Tuesday, July 11, 2017

አረጋዊው ማን ነው?

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
4/11/2009
መቼም ስለ ዕድሜ ሲነገር ቆጠራው ከጽንሰት ከተጀመረ እንደ ጻድቁ ኢዮብከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል”(ኢዮ.141) ማለታችን ግድ ነው፡፡ ከጽንሰት የምንጀምራት ዕድሜአችን እንደ ጠዋት ጤዛ ወይም እንደ ሳር አበባ ናት፡፡ ባንድ ቀን ለምልማ በአንድ ቀን የምትረግፍ አበባ ማለት ይህቺ ምድራዊዋ ዘመናችን ናት፡፡ ቢሆንም ዋጋ ያላትም ይህቺው ዕድሜአችን ናት፡፡ በዚህች ዕድሜአችን በሰውነት ሕዋሳቶቻችን ሁሉ መልካምን ካልሠራንባቸው ዕዳዋ ዘለዓለማዊ ሆኖ ይሠፈርብናል፡፡ ከሠራን ደግሞ የተጠቀጠቀና የተጨቆነ ብድራትን ከአምላክ ዘንድ እናገኝባታለን፡፡ ግን ደግሞ ዕድሜአችንን በአምላክ ሕሊና ከመታሰባችን ጊዜ አንስቶ እንደ ንጉሥ ዳዊትአቤቱያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አን ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ”(መዝ.13816) ብለን የቆጠርን እንደሆነ ዕድሜአችን የትናለሌ ሊሆን ነው፡፡ ከመቼ ጀምሮ በአምላክ ሕሊና እንደታሰብን በጭራሽ አናውቀውም ግን ደግሞ አምላክ እንደ ሰው አያስብምና መነሻ አለው ማለት አይቻለንም፡፡ እርሱ ያሰበው ከዘለዓለም ያሰበው ነው፤ እንዲያስብ ምክንያቶች አያስፈልጉትም፡፡ የማያውቀው ወደፊት የሚያውቀው ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ ዕድሜአችንን በእግዚአብሔር ሕሊና ከመታሰባችን አንስቶ ከቆጠርነው ሳንወለድም በፊት አረጋውያን ነን ምክንያቱም ሳይሠራን በሕሊናው ነበርን ሳንፈጠርም ቀኖቻቸችን በእርሱ ሕሊና የታወቁ ናቸውና፡፡
አደራ ግን ይህ ቃል ስለ ዳዊት ብቻ የተነገረ ነው እንዳትሉኝ ምክንያቱም አምላክ ሳያስበው የሚፈጥረው ነገር የለምና፡፡ አይደለም እርሱ እኛ እንኳ ያላሰብነውን አንተገብርም፡፡ በሕሊናችን የጨረስነውን በተግባር እንፈጽመዋለን፡፡ ስለዚህ ቃሉ ያለጥርጥር ለዳዊት ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ለእኛም ይሠራል፡፡ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ዕድሜአችን ስንት ነው? እንጃ እርሱ እግዚአብሔር ያውቀዋል እኛ ልናውቅ የምንችለው ቢኖር በሥጋ ተጸንሰን በዚህ ምድር የተመላለስንባትን ዕድሜ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ዕድሜ የለም ከዚያም በኋላ በትንሣኤ ዕድሜ አይኖርም፡፡ ከእነዚህ አንጻር በሥጋ የምንኖርባት ይህቺ ዕድሜ ስትሰላ እንደ ጠዋት ጤዛ ጠዋት ታይታ ፀሐይ ሲተኩስ የምትጠፋ ወይም እንደ ምድር አበባ በአንድ ቀን አብባ በአንድ ቀን የምትከስም እንደሆነች እንረዳለን፡፡