እንደ ጢሞቴዎስ ከልጅነት ጀምሮ ከቅዱሳን መጻሕፍትና ከመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም ከትርምት ሕይወት ስለእግዚአብሔር የተማረ፤ የልቡናውን ደጅ በመዝጋት ከሕግ መምህር ትምህርቱን የቀዳ ክርስቲያን ለእርሱ ከትዳር ሕይወት ይልቅ የድንግልና ሕይወት እንዴት የተመረጠ ሕይወት አይሆነው? ይህ ሰው ማዕረጉ ከመላእክት ወገን ነውና የሥጋ ፍትወት የራቀለት በትንሣኤ ሕይወት የሚኖር እግዚአብሔር ሳይመርጥ ኃጥኡንም ጻድቁንም እንዲወድ ሁሉን የሚወድ በአንዲት ብላቴና ፍቅር ታሥሮ እርሱዋን አስቀድሞ ሌላውን አስከትሎ መውደድ የማይቻለው፣ እንደ አምላኩ ሁሉን አስተካክሎ የሚወድ በትዳር ውስጥ ያሉቱ ጥንዶች በትንሣኤ የሚያገኙት ሙሉዕ የሆነ ፍቅር አግኝቶ የሚኖር ሰው ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሕይወት “ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፡- እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው”(1ቆሮ.7፡8) ብሎ ጻፈልን፡፡ ይህ ሕይወት በተባሕቶ ወይም በትርምት ሕይወት ውስጥ የሚያገኙት ሕይወት ነው፡፡ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያለ ሰው ግን ይህን ፍቅር የሚማረው በትዳር ውስጥ ነው፡፡ በድንግልና ሕይወት ውስጥ ያለ ሰው ይህን ፍቅር ላለመማር እንቅፋት የሚሆነው እርሱ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር የማይለወጥ ሁሌም በባሕርይው ውስጥ የሚገኝ አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በትዳር ሕይወት ውስጥ ከትዳር ተጋሪው ጀምሮ በማኅበራዊው ሕይወት በሚገጥሙት ፈተናዎች በትንሣኤ ወደምናጣጥማት ፍቅር እንዳያድግ እንቅፋት ሊሆኑበት ወይም ጉዞውን ሊያረዝሙበት ይችላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በተባሕቶ ሕይወት ውስጥ ያለ ክርስቲያን ከራሱ ጥረት ውጪ በዙሪያው ሌሎች እንቅፋቶች የሉበትም፡፡ በእርግጥ በደቂቃ ውስጥ የሚያልፍ የሥጋ ፍትወት እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ “በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ፡፡”(1ቆሮ.7፡9) ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ ግን ይህ የሚሆነው ልቡና በእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ካለመሆን የተነሣ ነው፡፡ በሕሊና ያልታሰበ ወይም ሕሊና ያላመነበትን ቀሪው አካል አይተገብርም፡፡ ሰው ስለአንድ ነገር ሃሳቡ ከሌለው ፈቃዱም ምኞቱም አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች መራቅ ብልህነት ነው፡፡ ለምሳሌ ጊዜን ዋዛ ፈዛዛ በሆነ ነገር ማሳለፍ ከጸሎት ሕይወት መራቅ አብዝቶ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መገኘት እና ይህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡
ነፍስን በእጅጉ ደስ የሚያሰኛትና እረፍት የሚሰጣት ሕይወት ቢኖር ይህ የትርምት ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ በዝምታ ከአምላኳ ዘንድ እንደ ውኃ ጅረት በዝቶ የሚፈሰውን ቃሉን በጸጥታ ውስጥ ሆና ትሰማለች፡፡ በዚያን ጊዜ መላእክት ትዝ አይሏትም፤ ሁለመናዋ በአምላክ የእውቀት ብርሃን ብሩህ ስለሚሆን የረቀቁት ገዝፈው የራቁት ቀርበው የተሰወሩት ተገልጠው ይታዩአታል፡፡ ከእርሷ ዘንድ የተሠወረ በላይ በሰማይ በታች በምድር አንዳችም ነገር አይኖሩም፡፡ መላእከት ረቂቅነታቸው ያከትማል፤ ሰዎችም በዚህች ነፍስ የሚነበቡ ድንቅ የአምላክ መልእክታት የሰፈሩባቸው ሰሌዳዎች ሆነው ታገኛቸዋለች፡፡ ይህች ነፍስ ከአምላኳ ዘንድ መማር ብቻ ሳይሆን ከፍቅሩም ስለምትመገብ በፍቅሩ ተማርካ ሥጋዋን ፈጽማ ትዘነጋታለች፡፡ በእውነት በትክክለኛው መንገድ በዚህ ተመስጦ ውስጥ በመገኘት ከአምላክ ጋር ፊት ለፊት የተገናኙ ነፍሳት ብሩካን ናቸው፡፡
የሚደንቀው ግን በግርግዳ ውስጥ እንኳ ማለፍ የማይሳናትና ግዙፉ ዓለም ወስኖ የማይዛት ነፍስ በግዙፏ ሥጋ ተወስና አመለካከቷም በእርሷ ፈቃድ ተሸብቦ መኖሩ ነው፡፡ ይህ በእውነቱ የሚያሳዝን ነው፡፡ ራስ ሆና ሥጋን መምራት የሚገባት ነፍስ ለሥጋ ፈቃድ ባሪያ ሆና ማስተዋልዋ ተቀምቶ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
ጊዜአት ሁሉ የእግዚአብሔር ናቸው፡፡ ለእኛ ተሰጠችን የምንላት ጊዜ ብትኖር እንኖርባት ዘንድ ከአምላክ የተፈቀደችልን የአሁኗ ጊዜ ብቻ ናት፡፡ ጊዜ በእርሱ ተሰፍራ የምትሰጥ እንጂ አንዴ የተሰጠችን አይደለችም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በስፍር ለክቶ በሰጠን ጊዜ የሥጋን ፈቃድ እየፈጸሙ ባክኖ መኖር ለነፍስ ስቃይ ነው፡፡ ሰው ግን ይህን አልተረዳም፡፡ በነፍሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሰው ከዚህ የተነሣ ነፍሱ በመብሰልሰል በቁጭት በንዴት ተሞልታ ትኖራለች፡፡ ምክንያቱም በሥጋ እስራት ምክንያት ነፍስ ከአምላኳ ጋር ሳትገናኝ ስለምትኖር ነው፡፡ይህቺ ነፍስ ከአምላኳ የምታገኘውን ታውቀዋለች ግን አትደርስበትም ትረዳዋለች ግን አትኖርበትም፡፡ ይህ ታዲያ እንደ ነዌና አልዓዛር መሆን አይደለምን? ወይም በሲኦል ሆድ ውስጥ እንደነበሩት የአምላክን ሥጋ መሆን እንደሚጠባበቁ ነፍሳት አልሆነምን? በሥጋ ፈቃድ የተሸበበች ነፍስ በሲኦል ውስጥ እንዳለች ነፍስ ናት፡፡ ሥጋን ገርታ የምትኖር ነፍስ ግን ሥጋ ለእርሷ አምላኳን የምታመልክበት ቤተ መቅደሷ ትሆንላታለች፡፡ ጊዜው ግን አሁን ነው፡፡ መጪው ጊዜ የእኛ ሳትሆን እርሱ ሲሰጠን የምናገኛት ናት፡፡ ይህንን ሕይወት ሕይወታችሁ አድርጋችሁ የምትኖሩ ቅዱሳን ሆይ ይህንን ሕይወት እኛም እንኖረው ዘንድ ለምኑልን!!!
ቃለ ሕይወት ያሰማልን። እባክዎት ሌሎች ጽሁፎችንም በተሻለ ፍጥነት ይለጥፉልን።
ReplyDeleteእሺ ወዳጄ በተቻለኝ ፍጥነት ለማድረስ እሞክራለሁ።
ReplyDelete