Saturday, July 7, 2012

የቤተ ክርስቲያንን ለቤተ ክርስቲያን የገዳምን ለገዳማውያን



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/10/2004
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ …ትወደኛለህን? ብሎ ከጠየቀውና እርሱም አዎን ብሎ ከመለሰ በኋላ “... ግልገሎቼን አሰማራ…ጠቦቶቼን ጠብቅ … በጎቼን አሰማራ” ብሎ መንጋውን እንዲጠብቅ አደራ እንደሰጠው እናውቃልን፡፡(ዮሐ.19፡15-17)ይህ ሓላፊነት ምንም እንኳ ለእርሱ ይነገረው እንጂ ለሐዋርያት ሁሉ የተሰጠ ሓላፊነት ነበር፡፡ እነርሱም የክርስቶስን መንጋ ከሥጋና ከመንፈስ ርሃብ ጠብቀው የድርሻቸውን ተወጥተው አልፈዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት ሕጻናት፣ ወጣቶችና አረጋዊያን በአንድነት የሚኖሩባት፣ በምድር ያለች ግን ሰማያዊት፤ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳን ነፍሳትና በምድር ያለነው በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በሞቱ ለዚህ ዓለም ኃጢአት የሞትን፤ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ሕይወት ሕያዋን የሆንንና በትንሣኤ ሕይወት የምንመላለስ የምንኖርባት፤ ጌታችን መድኀኒታችን የሚገዛትና የሚመራት ከምድር እስከ ሰማይ የተተከለች ዘለዓለማዊት መንግሥት ናት፡፡ ገዳም ግን መነኩሳት በፈቃድ የብሕትውናን ሕይወት መርጠው የሚኖሩባትና ለእነርሱ ብቻ የምትስማማ ሆና ሥርዐት የተበጀላት መንፈሳዊት ሥፍራ ናት፡፡


Wednesday, July 4, 2012

ዳግማዊቱ አዳም


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/10/2004
ክርስቲያኖች ሆይ ኑ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር መንፈሳዊ ቅኔን እንቀኝ፡፡ እርሱ ስለቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ይላል “አዳም ለሔዋን እናትም አባትም እንደነበር እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም ለልጁዋ ለወዳጁዋ እናትም አባቱም ሆነች፡፡” ከዚህ ተነስተን  አዳም የሚለው መጠሪያ ለድንግልም የሚያገለግል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ አዳም ስንል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማለታችን እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ አዳም ስንል ቅድስት ድንግል ማርያም ማለታችንም ነው፡፡በእርግጥ ጥንትም አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለወንዱ ብቻ የሚያገለግል መጠሪያ ሰም አልነበረም “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረበት ቀን ወንድና ሴት አድረጎ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው” ይላልና፡፡(ዘፍ.5፡2) እነሆ አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለሴቶችም እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ አዳም ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናትም አባትም ሆና አሳደገችው፡፡ ይህ ምሥጢር ሌላም እውነታን በውስጡ አዝሎ ይዟል፡፡ እርሱም፡- በክርስቶስ አምነን የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ለሆነውና በእርሱ አካል ለምንገለጠው ክርስቲያኖችም( ሮሜ.12፡5) ቅድስት ድንግል ማርያም እናትም አባትም መሆኑዋን እንረዳለን፡፡ ኦ ጌታችን ሆይ!!! ይህ እንዴት ድንቅ የሆነ ምሥጢር ነው!!!

Tuesday, July 3, 2012

ስለድንግል ምልጃ ከመነገሩ በፊት የሚቀድመው ቁም ነገር!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/10/2004
ቅድስት ድንግል ማርያም ነጻ ፈቃዷን ተጠቅማ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” በማለት ለመዳናችን ምክንያት የሆነችን እናት ናት፡፡ እርሱዋ በአንደበቱዋ “ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል መንፈሴም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሃሴትን ታደርጋለች” ብላ እንደገለጠችልን ሥጋዋን ብቻ ሳይሆን  ነፍሱዋንና ሕሊናዋን ለጌታ ማደሪያ በማድረግ ለእኛ ክርስቲያኖች አብነት የሆነች የመጀመሪያይቱ ክርስቲያንና  አማናዊቱ ቤተክርስቲያን ናት፡፡
እኛም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በሥጋችን ቤተ መቅደስ፤ ሕጉንና ፈቃዱን እንዲሁም መንፈሱን በነፍሳችንና በሕሊናችን ማኅደር በማሳደር እርሱዋን እንመስላታለን፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለእርሱዋና ስለእኛ በአንድነት ሲናገር“እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ”አለን(2ቆሮ.12፡2)