በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
1/03/2005
ማንም ሊገነዘብ የሚገባው እውነት
ይህ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን(oriental church) ትምህርት በሦስት መሠረታዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፣እግዚአብሔር በገለጣቸው እውነታዎች ላይ(በመንፈስ
ቅዱስ)፣ ቤተክርስቲያን በተቀበለቻቸው በተለይ 1-5 ክ/ዘመን በተነሡ ቅዱሳን አባቶች ትምህርት
ላይ ነው፡፡ ወይም በዐራት ሕግጋት ላይ የተመሠረቱ ናቸው እነዚህም 1. በተፈጥሮአዊ ሕግ (1ቆሮ.11፡14፤15) 2.
በሕሊናዊ ሕግ ላ(ሮሜ.2፡14) 3. በመጽሐፋዊ ሕግና በመንፈሳዊ ሕግ ላይ(God revelation.1ቆሮ.2፡12-16፤)ናቸው፡፡
አንድ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እነዚህን
ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡ከእነዚህ ዐራት መሠረታዊ የሕግ ምንጮች ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የእነዚህም አቀራረባቸው:-
በእምነት(በቀጥታ በመቀበል፡፡ ይህ ከአእምሮ መረዳት በላይ የሆኑ እግዚአብሔር የገለጣቸውን እውነታዎችን ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር
ወልድን ከአብ መወለድን በተመለከተ፤የሥጋና የመለኮት ተዋሕዶን በተመለከተ፣ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት፣ ወይኑ ወደ ደመ መለኮት
የሕብስቱም ወደ ሥጋ መለኮት የመለወጥን ምሥጢርና ሌሎቹም ይገኙበታል) እና በምክንያት (logic or reason) ላይ የተመሠረቱ
መሆን አለባቸው፡፡ ይህ በተፈጥሮአችንና በሕሊናችን ለተሠሩት ሕግጋት ትንታኔ የምንሠጥበት መንገድ ነው፤እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ
እንድንረዳቸው የሆኑትንም ያካትታል፡፡
የሰው ተፈጥሮም እነዚህን መሠረት
ያደረገ ነው፡፡ የሚታይ ግዙፍ አካል አለው፡፡ ይህን አካል በተፈጥሮው የተሠሩለት ሕግጋት ይገዙታል፡፡ ረቂቅ የሆነች መንፈሳዊት
አካል አለችን እርሱዋም ነፍሳችን ናት፡፡ ይህቺም ሕሊናዊው ሕግ ይገዛታል፡፡ ሁለቱ በአንድነት በእግዚአብሔር አርዓያ ስለተፈጠሩ
ደግሞ ለእግዚአብሔር መንፈስ ይገዛሉ፡፡ ስለዚህም ተፈጥሮአዊ ሕግ አለ፡፡ ሕሊናዊ ሕግ አለ መንፈሳዊ ሕግ አለ፡፡ ነገር ግን ሰው
በገዛ መተላለፉ ምክንያት እነዚህን ሕግጋት በአግባቡ ተጠቅሞ ሊመላለስባቸው አልቻለምና ስለዚህም ከተፈጥሮው፣ ከሕሊናውና ከመንፈስ
ቅዱስ ሊያገኛቸው የሚገቡትን እውቀቶች በማጥፋቱ በቀለም በወረቀት ላይ የተጻፉ ሕግጋቶችና መልእክቶች አስፈለጉት፡፡ ይህም መጽሐፍ
ቅዱስ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ማለት የራሳችንን
መልክ የምናይበት መስታወት ማለት ነው፡፡(ያዕ.1፡23-24) ነገር ግን ራሳችንን እንደተፈጠርንበት ዓላማ ያኖርን እንደሆነ የመጻሕፍት
ድጋፍ ላያስፈልገን ይችላል፡፡ ቢሆንም ላልበሰሉትና ለሕፃናት መንፈሳዊውን ሕይወትና ትምህርት ለማስረዳት እንዲቻለን እንደ ጌታችንና
እንደ ሐዋርያት መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን እናስተምራለን፡፡ ስለዚህም ምልልሳችን ልክ እንደ ሐዋርያት ሆነ ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም
ከላይ ከገለጥኩዋቸው ጋር የሚጣጣሙ ወይም በእምነት የምንቀበለውን እውነታዎችን ይነግረናል ያስተምረናል፡፡ እኛም በሰገነት ላይ እንሰብከዋለን
እኛም እንኖርበታለን፡፡ ይህን የመንፈስ ቅዱስ ምሪት መንፈሳዊ ሕግ እንለዋለን፡፡ ሕይወቱንም መንፈሳዊነት እንለዋለን፡፡ እንሂን
ሁሉ ቤተክርስቲያናችን ከምትቀበላቸው አባቶች ጽሑፍ ውስጥ በግልጽ የምናስተውላቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መሠረት ያላደረገና
ከእነዚህ የወጣ ማንኛውም መንፈሳዊ ጽሑፍ ወይም ትውፊት(Tradation) ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡
Kale hiywot yasemalin wendimachin
ReplyDelete