Wednesday, February 27, 2013

የዛሬ ገጠመኜ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/06/2005
ዛሬ አንድ የገጠመኝን ገጠመኝ ላውጋችሁ እንዲህ ነው፡- አንድ የልብ ወዳጄለሆነ ጉዳይ እፈልግሃለሁብሎ ወደ እርሱ በታክሲ አመራሁ የሥራ ቦታው ወደ መስቀል ፍራዎል አካባቢ ነበር፡፡ ሄድኩ በፍቅር ተወያየን ለእኔ ጥሩ አሳቢ ነበርና በእርሱ አምላኬን አመሰገንኹት፡፡ ከእርሱ ጋር ውይይቴን ከጨረስኩ በኋላ ከአምባሳደር ዐራት ኪሎ የሚለውን ታክሲ ይዤ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡
በመንገድ ላይ ሳለሁ ግን አንድ ወዳጄ ከክፍለሀገር ደወለልኝ፡፡ ስለ ግል ጉዳያችን ከተጠያየቅን በኋላ ወደ መጨረሻ ላይ ለመሆኑየአብርሃም ርስት ርስታችንየሚለውን ምንባብ ተመለከትከውን? አልኩት ተመልከቼዋለሁ ግን ካነበብኩት ስለቆየሁ እስቲ ትን አስታውሰኝ አለኝ፡፡ እኔምለአብርሃም በራሱ ምሎ በመሐላ መካከል የገባውና በሞቱ ርስቱን ለአብርሃምና የአብርሃምን እምነት ይዘው ላሉት ሊያወርስ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ራሱን ስለሰዋው እግዚአብሔር ቃል የሚያትት ነው” ብዬ አስታወስኩት፡፡ እርሱም ፈላስፎች የሚያነሡትን ጥያቄ አስታውሶ እንዲህ አለኝ፡- “ክርስቶስ እግዚአብሔር ከሆነ እርሱ ሞቶ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ከነበረ በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ ዓለምን የሚመግባት ማን ነበር? ብለው ፈላስፎች ይጠይቃሉና ስለዚህ ምን ትላለህ? ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ይህ ጥያቄ እንደው ለእነርሱ ከባድ መስሎአቸው ያነሱት ጥያቄ እንጂ ፍልስፍናን በማወቃቸው የጠየቁት ጥያቄ አይመስለኝም፡፡
 
የእነርሱ ጥያቄ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ስለክርስቶስ ሞትና ሕያውነት የተናገረውን አስታውሶኝ ስለእርሱ እነግረው ገባሁ፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ እንዲህ ይላልክርስቶስ በመስቀል ላይ ነፍሱን ከሰጠ በኋላ ከጠባቂዎቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወግቶት ነበር፡፡ እናም ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰእነዚህን ቅዱስ ዮሐንስ ምስክሮች ይላቸዋል፡፡(1ዮሐ.58) ከሞተ ሰው አካል እዥ (ውኃ የመሰለ ፈሳሽ) ይፈሳል፡፡ ከክርስቶስም ጎን ደግሞ ውኃ ፈሱዋል፡፡ ይህ በእርግጠኝነት ስለመሞቱ ምስክር ነው፡፡ ነገር ግን ከሞተ ሰው ሰውነት ደም አይፈስም፡፡ ሰው ሕያው ሳለ ሰውነቱ በአንድ ነገር ቢቆስል ወይም ቢወጋ ደም ይፈሰዋል፡፡ ከሞተ በኋላ ግን ቢወጉት ወይም ቢያቆስሉት ደም አይፈሰውም፡፡ ነገር ግን ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ነፍሱን ከሰጠ በኋላ ከጠባቂዎች አንዱ ጎኑን በጦር ሲወጋው ደም ከጎኑ ፈሱዋል፡፡ ይህ የሕያውነቱ ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ጊዜ ክርስቶስ ሞቶአልም ሕያውም ነው፡፡ በሕያውነቱም ዘለዓለማዊ ነውና ዓለምን ሲገዛትና ሲመግባት ይኖራልብሎ እንደጻፈልን ነገርኩት፡፡ አስከትዬም፡- ስለዚህ የክርስቶስሞት ርስቱን በእርሱ ለሚያምኑት ሊያወርሳቸው ነው፡፡ ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስበዙፋኑና በዐራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ” (ራእይ.56) ብሎ ከገለጸው ጋር ይመሳሰላል፡፡እንደ ታረደ በግሲል ሞቱን ያሳየናል፡፡ መቼም ቢሆን የታረደ በግ አይቆምም ነገር ግን ወንጌላዊውእንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁበማለት ታርዶም ቆሞም እንደነበር ይገልጥልናል፡፡ቆሞ አየሁሲል ሕያውነቱን ሲያስረዳን ነው እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ጊዜ ሞቶአልም ሕያውም ነው ብለን ደምድመን መናገር እንችላለን፡፡
ፈላስፎች የሳቱት እንግዲህ ፍልስፍናን ባለማወቃቸው እንጂ አውቀውት ቢሆን ኖሮ ፍልስፍና የትምህርቶች ሁሉ እናትና አናት ነውና ደም ሕያው ከሆነ ሰው እንጂ ከሞተ ሰው ሊፈስ እንደማይችል አውቀው ቢሆን ኖሮ የክርስቶስን ሞትን ብቻ ሳይሆን ሕያውነቱንም አብረው አስተባብረው በተቀበሉ ነበር፡፡ ይህም ፍልስፍናን ጠንቅቀው ካለማወቃቸው የመጣ ነው፡፡ብዬ እየመለስኩለት ሳለ ዐራት ኪሎ መውረጃዬ ጋር ደረስኩ፡፡ ነገር ግን አጋጣሚ ሆኖ ሞባይሉ ሳንቲም ጨርሶ ውይይታችን በዚህ ተቋረጠ፡፡ ነገር ግን ንግግሬን ያዳምጡኝ የነበሩ አንዲት እናት ሲሰሙና ሲቆጩ አንደነበሩ በሚገልጥ ቃልአበቃአሉ፡፡ ዞር ብዬ ተመለከትከትኳቸው እሳቸውም መልሰው እኔን በጥላቻ ዓይን ገለመጡኝ፡፡ ፊቴን ከእሳቸው መለስ ሳደርግሰሞኑን ደግሞ እነዚህ ጆቫ ዊትነሶች እንዲህም ዓይነት ስልት ይዘው ብቅ ብለዋልብለው ሲናገሩ ሰማዋቸው፡፡ ድንግጥ አልኩኝ፡፡ የትኛው ንግግሬ ነበር ጆቫ ዊትነሶችን የሚመስለው ብዬ አሰብኩ፡፡ ቢሆንም እናቴ ናቸውና በእኔ እንዳይሰናከሉ እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እንደሆንኩ ለመግለጽ ሞከርኩ እሳቸው ግን ይበልጥ ሸሹኝ፡፡ እኔም እየተገረምኩ ከታክሲ ወርጄ ሾላ ቀበና ብሎ ከሚጣራው ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ ወደ ቤቴም አመራሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁላችንንም በፍቅሩ ይጎብኘን ምሥጢሩንም ይግለጥልን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment