በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም
ሰውነታችሁን በእውነት በጽድቅ ሕይወት ቤተ መቅደስ አድርጋችሁ እርሱ የሁሉ ጌታ የሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች ነፍሳችሁ መንገሡ የሚታወቃችሁና እርሱን አውቃችሁ እጅግ ትሑታን ሆናችሁ
የምትመላለሱ ቅዱሳን ሆይ እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የእናንተ ጭንቀት በሰውነታችሁ መቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን
ውስጥ ነግሦ ያለውን ጌታ አለማሳዘን የሆነ በሕሊናችሁ ውስጥ ስለምታሰላስሉት ሓሳብ እንኳ የምትጠነቀቁ ቅዱሳን ሆይ
እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ እናንተ በሦስት አጥሮች ራሳችሁን አጥራችሁ ግርማውን እያያችሁ እንደ ቅዱሳን
መላእክት በፍርሃትና በርዓድ ሆናችሁ በእርሱ ፊት ዘወትር የምትቆሙ ቅዱሳን ሆይ በእውነት እናንተ ንዑዳን ክቡራን
ናችሁ፡፡