም ተፈጽሞ ጠላት ዲያብሎስ ዘምቶብናል፡፡



እግዚአብሔር ቃል አስቀድሞም ለእናትነት እርሱዋን መምረጡ ስለንጽሕናዋና ስለቅድስናዋ እንዲሁም እግዚአብሔርን ከነፍሱዋ ስለመውደዱዋ ነበር፡፡ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሐሴትን ታደርጋለች” የሚለው ቃሉዋም የሚያስረዳው ስለእርሱዋ መመረጥ ምሥጢር ነው፡፡ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን”(ዮሐ.14፡23) እንዲል ጌታዋን መውደዷ በተግባር የተገለጠ ስለነበረ እግዚአብሔር ቃል እናቱ ትሆን ዘንድ ከሴቶች ሁሉ መረጣት፡፡ እኛም በምግባር እንደ እርሱዋ ደስ ብናሰኘው ለእርሱ እናቱ፣ ወንድሞቹና እኅቶቹ እንሆናለን፡፡ የእርሱዋ ግን በተግባር የታየና አምላክን በመውለድ የተገለጠ ነው፡፡ ልዩነቱም እዚህ ላይ ነው ይህም ፈጽሞ የማይነጻጸር ነው፡፡
 በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ውስጥ እርስዋን እንመለከታታለን፡፡ በሥጋ ከእርስዋ ብቻ ተወልዶአልና የጌታችን መልክ የእርስዋን መልክ ይመስላል፡፡ ስለዚህም በእርሱ መልክ ውስጥ እርሱዋን እንመለከታታለን፡፡ እርሱዋን የሚቃወሙ በጌታ መልክ ውስጥ የእርስዋን መልክ ሲመለከቱ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ወይስ በዚህ ምክንያት ከእርሱ ይሸሻሉ? ነገር ግን ጌታችን የእርሱዋ እግዚአብሔርን መውደድ፣ ቅድስና፣ ንጽሕና፣ እምነትና በእምነት መታዘዝ ሁሌም ተገልጦ እንዲኖር በእርሱ መልክ ውስጥ እርሱዋን እንድናያት አደረገን፡፡  
ወገኖች ሆይ እስቲ አስተውሉ የክርስቶስ ቅድመ አያቶች የተባሉትን ሁሉ ተመልከቶአቸው፤ ሁሉም አምላክ የወደደላቸው አንዳች በጎ ነገር ነበራቸው፡፡ እነዚህ የክርስቶስ አያቶች ሁሉ ወይ እምነታቸው ወይም ምግባራቸው ጌታን ደስ አሰኝቶት ነበር፡፡ ስለዚህም አያቶቹ ይሆኑ ዘንድ ፈቀደ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ሁሉን አሟልታና አካታ ስለተገኘች ከእስራኤል ደናግላን ሁሉ እርሷን ለእናትነት መረጣት፡፡ እርሷ ለመዳናችን በፈቃደኝነቷና በእምነቱዋ የራሱዋ የሆነ ተሳትፎ ያላት እናትም ድንግልም ናት፡፡ ብዙዎች ግን በዚህች ቅድስት የአምላክ እናት ላይ አፋቸውን ሲያንቀሳቅሱ ይታያሉ ለምን እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ጥፋቱዋስ ምንድን ነው? ወይስ የመዳናችን ምክንያት ስለሆነች ይህን እውነት እንደ እስላሙ ወይም እንደ አይሁድ ስላልተቀበሉት ይሆን? ይህ እጅግ በጣም የሚገርመኝና የሚደንቀኝ ጉዳይ ነው!!!ቢሆንም ለሁሉም ይህ ምሥጢር እንዲገለጥላቸው ምኞቴ ነው፡፡ 

1 comment:

  1. በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ውስጥ እርስዋን እንመለከታታለን፡፡ በሥጋ ከእርስዋ ብቻ ተወልዶአልና የጌታችን መልክ የእርስዋን መልክ ይመስላል፡፡ ስለዚህም በእርሱ መልክ ውስጥ እርሱዋን እንመለከታታለን፡፡ እርሱዋን የሚቃወሙ በጌታ መልክ ውስጥ የእርስዋን መልክ ሲመለከቱ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ወይስ በዚህ ምክንያት ከእርሱ ይሸሻሉ? ነገር ግን ጌታችን የእርሱዋ እግዚአብሔርን መውደድ፣ ቅድስና፣ ንጽሕና፣ እምነትና በእምነት መታዘዝ ሁሌም ተገልጦ እንዲኖር በእርሱ መልክ ውስጥ እርሱዋን እንድናያት አደረገን፡፡

    ReplyDelete