Tuesday, March 12, 2013

“በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ”(1ጴጥ.3፡18)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03 /07/2005
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በእግዚአብሔነቱ መንፈስ ነው፡፡ ያም ማለት ግን ሥጋና አጥንት የለውም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሲሆን አምላክነቱ ሳይለወጥ እንደሆነ እንዲሁ ሥጋ አምላክ ሲሆን የሥጋ ባሕርይውን ሳይለውጥ ነው፡፡ ያም ማለት ረቂቁ ረቂቅነቱን ሳይተው ግዙፍ ሆነ፤ ግዙፉም ግዙፍነቱን ሳይለቅ ረቂቅ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰውነቱ አምላክም ሰውም ነው ማለት ነው፡፡
ይህን ከትንሣኤ በፊት ከልደቱ ጀምሮ የምናስተውለው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ይህ ግዙፍ ሆኖ ነገር ግን ረቂቅ መሆኑን ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ሰብአ ሰገል ለሕፃኑ ሰገዱ ይለናል፡፡(ማቴ.2፡30) ለመለኮት ሕፃን የሚለውን ቃል አንጠቀምም ነገር ግን ከድንግል ማርያም ለነሳው ሰውነት ይህን ቃል እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ለሕፃኑ ሰገዱ ሲሉ ለሰውነቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሲለን ነው፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡

Wednesday, February 27, 2013

የዛሬ ገጠመኜ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/06/2005
ዛሬ አንድ የገጠመኝን ገጠመኝ ላውጋችሁ እንዲህ ነው፡- አንድ የልብ ወዳጄለሆነ ጉዳይ እፈልግሃለሁብሎ ወደ እርሱ በታክሲ አመራሁ የሥራ ቦታው ወደ መስቀል ፍራዎል አካባቢ ነበር፡፡ ሄድኩ በፍቅር ተወያየን ለእኔ ጥሩ አሳቢ ነበርና በእርሱ አምላኬን አመሰገንኹት፡፡ ከእርሱ ጋር ውይይቴን ከጨረስኩ በኋላ ከአምባሳደር ዐራት ኪሎ የሚለውን ታክሲ ይዤ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡
በመንገድ ላይ ሳለሁ ግን አንድ ወዳጄ ከክፍለሀገር ደወለልኝ፡፡ ስለ ግል ጉዳያችን ከተጠያየቅን በኋላ ወደ መጨረሻ ላይ ለመሆኑየአብርሃም ርስት ርስታችንየሚለውን ምንባብ ተመለከትከውን? አልኩት ተመልከቼዋለሁ ግን ካነበብኩት ስለቆየሁ እስቲ ትን አስታውሰኝ አለኝ፡፡ እኔምለአብርሃም በራሱ ምሎ በመሐላ መካከል የገባውና በሞቱ ርስቱን ለአብርሃምና የአብርሃምን እምነት ይዘው ላሉት ሊያወርስ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ራሱን ስለሰዋው እግዚአብሔር ቃል የሚያትት ነው” ብዬ አስታወስኩት፡፡ እርሱም ፈላስፎች የሚያነሡትን ጥያቄ አስታውሶ እንዲህ አለኝ፡- “ክርስቶስ እግዚአብሔር ከሆነ እርሱ ሞቶ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ከነበረ በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ ዓለምን የሚመግባት ማን ነበር? ብለው ፈላስፎች ይጠይቃሉና ስለዚህ ምን ትላለህ? ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ይህ ጥያቄ እንደው ለእነርሱ ከባድ መስሎአቸው ያነሱት ጥያቄ እንጂ ፍልስፍናን በማወቃቸው የጠየቁት ጥያቄ አይመስለኝም፡፡

Thursday, February 14, 2013

የአብርሃም ርስት ርስታችን




በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2005
ቅዱስ ጳውሎስ ርስት እንዴት እንደሚወረስ ሲገልጥልን “ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፡፡ ሰው ሲሞት ኑዛዛው ይጸናል ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን አይጠቅምም” ይለናል፡፡(ዕብ.9፡16-17)ይህ ክርስቶስ እኛን የርስቱ ወራሾች ሊያደርገን እንደ ሞተ ለማስረዳት የተጠቀመበት ኃይለ ቃል ነው፡፡
 ጥንተ ነገሩን ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም “በእውነት እየባረክሁ አባርክሃለሁ እያበዛሁ አበዛሃለሁ ብሎ በሌላ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለለት፡፡”(ዕብ.6፡13-14) አብርሃም ይህን እግዚአብሔር የማለለትን መሐላ ይዞ ከልጆቹ ጋር በስደት በባዕድ ሀገር ኖረ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት  በእምነት ታዘዘ፡፡ ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖረ የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፡፡ መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የመሠረታትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና” ብሎናል፡፡(ዕብ.11፡8-10) ይህ መሐላ የአብርሃምን እምነት ይዘው የርስቱ ወራሾች ሊሆኑ ለተጠሩት ሁሉ የሚሠራ መሓላ ነው፡፡