Tuesday, July 3, 2012

ጸሎት ዘአረጋዊ ዮሐንስ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/10/2004 
“ከእኔ የተሰወርክና የተሸሸግህ ጌታዬ ሆይ! አንተነትህን ግለጥልኝ ፡፡ ከእኔ ውስጥ ያለውን ያንተን ውበት አሳየኝ ፡፡ ሰውነቴ ለአንተ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ይሆን ዘንድ የሠራኸው ጌታዬ ሆይ! (፩ቆሮ.፫፥፲፮-፲፯፤፪ቆሮ.፮፥፲፮)የክብርህ ደመና ቤተ መቅደስህ የሆነውን ሰውነቴን ይክደነው፤ የመሠዊያህም አገልጋይ የሆነችው ነፍሴ በፍቅር በመሆን አንተን ቅዱስ እያሉ በአድንቆትና በአግርሞት፣ በፍጹም ትጋትና ቅድስና እንደሚያገለግሉህ ሕያዋንና መንፈሳውያን ኃይላት ታመሰግንህ ዘንድ እርዳት፡፡…
የይቅርታ ውቅያኖስ የሆንክ ክርስቶስ ሆይ! ካንተ የሆነውን ብርሃናዊ ልብስ ተጎናጽፌ እንዳንጸባርቅ ባንተ ውኃነት በኃጢአት ያደፈውን ሰውነቴን እንዳጥብ ፍቀድልኝ፡፡ ሕቡዕ በሆኑ ምሥጢራት የተሞላው የክብርህ ደመና(መንፈስ ቅዱስ) እኔን ይከድነኝ ዘንድ (በእኔ ያድር ዘንድ) በዐይኔ ከማላያቸው ጀምሬ ወደ አንተ ውበት የሚወስዱኝን የጽድቅ ጎዳናዎች አስተውል ዘንድና ባንተ ግርማ ተማርኬ ያለማቋረጥ ክብርህን አደንቅ ዘንድ እንዲሁም በዓለም ጉዳይ ዐይኖቼ ከመባከን ያርፉ ዘንድ ምንም ቢሆን ምን ከአንተ ፍቅር የሚለየኝ እንዳይኖር ከዚህ ይልቅ አንተን በመናፈቅ እንድኖር ያለማቋረጥ ፊትህን እመለከት ዘንድ የልቡናዬን ዐይኖች ግለጥልኝ የልቡናዬንም እርሻ  አለስልሰው ፡፡” 

Tuesday, June 12, 2012

እምነት እውነት ፍቅር በክርስትና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/10/2004
አንድ በሀገራችን የነገሡ ንጉሥ ነበሩ፡፡ እኒህ ንጉሥ አንድ ወቅት “ልጅ ለአባቱ እምነት ለእናቱ እውነት ነው”ብለው ተናገሩ ይባላል፡፡ እንዲህ ብለው ከሆነ በእውነት ድንቅ የሆነን እውነት ተናገሩ፡፡ እኔ ግን እንዲህ እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሔዋን አዳምን ታውቀውና ታፈቅረው እንዲሁም እንደ እናትነቱና እንደ አባትነቱ ትታዘዘው ዘንድ፣ እርሱን ፈጥሮ ካበቃ በኋላ ልክ ልጅ ከእናቱ ተወልዶ በአካል እስኪገለጥ ድረስ ከእናቱ ሰውነት ውስጥ ተሰውሮ እንዲቆይ እንዲሁ በአዳም አካል ተሰውራ እንድትቆይ አደረጋት፡፡ እናት ልጁዋን በዐይን ለማየት እንድትናፍቅ እርሱዋን ለማየት አዳም በናፈቀ ጊዜ እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ በመስቀል ላይ በተቀበለው ሕማም አርዓያ ሔዋንን ከአዳም ጎኑ አስገኛት፡፡ ስለዚህ ለአዳም አባታችን ሔዋን እውነቱ እንጂ እምነቱ አልነበረችም፡፡ እንዲሁም ሔዋን በአዳም አካል ውስጥ በነበረችበት ወቅት አዳም ፈጽሞ እንደሚወዳትና እንደሚያውቃት መጠን እርሱዋም እርሱን ፈጽማ ትወደውና ታውቀው ነበርና ለእርሱዋ አዳም እምነቷ ብቻ ሳይሆን እውነቷም ነው፡፡

Tuesday, June 5, 2012

"አባታችን ሆይ" በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመጨረሻው ክፍል


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
29/09/2004
...እርሱ ንጉሣችን ከሆነ ማን ያስፈራናል? ጌትነቱን ማንም ሊቃወምና ሊያጠፋ የሚቻለው የለም ፡፡ አርሱ  “መንግሥት የአንተ ናትና” ሲለን እኛን የሚዋጋውን ለጊዜ እግዚአብሔርን የሚቋቋም የሚመስለውን ሰይጣንን ለእኛ እንዲገዛ አሳልፎ እንደሚሰጠን ሲያመላክተን ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እርሱ ከእግዚአብሔር ባሪያዎች አንዱ ነው ፤ ምንም እንኳ ከተዋረዱትና ለመተላለፋችን ምክንያት ከሆኑት ወገኖች ዋናው ቢሆንም ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈቃድ ካለገኘ በቀር በእግዚአብሔር ባሮች ላይ የማደር መብቱ የለውም፡፡ ስለምን  እኔ “ በባሮቹ ላይ” እላለሁ ፣ በእሪያዎች ላይ እንኳ በማደር እነርሱን አስቻኩሎና አጣድፎ ለማጥፋት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድን መቀበል የግድ አለበት (ማቴ.፯፥፲፬) በእንስሳት መንጋ ላይ እርሱ ካለፈቀደለት በቀር ከቶ ሊያድር ካልቻለ በሰው ልጆች ላይ እርሱ እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር እንዴት ሊያድር ይችላል?