Thursday, February 14, 2013

የአብርሃም ርስት ርስታችን




በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2005
ቅዱስ ጳውሎስ ርስት እንዴት እንደሚወረስ ሲገልጥልን “ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፡፡ ሰው ሲሞት ኑዛዛው ይጸናል ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን አይጠቅምም” ይለናል፡፡(ዕብ.9፡16-17)ይህ ክርስቶስ እኛን የርስቱ ወራሾች ሊያደርገን እንደ ሞተ ለማስረዳት የተጠቀመበት ኃይለ ቃል ነው፡፡
 ጥንተ ነገሩን ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም “በእውነት እየባረክሁ አባርክሃለሁ እያበዛሁ አበዛሃለሁ ብሎ በሌላ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለለት፡፡”(ዕብ.6፡13-14) አብርሃም ይህን እግዚአብሔር የማለለትን መሐላ ይዞ ከልጆቹ ጋር በስደት በባዕድ ሀገር ኖረ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት  በእምነት ታዘዘ፡፡ ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖረ የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፡፡ መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የመሠረታትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና” ብሎናል፡፡(ዕብ.11፡8-10) ይህ መሐላ የአብርሃምን እምነት ይዘው የርስቱ ወራሾች ሊሆኑ ለተጠሩት ሁሉ የሚሠራ መሓላ ነው፡፡

የርስቱ ወራሾች ለመሆን ደግሞ ርስቱን የሚያወርሰው እርሱ ሊሞት ይገባዋል ያለበለዚያ “ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን አይጠቅምም” ይላልና ስለዚህ እግዚአብሔር ቃል ርስቱን ሊያወርሳቸው ከእናታችን ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም በሥጋ ሊወለድና ሞትን ሊቀበል ተገባው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ የእግዚአብሔር የርስቱ ወራሽ የሆነው ከቅድስት ድንግል ማርያም የተካፈለው ሥጋና ደም ነበር፡፡ እርሱ በጽንሰት ከመለኮት ጋር ሲዋሐድ ፍጹም አምላክ ሆነ፡፡ ስለዚህ ለመለኮት ገንዘቡ የሆነው ሁሉ ለእርሱ ሆነ፤ የእርሱ የሆነው ሁሉ ደግሞ ለመለኮት ሆነ፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራዊያን መልእክቱ መግቢያ ላይ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው” ብሎ ስለክርስቶስ መናገሩ፡፡(ዕብ.1፡2) “ሁሉን ወራሽ” ባደረገው ሲል እግዚአብሔር ቃል ገንዘቡ ስላደረገው ከድንግል ማርያም ስለነሣው ሰውነቱ እየተናገረ ነው እንጂ እርሱስ እግዚአብሔር ነው ርስትን ይሰጣል እንጂ ርስትን አይቀበልም፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጡር የነበረውን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተካፈለውን ሥጋና ደም በጽንሰት ፍጹም አምላክ ሲያደርገው የሥጋ ሰውነት አስቀድሞ ገንዘቡ ያልነበረውን አምላክነትን ገንዘቡ አደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት “ሁሉን ወራሽ ባደረገው” ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ተናገረለት፡፡

 እግዚአብሔር ቃልም በራሱ ፈቃድ በአብና በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ለአብርሃም የማለውን መሐላ ሊፈጽም  ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት ሰው ሆነ፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ “የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይችል በሁለት በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ መካከል ገባ” ብሎ ጻፈልን፡፡(ዕብ.6፡17-18) "በመሐላ መካከል ገባ" ማለት ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መሐላው የሚፈጸመው ሰው ሲሆን ነውና፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቃል ሰው መሆኑ ብቻ የርስቱ ወራሾች እንድንሆን አያደርገንም፡፡ ምክንያቱም ከላይ ከመነሻችን እንደጠቀስነው “ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን አይጠቅምም” ይላልና፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ቃል ለአብርሃም የገባውን መሐላ ሊፈጽም እንዲሁም አብርሃምን በእምነት መስለው መዳናቸውን በተስፋ ለሚጠባበቁ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ሁሉ፣ በሕይወት ለነበሩትና ላለነው ለእኛ፣ ወደፊት ለሚነሡትም ሁሉ በሥጋ ሰውነቱ መሞት ነበረበት፡፡ በእርሱ ሞትም በሲኦል ያሉ ነፍሳት የርስቱ ወራሾች ሆኑ፣ እኛም ወደፊትም አብርሃምን በእምነትና በምግባር የመሰሉት ሁሉ አንድ ጊዜ በፈጸመው ቤዛነት የርስቱ ወራሾች ይሆናሉ፡፡
 ስለዚህም ጌታችን እኛን በሞቱ ወልዶን የርስቱ ወራሾች ሊያደርገን ለመስቀል ሞት ታዘዘ፡፡ በሞቱም ከአዳም ጀምሮ ያሉትን ነፍሳት በነፍሱ ወደ ሲኦል በመውረድ ወደ ርስቱ አፈለሳቸው፡፡ እኛም በአብርሃም አባታችን እምነት የተገኘን በሞቱ የርስቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከሞቱ ጋር ተባበርን የትንሣኤው ተካፋዮችም ሆንን፡፡ 
የአብርሃምን እምነት ለወደደ ራሱን እስከ መስጠት ደርሶ የርስቱ ወራሾች እንድንሆን ላበቃን ለልጁ ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን!!!     

1 comment:

  1. Amen kale hiowten yasemalen mengesete semayate yaworeselen yagleglote zemenhen yarezemelen !!!

    ReplyDelete