Tuesday, March 12, 2013

“በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ”(1ጴጥ.3፡18)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03 /07/2005
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በእግዚአብሔነቱ መንፈስ ነው፡፡ ያም ማለት ግን ሥጋና አጥንት የለውም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሲሆን አምላክነቱ ሳይለወጥ እንደሆነ እንዲሁ ሥጋ አምላክ ሲሆን የሥጋ ባሕርይውን ሳይለውጥ ነው፡፡ ያም ማለት ረቂቁ ረቂቅነቱን ሳይተው ግዙፍ ሆነ፤ ግዙፉም ግዙፍነቱን ሳይለቅ ረቂቅ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰውነቱ አምላክም ሰውም ነው ማለት ነው፡፡
ይህን ከትንሣኤ በፊት ከልደቱ ጀምሮ የምናስተውለው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ይህ ግዙፍ ሆኖ ነገር ግን ረቂቅ መሆኑን ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ሰብአ ሰገል ለሕፃኑ ሰገዱ ይለናል፡፡(ማቴ.2፡30) ለመለኮት ሕፃን የሚለውን ቃል አንጠቀምም ነገር ግን ከድንግል ማርያም ለነሳው ሰውነት ይህን ቃል እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ለሕፃኑ ሰገዱ ሲሉ ለሰውነቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሲለን ነው፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡

እውር ሆኖ ተወልዶ የነበረው ሰውን ጌታችን ከፈወሰው በኋላ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው እርሱም መልሶ ጌታ ሆይ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ፡፡ ኢየሱስም አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው፡፡ እርሱም ጌታ ሆይ አምናለሁ አለ ሰገደለትም፡፡ኢየሱስም የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እዲታወሩ እኔ ለፍርድ መጣሁ”አለ፡፡ (ዮሐ.9፡35-37) እንግዲህ በዚህ ቦታ ከመወለዱ ጀምሮ እውር የነበረው ሰው ላየው አካል ነው የሰገደው፡፡ መለኮት በባሕርይው አይታይም፡፡ ጌታችን ግን “አይተኸዋልም ከአንተ ጋር የሚነጋገረውም እርሱ ነው” ነበር ያለው፡፡ ስለዚህ ሥጋ መለኮት ሳይሆን እንዴት ይህ ሰው ለክርስቶስ ሊሰግድለት ይችል ነበር? ክርስቶስስ ይህ ሥጋ ፍጡር ነው ለዚህ ልትሰግድ አይገባህም ብሎ ለምን አልተከላከለውም? ምክንያቱም አካሉ ያደረገውን ሰውነቱን አምላክ ስላደረገው ነው፡፡
 ከሕዝብም መካከል ሆኖ ሳለ በመሰወር ምንም ግዙፍ አካልን ቢለብስ ረቂቅም እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወልድ እኔ አለሁ አላቸው ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ ኢየሱስ ግን “ተሰወራቸው” ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡(ዮሐ.8፡18-19)እንዲል ማለት ነው፡፡ ይህም ምንም ግዙፍ ቢሆን ረቂቅም መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡ ከትንሣኤም በኋላ በተዘጋ በር በመግባትና መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም በማለት የተወጋው ጎኑንና የተቸነከሩትን እጆቹን በማሳየት ሕያው ሆኖ ከሞት እንደተነሣ አሳይቶአቸዋል ከእነርሱም ፊት በልቶአል፡፡(ዮሐ.20፡19.ሉቃ.24፡36-43) በዝግ ቤት መግባቱ ረቂቅነቱን የሚዳሰሰውን አካል ማሳየቱና መብላቱ ግዘፍ አካልን ገንዘብ ማድረጉን ያስረዳናል፡፡
ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት በሥጋ ሰውነቱ ዘመን ተቆጠረለት፡፡ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ስለዚህም መጥምቁ ዮሐንስ “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ያልሁት ይህ ነው፡፡” ብሎ “አንድ ሰው” በማለት ቅድምና ያልነበረው ሰዋዊውን ባሕርይ በፅንሰት በተፈጸመው ፍጹም አንድነት ወይም ተዋሕዶ ቅድምና ያለው እንዳደረገው ጽፎልን እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ጌታችን “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት አስቀድሞ ቅድምና ያልነበረውን ሰውነት ቅድምና ሰጥቶት መናገሩን እናስተውላለን፡፡(ዮሐ.1፡30፤3፡13) ይህን የመሰሉ ብዙ ጥቅሶችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሥጋው ሞተ ሲለን ነፍሱ ከሥጋው ፈጽማ ተለየች ሲለን ሲሆን በዚህም ሞታችንን መሞቱን እንረዳለን፡፡ “በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” ሲል ግን ነፍስ ከሥጋ ጋር ተዋሕዳ ለሥጋ ሕያውነትን እንደምትሰጠው እንዲሁ በፅንሰት ከሥጋ ጋር የተዋሐደው መለኮት ለዐይን ቅጽበት እንኳ ከሥጋ ስለማይለይ ለሥጋ ሕይወትን ሰጠው ሕያው አደረገው ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ ምንም በመቃብር ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቢያድር ሥጋው መበስበስን አላየም፤ እንዲሁም በትንሣኤው መግነዜን ፍቱልኝ መቃብሬን ክፈቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ይህም ክርስቶስ በሚዳሰሰው አካሉ ረቂቅም ግዙፉም መሆኑን የሚስረዳን ነው፡፡ ይህም ማለት አምላክም ሰውም መሆንኑን የሚያስረዳን ነው፡፡ በሥጋ ሰውነቱ ሰው ብቻ ከሆነ በአምላክ ግን ካልሆነ እንዴት መግነዙ ሳይፈታ መቃብሩ ሳይከፈት መነሣት ይችል ነበር? ይህም በራሱ የሥጋ ሰውነቱ አምላክም ሰውም መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን ምንም ነፍሱ ከሥጋው በመለየቱዋ ሞቷል ብንልም ከሥጋውና ከነፍሱ ጋር ተዋሕዶ ባለው መለኮት ሕያውም ነው፡፡
 በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ሕያውም ነው ሞቷልም እንላለን፡፡ ሰውነቱን ሕያው ነው ስንል አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ ሞቶአል ስንል ደግሞ ነፍሱ ስለተለየች ነው፡፡ መልአኩም መግደላዊት ማርያምን “ሕያውን ከሙታን መካከል ለምን ትፈልጉታላችሁ ተነሥቶአል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡(ሉቃ.24፡5) አሁን በሞቴ “ሕያው” ያለው ከሙታን መካከል የተነሣው የጌታን ሥጋን ነው ወይስ መለኮቱን? ይህ ያለ ጥርጥር ስለሥጋው ሰውነት እየተናገረ እንደሆነ ግልጥ ነው፡፡ ራሱም ጌታችን “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ” ብሎ አረጋግጦ አስረዳን፡፡(ራእይ.1፡16-17) “ሕያውም ነኝ ሞቼም ነበርሁ” ሲል ምን ማለቱ ይሆን ጌታችን? ሕያውነቱ ሥጋው አምላክ ስለሆነ ነው “ሞቼም ነበርሁ” ሲል ደግሞ ምንም ሥጋ አምላክ ቢሆን የሥጋ ባሕርይው እንዳልተለወጠ ሲያስረዳን ነው፡፡ ሥጋ ነፍስ ስትለየው ይሞታልና፡፡ እንዲያም ሆኖ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ” በማለት ለሥጋው ሰውነቱ ለአምላክ ብቻ የሚሰጠውን ስም መስጠቱን እንመለከታለን፡፡ “ሞቼም ነበርሁ” የሚለው ቃል በግልጥ እንደሚያስረዳን ይህንን ቃል ጌታችን እየተናገረ ያለው ስለሥጋው ሰውነቱ መሆኑን ነው፡፡ ፊተኛውና መጨረሻው የሚለው ስም የሚሰጠው አምላክ ለሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ እንደሆነ በግልጥ ያስረዳናል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ” “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” ማለቱ፡፡ 

3 comments:

  1. Denk Agelalaetse New. Kale Hiwoten Yasemalen.

    ReplyDelete
  2. Kale hiowten yasemalen tesfa mengiste semayaten yawereselen yagelgelote zemenen yarezemelen !!!

    ReplyDelete
  3. ትልቁን የተዋሕዶ ምሥጢር ነው ግልጥልጥ ያደረግህልን ፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን ፡፡

    ReplyDelete