Wednesday, November 7, 2012

ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ድንግል ማርያም በንጽጽር(ቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/02/2005
አረጋዊቱ ኤልሳቤጥ የነቢያት ፍጻሜ የሆነውን ዮሐንስ መጥምቅን በእርጅናዋ ወለደች፤ ታናሽዋ ብላቴና ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የመላእክትን ጌታ ወለደች፡፡ ከአሮን ወገን የሆነችው ኤልሳቤጥ በምድረ በዳ የሚጮኸውን የሰው ደምፅ ወለደች፤ የዳዊት ልጅ የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ለሰማያዊው ንጉሥ ቃሉ የሆነውን ክርስቶስን ወለደችው፡፡ የካህኑ ዘካርያስ ሚስት የሆነችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በጌታ ፊት የሚሄድ መልእክተኛውን ወለደች፤  የዳዊት ልጅ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ምድሪቱን የሚገዛት እግዚአብሔርን በሥጋ ወለደች፡፡  መካን የሆነች መኅፀን ሰዎችን ለንስሐ የሚያዘጋጅ ልጅን ወለደች፡፡ ድንግል የሆነች ማኅፀን ግን የሰው ልጆችን ኃጢአት የሚያስወግድ ልጅን ወለደች፡፡ ኤልሳቤጥ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ልጅን ወለደች፡፡ ድንግል ማርያም ግን በኃጢአት ያደፈችውን ምድር በደሙ የሚነጻ ልጅን ወለደችልን፡፡ በፅንሰት ታላቁ የሆነው ዮሐንስ ለያዕቆብ ቤት ብርሃን ሆናቸው፡፡ በፅነሰት ታናሹ የሆነው የድንግሊቱ ልጅ ክርስቶስ ግን ለዓለም ሁሉ የጽድቅ ፀሐይ ሆነ፡፡

መልአኩ ለካህኑ ዘካርያስ የምስራችን ነገረው፡፡ በዚህም በቤተመቅደስ የሚሠዋው ካህኑ ዘካርያስ ስለብዙዎች ስለሚሠዋው ክርስቶስ ሲያውጅ፤ ክፉው ሄሮድስ(ሰይጣን) ደግሞ ሞትን በሕፃናት ላይ አወጀ፡፡ በውኃ የሚያጠምቀው ዮሐንስ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ስለሚያጠምቀው ክርስቶስን አወጀ ነጋሪው ሆነ፡፡  ታናሹ ብርሃንም ስለ ጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ አወጀ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስን ለሚሰጠው ለእርሱ አዋጅ ነጋሪው ሆነ፡፡ ካህኑ ዘካርያስ በመለከት ድምፅ ለሰዎች በዘመኑ ፍጻሜ ስለሚነሣው የአዋጅ ነጋሪ ድምፅ ስለተባለው ልጁ አዋጅን ነገረ፡፡ ይህ የአዋጅ ነገሪ ድምፅም እግዚአብሔር ቃልን በተመለከተ አዋጅ ነጋሪ ሆነ፡፡ መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል በጌታ ላይ ማረፉን የተመለከተው ዮሐንስ ከመብረቅ በፊትን እንደሚነጉደው ነጎድጓድ ድምፅ ሆኖ ለብርሃን ክርስቶስ ምስክርነቱን ሰጠ፡፡
“ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል”(ሉቃ.1፡79)ሲል ካህኑ ዘካርያስ ሰብአ ሰግልን እየመራው ስለመጣው ኮከብ መናገሩ ነው፡፡ “በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት” ሲልም የጽድቅ ፀሐይ የሆነው ክርስቶስ እንደወጣ ዘግይተው ስለተረዱት የሚናገር ነው፡፡ ወይም “በጨለማ ውስጥ እስራኤላውንን ይመለከታል፡፡ የጥበብ ሰዎች ለዓለም በወጣው ብርሃን ምክንያት ራሳቸውን አራቀቁ፡፡  ስለዚህም ነው ካህኑ ዘካርያስ “እግሮቻቸውንንም በሰላም መንገድ ያቀናል” ብሎ መናገሩ፡፡ ምስጋና ይሁን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment