Saturday, July 28, 2012

“ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን”(በቅዱስ ኤፍሬም)የመጨረሻ ክፍል



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/11/2004 ዓ.ም
ጌታችን “በሰገነት ላይ ያለ ወደ ኋላ አይመለስ”(ሉቃ.17፡31) በሚለው ኃይለ ቃሉ በእነርሱ ላይ ቁጣው ምንም የነደደ ቢሆንም የእነርሱን ጥፋት እንደማይወድ ያሳየበት ኃይለ ቃል ነው፡፡ “በዚያችም ወራት ለርጉዞች ለሚያጠቡ ወዮላቸው”(ማቴ.24፡19) ሲልም በጊዜው ስለፀነሱት ሴቶች ልጆቻቸው እየተናገረ ሳይሆን በሮማዊያን ጭንቅ የሆነ መከራን ትቀበላላችሁ ሲላቸው ነበር፡፡ ስለዚህም “ችግር በምድር ላይ በዚህም ሕዝብ ላይ ይሆናል”(ሉቃ.21፡23)ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” በማለት ከዚህ መከራ እንዲድኑ ጌታችን አስጠነቀቃቸው፡፡ እንዲህም ሲል የጽድቅን ሥራ የማትሠሩባት ቀን ትመጣለች፡፡ በዚያች ዕለት መብራታችሁን ከዘይታችሁ ጋር ሳትይዙ እንዳትገኙ፤ ይህም ማለት ፍቅርን ከምጽዋትና ከንጽሕና ጋር ወይም እምነትን ከምግባር ጋር ሳትይዙ እንዳትገኙ ተጠንቀቁ በዚያች በመጨረሻዋ ሰዓት ለመብራታችን ዘይት እንፈልግ በማለት ያም ማለት የትሩፋት ሥራዎችን እንሥራ ብትሉ አይቻላችሁም፤ ምክንያቱም ጊዜው የሥራ ሳይሆን የፍርድ ጊዜ ነውና፡፡(ማቴ.25፡1-13) ስለዚህም ጽድቅን ሳትሠሩ ጊዜው ፈጥኖ እንዳይደርስባችሁና እንዳይፈረድባችሁ በጸሎት ትጉ ሲል “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተጠንቀቁ” አላቸው፡፡ በክረምት ፍሬ እንደሌለ በሰንበትም ሥራ የለም፡፡ ስለዚህም ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን ሲል እምነትንና ምግባርን ሳትይዙ ድንገት ምጽአቱ እንዳይደርስባችሁ በጸሎት ትጉ ሲል ነው፡፡

ሰንበትንና ክረምትን በፈቃድና ተገደን የምናርፍባቸው ጊዜአት ናቸው፡፡ ሰንበትን በፈቃድ ክረምትን ግን በተፈጥሮ አስገዳጅነት እናርፍባቸዋለን፡፡ በክረምት ሲል የዘር ወቅት ካለፈ በኋላ ማለቱ ነው፤ ይህም ሌላ አንድምታ ይሰጠናል፡፡ ውጫዊ ምክንያቶች ወይም የገዛ ፈቃዳችሁ የጌታን ፈቃድ እንዳትፈጽሙ እንቅፋት አንዳይሆባችሁ ተጠንቀቁ በጸሎትም ትጉ ሲልም ነው፡፡ ስለዚህ “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን” አለን፡፡ ያም ማለት ጊዜን ሳትመርጡ መልካምን በመፈጸም ያጸናችሁ ዘንድ ትጉና ጸልዩ ማለቱ ነው፡፡
ጌታችን በእነርሱ ላይ ቁጣው እንደምትነድ ገልጦ ካበቃ በኋላ ጥፋታቸውንም ማየት ስለማይወድ ከዚህች ክፉ ቀን የሚያመልጡበትንም መንገድ “ተግታችሁ ጸልዩ በማለት” ጠቆማቸው፡፡ ይህም ሰው ሁሉ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃዱ እንዳልሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህም በጊዜው ስለሚፈጸመው ቁጣው በዚህ መልክ ከገለጠላቸው በኋላ ስለ ርኅራኄው ደግሞ ከዚህ ቁጣ ያመልጡ ዘንድ መንገዱን አሳያቸው፡፡ እንዲህ ማለቱ ይህ ቁጣ በእነርሱ ላይ ከመፈጸም ይመለሳል ማለቱ ሳይሆን በጸሎት ቢተጉ በዚያ መከራ ሰዓት በእነርሱ ላይ ከሚመጣባቸው መከራ እንደሚጠብቃቸው የሚያስረዳ ነው፡፡
የጌታ ምሕረት ግን ሁለቱን አንድ ላይ በዚያን ጊዜ ትፈጽማለች፡፡ ይህ ጭንቅ የሆነ የፍርድ ሰዓት እንድትመጣ በእርሱ ዘንድ ተቆርጣለች፡፡ እነርሱም ከመከራ የተነሣ እንደሚሰደዱ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በክረምት በእናንተ ላይ የሚመጣው መከራ እንዳይደርስባችሁ በጸሎት ትጉ፡፡ ምክንያቱም ይህን ጭንቅ የሆነ መከራ በመሰደድ የምታመልጡት ወይም ሰንበትን በማክበራችሁ የምታመልጡት አይደለም፡፡ ነገር ግን በጸሎት ብትጸኑ በዕረፍታችሁ ቀን የሚመጣባችሁ መከራ እናንተን የሚያስደነግጣችሁ አይሆንም ሲላቸው ነው፡፡
በዚህ ቦታ ጌታችን ምንም እንኳ ለሙሴ የተሰጠችውን ሕግ ሊያሳልፋት ቢመጣም የሕግ አውጪው ልጅ እንደመሆኑ መጠን የሕጉ ጠባቂ መሆኑን ለአይሁድ በትምህርቱ ገለጠላቸው፡፡ እንዲህ ሲል “ከእናንተ መካከል ራሳቸውን በንጽሕናና በየዋሃት የምታመላልሱ፣ ሰንበትን በሰላሙ ቀን እንደምታከብሩዋት በጦርነትም ሰዓት የምትጠብቁ አላችሁ፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ማምለጫ በሌለው ዋሻ እንደተገኙ ሰዎች አጥፊዎቻችሁ በሰንበትና በክረምት ሊገድሉአችሁ ይችላሉ፡፡ ክረምት ከበጋ ሥራችን ሁሉ የምናርፍበት ነው፡፡ ይህ ግን አያስፈራችሁ፤ ይህችኛዋ ሰንበት ከሥራችና ከድካማችን የምናርፍባት ሰንበት ጥላ ናት፡፡ ጌታችን የሚሰጠን ሰንበት ግን ከሰባቱ የሥራ ቀኖቻችን የምናርፍባት ናት(ስምንተኛው ቀን የምትባለዋን በትንሣኤ የምናገኛት ዘለዓለማዊ ዕረፍታችን ናት( ስለ “ስምንተኛዋ ቀን” ለማወቅ እዚህ ይጫኑ )ይህች ሰንበት ሐዋርያው “እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል”ብሎ የተናገረላት ለዘለዓለም ከሥራ ሁሉ የምናርፍባት ቀን ናት፡፡(ዕብ.4፡9) ስለዚህም ጌታችን “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ”ብሎ አስተማረን፡፡(ሉቃ፡21፡36) በዚህም ጌታችን ስለኢየሩሳሌም ጥፋትና ስለ መጨረሻው የፍርድ ሰዓት በአንድነት ተናገረ፡፡
“ትሰደዱ ዘንድ አላችሁ” ሲል ስለትንሣኤ መናገሩ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ራሳቸውን በጽድቅ ሕይወት ያላጸኑት ሰዎች ከታዘዘባቸው መከራ የተነሳ ፍርሃት ሲወድቅባቸው በጽድቅ ሕይወት የጸኑት ግን በእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፡፡(ማቴ.13፡43)
አንዳንዶች ይህን ለሐዋርያት ሰጥተው የሚተረጉሙም አሉ፡፡ ስለዚህም ጌታችን ስደስተኛዋ ቀን በዕለተ ቀዳሚት ሰንበት አልፋ ጀምበር ልትወጣ ስታቀላላ ሐዋርያት የትንሣኤውን ዜና ሰምተው ደስ ይላቸዋል ሲል እንዲህ አለ ብለው ይተረጉማሉ፡፡
ጌታችን በዚህ ቦታ ሰንበትን መጥቀሱ አይሁድ በሰንበት ስለሚመኩ ነበር፡፡ ክርምትንም ማንሣቱ በክረምት ከባድ የሆነ ቅዝቃዜ አለና በፍርድ ጊዜ የሚመጣን መከራ ጽናት ለማስረዳት እንዲመቸው ነበር፡፡
“ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነገር ግን ስለመረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ፡፡”(ማር.13፡20)በማለቱ ጌታችን የቀናቱን ወይም የሰዓቱን ማጠር እየተናገረ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜው በራሱ አጭር ነውና፤ ነገር ግን በጸሎት የተጉት “ምርጦቹ” የተባሉት ቅዱሳኑ ላይ የሚመጣው መከራ አይበዛባቸውም፤ መዳናቸው ወዲያው ይፈጸምላቸዋል ሲለን ነው፡፡
አምላካችን ሆይ! ሁሌም መብራታችንን ከዘይታችን ጋር አስተባብረን ይዘን በጸሎት ጸንተን እንደ ቅዱሳኖችህ “ጌታችን ሆይ ና”(1ቆሮ.16፡22) ብለን በድፍረት ወደ አንተ ለመጣራት እንድንበቃ ሁል ጊዜም ምጽአትህን በማሰብና እንደፈቃድህ በሆነ የጽድቅ ሕይወት መመላለስን ስጠን፡፡ ለአንተ ለወደድከን እንጠፋ ዘንድ ለማትወድ አምላክ ክብር ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!   

No comments:

Post a Comment