Tuesday, March 12, 2013

“በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ”(1ጴጥ.3፡18)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03 /07/2005
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በእግዚአብሔነቱ መንፈስ ነው፡፡ ያም ማለት ግን ሥጋና አጥንት የለውም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሲሆን አምላክነቱ ሳይለወጥ እንደሆነ እንዲሁ ሥጋ አምላክ ሲሆን የሥጋ ባሕርይውን ሳይለውጥ ነው፡፡ ያም ማለት ረቂቁ ረቂቅነቱን ሳይተው ግዙፍ ሆነ፤ ግዙፉም ግዙፍነቱን ሳይለቅ ረቂቅ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰውነቱ አምላክም ሰውም ነው ማለት ነው፡፡
ይህን ከትንሣኤ በፊት ከልደቱ ጀምሮ የምናስተውለው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ይህ ግዙፍ ሆኖ ነገር ግን ረቂቅ መሆኑን ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ሰብአ ሰገል ለሕፃኑ ሰገዱ ይለናል፡፡(ማቴ.2፡30) ለመለኮት ሕፃን የሚለውን ቃል አንጠቀምም ነገር ግን ከድንግል ማርያም ለነሳው ሰውነት ይህን ቃል እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ ለሕፃኑ ሰገዱ ሲሉ ለሰውነቱ ሰብአ ሰገል ሰገዱ ሲለን ነው፡፡ ይህም ሥጋ አምላክ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡