ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/11/2004
ቅዱስ ኤፍሬም በዚህ ቅኔያዊ ድርሰቱ ኖህ ከጥፋት ውኃ የዳነባትን መርከብ በቤተክርስቲያንና
በመስቀሉ እንዲሁም በእምነት መስሎ ድንቅ በሆነ መልኩ አቅርቦት እንመለከታለን፡፡
የኖህ ተምሳሌትነት በዘመኑ ከነበሩት ሕዝቦች
ጋር ሲነጻጸር እንዴት ታላቅ ነበር፤ንጽሕናን እንደጥሩር ከለበሰው ኖህ ጋር በፍትሕ ሚዛን ሲመዘኑ እንደማይጠቅሙ እንደማይረቡ ሆነው
ተቆጠሩ፡፡ፈጽሞ የማይነጻጸሩ ነበሩና በጥፋት ውኃው ሥር ዘቅጠው ቀሩ፡፡የኖህን ንጽሕና ከፍታ ለማሳየትም
ኖህ በመርከብ ሆኖ ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለ፡፡ በኖህ ንጽሕና ደስ ለተሰኘህ ለአንተ ለእግዚብሔር ክብር ይሁን፤ ለገዢነትህም ምስጋና
ይገባል፡፡
ኖህ ከጥፋት ውኃ በፊትና ከጥፋት ውኃው በኋላ ተምሳሌትነቱ ቀጥሎ ነበር፤ ያለፈው ዳግም እንዳይመለስ እንደታተመ፤
አዲስ የሆነ ሕይወትም እንደተሰጠን ጥላ ሆነን፡፡ እርሱ ለሁለቱ ትውልዶች እንደምሳሌ ነው፤ ያለፈው እንደተቋጨ፤ መጪውም ሕይወት
እንደ ተዘጋጀ እንደ ጥላ ነበር፡፡ እርሱ አሮጌውን ትውልድ ሲቀብረው፤ ለአዲሱ ትውልድ መጋቢ ሆነ፤
እርሱን ለዚህ ታላቅ ክብር ለመረጠው ፈጣሪ ምስጋና ይሁን፡፡
የሁሉ ጌታ ያነፃት መርከብ ከጥፋት ውኃው በላይ ከፍ ከፍ በማለት ተነሳፈፈች፤ ከምሥራቅ ተነቀሳቅሳ ከምዕራብ አረፈች፤
ከደቡብም ተንቀሳቅሳ ሰሜንን በጉዞዋ ዳሰሰችው፤ለምድሪቱ ትንቢትን እየተናገረች በውኃይቱ ላይ ቀዘፈች፤ አዲሱ ትውልድ እንዴት እንደሚፈጠር
እየሰበከች ሀገራትን ሁሉ እያካለለች ዞረች፤ ኖህን ከጥፋት ላዳነው ጌታ ምስጋና ይሁን፡፡
መርከቢቱ በዙረቱዋ የእግዚአብሔር አዳኝነት ሰበከች፤ በውኃ ላይ ቤተክርስቲያንን ሊመሠርት የመጣው በመስቀል ለተመሰለችው
መርከብ መሪ ነበር፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤በዚች መርከብ የተጠለሉትን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከጥፋት አዳናቸው፤በርግቢቱ
ምትክ መንፈስ ቅዱስ በእርሱዋ የከበሩትን አገለገላቸው፤ የክርስቶስን የማዳን ሥራ አከናወነው፤
ለአዳነን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡
የእርሱ ምሳሌ በኦሪት ሕግ ውስጥ ነበር፤ የእርሱ ጥላ በመርከቢቱ ላይ ነበር፤ አንዱ ለአንዱ አስረጂ ይሆናል፤ መርከቢቱ
ከጥፋት ውኃ በኋላ ባዶ እንደነበረች፣ ለክርስቶስ የተመሰሉት ምሳሌዎች በእርሱ መምጣት ፍጻሜ በማግኘታቸው በአማናዊው ተተካ፤መርከቢቱም
የእርሱ ለሆነች ቤተክርስቲያን ምሳሌነቷ እውን ሆነ፤ አምላክ ሆይ ለእኛን ለማዳን ስትል ወደዚህ ዓለም መምጣትህ የተመሰገነ ይሁን፡፡
ሕሊናዬ በአዳኛችን የማዳኑ ኃይል ውቅያኖስ ውስጥ በመስጠምዋ በአድንቆት ተሞላች፤ በጥፋት ውኃው ላይ በመርከቡ የተንሳፈፈ
ተመስጦው ያልተወሰደበት ኖህ ብሩክ ነው፤ጌታ ሆይ ለእኔም እምነቴ እንደ መርከብ ትሁነኝ የኃጢአትን ባሕርን ቀዝፋ ታሻግረኝ ፤ሰነፎች
ግን በአንተ ላይ በማፌዛቸው ሰምጠው ወደጥልቁ ወረዱ፤ አንተን ለወለደህ ለባሕርይ አባትህ ምስጋና ይሁን !!
ሕሊናዬ በአዳኛችን የማዳኑ ኃይል ውቅያኖስ ውስጥ በመስጠምዋ በአድንቆት ተሞላች፤ በጥፋት ውኃው ላይ በመርከቡ የተንሳፈፈ ተመስጦው ያልተወሰደበት ኖህ ብሩክ ነው፤ጌታ ሆይ ለእኔም እምነቴ እንደ መርከብ ትሁነኝ የኃጢአትን ባሕርን ቀዝፋ ታሻግረኝ ፤ሰነፎች ግን በአንተ ላይ በማፌዛቸው ሰምጠው ወደጥልቁ ወረዱ፤ አንተን ለወለደህ ለባሕርይ አባትህ ምስጋና ይሁን !!
ReplyDelete