ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
4/11/2009
መቼም ስለ ዕድሜ ሲነገር ቆጠራው ከጽንሰት ከተጀመረ እንደ ጻድቁ ኢዮብ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል”(ኢዮ.14፡1) ማለታችን ግድ ነው፡፡ ከጽንሰት የምንጀምራት ዕድሜአችን እንደ ጠዋት ጤዛ ወይም እንደ ሳር አበባ ናት፡፡ ባንድ ቀን ለምልማ በአንድ ቀን የምትረግፍ አበባ ማለት ይህቺ ምድራዊዋ ዘመናችን ናት፡፡ ቢሆንም ዋጋ ያላትም ይህቺው ዕድሜአችን ናት፡፡ በዚህች ዕድሜአችን በሰውነት ሕዋሳቶቻችን ሁሉ መልካምን ካልሠራንባቸው ዕዳዋ ዘለዓለማዊ ሆኖ ይሠፈርብናል፡፡ ከሠራን ደግሞ የተጠቀጠቀና የተጨቆነ ብድራትን ከአምላክ ዘንድ እናገኝባታለን፡፡ ግን ደግሞ ዕድሜአችንን በአምላክ ሕሊና ከመታሰባችን ጊዜ አንስቶ እንደ ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ… ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ”(መዝ.138፡16) ብለን የቆጠርን እንደሆነ ዕድሜአችን የትናለሌ ሊሆን ነው፡፡ ከመቼ ጀምሮ በአምላክ ሕሊና እንደታሰብን በጭራሽ አናውቀውም ግን ደግሞ አምላክ እንደ ሰው አያስብምና መነሻ አለው ማለት አይቻለንም፡፡ እርሱ ያሰበው ከዘለዓለም ያሰበው ነው፤ እንዲያስብ ምክንያቶች አያስፈልጉትም፡፡ የማያውቀው ወደፊት የሚያውቀው ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ ዕድሜአችንን በእግዚአብሔር ሕሊና ከመታሰባችን አንስቶ ከቆጠርነው ሳንወለድም በፊት አረጋውያን ነን ምክንያቱም ሳይሠራን በሕሊናው ነበርን ሳንፈጠርም ቀኖቻቸችን በእርሱ ሕሊና የታወቁ ናቸውና፡፡
አደራ ግን ይህ ቃል ስለ ዳዊት ብቻ የተነገረ ነው እንዳትሉኝ ምክንያቱም አምላክ ሳያስበው የሚፈጥረው ነገር የለምና፡፡ አይደለም እርሱ እኛ እንኳ ያላሰብነውን አንተገብርም፡፡ በሕሊናችን የጨረስነውን በተግባር እንፈጽመዋለን፡፡ ስለዚህ ቃሉ ያለጥርጥር ለዳዊት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ለእኛም ይሠራል፡፡ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ዕድሜአችን ስንት ነው? እንጃ እርሱ እግዚአብሔር ያውቀዋል እኛ ልናውቅ የምንችለው ቢኖር በሥጋ ተጸንሰን በዚህ ምድር የተመላለስንባትን ዕድሜ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ዕድሜ የለም ከዚያም በኋላ በትንሣኤ ዕድሜ አይኖርም፡፡ ከእነዚህ አንጻር በሥጋ የምንኖርባት ይህቺ ዕድሜ ስትሰላ እንደ ጠዋት ጤዛ ጠዋት ታይታ ፀሐይ ሲተኩስ የምትጠፋ ወይም እንደ ምድር አበባ በአንድ ቀን አብባ በአንድ ቀን የምትከስም እንደሆነች እንረዳለን፡፡
ቢሆንም ግን በእርሱ ሕሊና ውስጥ ሳለን ምንም ዘመነ ዘመናትን የኖርን ቢሆንም ኃጢአትን አናውቃትም ነበር፡፡ በዚህች ምድር ከወላጆቻችን ተጸንሰን ክፉና ደጉን ካወቅንባት ጊዜ አንስቶ ግን ለጽድቅ ሳይሆን ለኃጠአት የሚያዘነብል ጠባይ ተላብሰን ስላለን መበደላችን መቼም የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ይህች ግን በመኃሪነቱ ታምነን እኛም ወደን ፈቅደን ሳይሆን ከእውቀት ጉድለትና ደካሞች ከመሆናችን የተነሣ የፈጸምናቸውና ስለመተላለፋችን ንስሐ የገባን እንደሆነ ዘለዓለማዊ ዕረፍታችን አትጓደልብንም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳውም እንደ ሥራችን ቀሪው ዘመናችን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በዚህ ዘለዓለማዊነት ውስጥ ግን ዘለዓለማዊ ኩነኔ ወይም ዘለዓለማዊ ሕይወት አለ፡፡ ይህ ማሰቡ በራሱ እጅጉን ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም ተግባራችንን እናውቀዋለንና፡፡
ቢሆንም ግን በእርሱ ሕሊና ውስጥ ሳለን ምንም ዘመነ ዘመናትን የኖርን ቢሆንም ኃጢአትን አናውቃትም ነበር፡፡ በዚህች ምድር ከወላጆቻችን ተጸንሰን ክፉና ደጉን ካወቅንባት ጊዜ አንስቶ ግን ለጽድቅ ሳይሆን ለኃጠአት የሚያዘነብል ጠባይ ተላብሰን ስላለን መበደላችን መቼም የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ይህች ግን በመኃሪነቱ ታምነን እኛም ወደን ፈቅደን ሳይሆን ከእውቀት ጉድለትና ደካሞች ከመሆናችን የተነሣ የፈጸምናቸውና ስለመተላለፋችን ንስሐ የገባን እንደሆነ ዘለዓለማዊ ዕረፍታችን አትጓደልብንም፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳውም እንደ ሥራችን ቀሪው ዘመናችን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በዚህ ዘለዓለማዊነት ውስጥ ግን ዘለዓለማዊ ኩነኔ ወይም ዘለዓለማዊ ሕይወት አለ፡፡ ይህ ማሰቡ በራሱ እጅጉን ያስፈራል፡፡ ምክንያቱም ተግባራችንን እናውቀዋለንና፡፡
እናም ወዳጆቼ እርጅና የሥጋ አንዱ ባሕርይ ቢሆንም ወደ እግዚአብሔር መጠሪያ ዕድሜአችንን እንደ እርጅና ከወሰድነው ከማኅጸን ካለ ሽል በዕድሜ እስከሸበተው ድረስ አረጋዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሞትን ከጽንሰት ጀምረን ነውና ተሸክመናት የምንዞረው፡፡ ጌታችንም የመምጫውን ጊዜ በሦስት ወቅታት ከፋፍሎ አስተምሮናል፡፡ እነዚህ ፍሬ አፍርተን እንደሆነ ሊጎበኘን የሚመጣባቸው ወቅታት ሲሆኑ በእነዚህ ወቅታት ፍሬ አፈራንም አላፈራንም ልንቆረጥ የምንጎበኝበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን በጠባቂ መላእክቶቻችን ምልጃና በእርሱ ቸርነት ብዙ ጊዜ እንተርፋለን፡፡(ሉቃ.13፡8)
ሞት እንደ ሌባ ስለሚመጣ መች በአምላክ ፊት ለፍርድ እንደምንቆም አናውቅም፡፡ኢዮብ እንደ ምንደኛ ዕድሜአችን የተሰፈረች የተለካች እንደሆነ ይነግረናል፡፡(ኢዮ.14፡5-6) ከሁሉ በላይ ደግሞ እየኖርንባት ያለችዋን ቀን እንጂ መጪዋ ቀን ለእኛ የምትሰጥ በእኛ እጅ ያልሆነች መሆኗ እርጅናችን እንደኖርባት ቀን መጠን እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡
በእርግጥ ሰው ዕድሜው በጨመረ ቁጥር ሞትን ማሰቡ እየጨመረ እንደሚመጣ ይታወቃል፡፡ እርጅናው እንደ በሽታ ሲሆንበትና ሰውነቱን የሞትን ሽታ ማሽተት ሲጀመር ደግሞ ይበልጥ በሞት ሥጋት ውስጥ ይወድቃል፡፡ ብልህ ሰው ግን ሁሌም ሞትን ከፊቱ አስቀምጦ ለዚህ ዓለም ፈቃድ በመሞት በትንሣኤ ባገኘው ሕይወት ውስጥ በመኖር የአምላክን መምጫ ቀን እያሰብ በጥንቃቄ ይመላለሳል፡፡ ይህ ሰው ሕሊናውንና አካሉን ከክፋት ለመጠበቅ የሚጋደል ነው፡፡ ዘወትርም በሕጉ መመላለሱን እየመረመረ ይጓዛል በፍርሃትም ሆኖ በአምላክ ፊት ለጸሎት ይቆማል፡፡ ይህ ሰው ነው እንግዲህ በትክከለኛው ትርጉም አረጋዊ የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ነገ የእርሱ እንዳልሆነች ከአምላክ በስጦታ የሚያገኛት መሆኑን ስለተረዳና መች ወደ አምላኩ እንደሚወሰድ ስለማያውቅ በመጠንቀቅ ስለሚመላለስ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ወዳጆቼ ዕድሜ አንድም ለንስሐ አንድም “የዋኀን ብፁዓን ናቸው ምድርን ይወርሳሉና” እንዲል ለበረከት የሚሰጥ ቢሆንም መቼም መች ለዚህች ዓለም ስደተኞች እንደሆንን ልናስብ፣ ባልጠበቅናት ሰዓት አንድ ወቅት በሞት ልንጠራ እንደምንችል አስበን በጥንቃቄ እንጓዝ፣ ምክንያቱም ምርኩዝ አንጨብጥ እንጂ ሞትን ሁሌም ተሸክመናት የምንዞር አረጋውያን ነንና፡፡ ቢሆንም ግን ነግ በእኔ ነውና ትውልድ እንዲቀጥል ፍቅርን ለግሰው ያሳደጉንን አረጋውያንን ልናስባቸው፣ የሚገባቸውን ክብር ልንሰጣቸውና የሚያስፈልጋቸውን ልናሟላላቸው ይገባናል፡፡ ያለበለዚያ ሁሉም የዘራውን ነውና የምናጭደው ክፉን እንደዘራን በዚህም ምድር ሆነ በሚመጣውም በሠራነው ልክ ተሰፍሮ ይከፈለናል፡፡ ነገር ግን ነግ በኔ ብለን ለአረጋውያን ተገቢውን ሁሉ በአቅማችንና እንደ ችሎታችን ብናደርግ በነፍስም በሥጋም ተጠቃሚዎቹ እኛው እንሆናለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የተጠቀጠቀና ስፍሩ የሞላ በረከትን በዚህም ዓለምም በሚመጣውም ዓለም ይሰጠናል፡፡ አምላክ እርሱን ማሰብን ፈቃዱን መፈጸምንን ይስጠን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment