Thursday, July 26, 2012

ቅዱስ ገብርኤል ሆይ እስቲ ልጠይቅህ!


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/11/2004
ዛሬ የጌታችንንና የአፍቃሪያችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክና ግርማ ለብሶ በብሉይ ኪዳን ለቅዱሳን መጽናናትን ይሰጥ የነበረውና(ዳን.10፡5-5 ከ ራእይ.1፡14-16 ካለው ጋር ያነጻጽሩ፤ እንዲሁም ሕዝ. 1፡26 ከ ዳን.8፡15፤9፡21፤10፡18 እንዲሁም 3፡25 ያነጻጽሩ)በሐዲስ ኪዳንም የድኅነት ብሥራትን ይዞ ወንድሞቻችንን መላእክትን ወክሎ እንዲሁም ነፍስን በደስታ በምታስጨንቅ ፍስሐ ተሞልቶ፣(ሉቃ፡15፡10) ወደ ድንግል በመምጣት ሕዝቡን ከኃጢአት የሚያድናቸው የስሙ ትርጓሜ መድኀኒት የሆነውን "ኢየሱስን በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና ትወልጃለሽ"(ሉቃ፡1፡31) ብሎ ያበሠረ የተወዳጁ መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል ነው፡፡
 ሰውና አምላክ ፍጹም እርቅን የፈጸሙባትን ያቺን ዕለት ሳስባት ነፍሴ በሐሴት ትሰክራለች፡፡ ልጅ ከእናትና ከአባት ጥምረት ይወለዳል ፡፡ ስለዚህ ልጅ የእናትና የአባት ውሕደት አማናዊ መገለጫ ነው፡፡ እንዲሁ እግዚአብሔር አብ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ሊገልጥልን ስለወደደ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ከድንግል በሥጋ ይወለድ ዘንድ ላከው፡፡  ልጁም ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ በመወለድ ፍጹም እርቅ በሰውና በእግዚአብሔር  መካከል መፈጸሙን በልደቱ አበሠረን፡፡ 
ከአባት አብራክና ከእናት መኀፀን የተወለደን ልጅ አካፍሎ ወደፊት ለአባትና ለእናት መስጠት እንዳይሞከር እንዲሁ እግዚአብሔር ወልድ ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከተወለደ በኋላ አምላክ ወሰብእ ተብሎ ይኖራል እንጂ ወደፊት ተከፍሎ የለበትም፡፡

ከእኛም ጋር ፍጹም እርቅን እንደፈጸመ ያሳየን ዘንድ እግዚአብሔር ቃል ከእኛ ዘመድና አክሊል ከሆነችው ከድንግል የሰውን ተፈጥሮ ገንዘቡ በማድረግ በተዋሕዶ ተገለጠልን፡፡ ይህን ዘለዓለማዊ የእርቅ ዜናን ይዘህ የመጣ ቅዱስ ገብርኤል ሆይ! ለአንተ የማቀርበው ጥያቄ አለኝ፡፡ ያኔ ይህን ግሩምና ድንቅ የሆነውን የምሥራቹን ዜና ወደ ሰዎች ባመጣህ ጊዜ በእውነት ከደስታህ ብዛት የተነሳ ነፍስ ቀርታልህ ነበርን? ቅዱሱ መልአክ ገብርኤል ሆይ! በብሉይ አስቀድመህ እውቀትንና ማስተዋልን ልትገልጽለት ወደ ነቢዩ ዳንኤል ተልከህ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚሆነውን አንድም ሳታስቀር አሳውቀኸው ነበር፡፡ ነገር ግን ገብርኤል ሆይ ያኔ ወደ ድንግል በተላክህ ጊዜ በእውኑ በድንግል ስለተፈጸመው የተዋሕዶ ምሥጢር ለማስረዳት ተችሎህ ነበርን? ወይስ ስለዚህ ተዋሕዶ ለመረዳት ከድንግል ትረዳ ዘንድ ዝቅ ብለህ በትሕትናና በአክብሮት ጠይቀሃት ይሆንን? ድንግልስ ለአንተ፡- “ለሰው ልጆች ተጨናቂ የሆንክና የልጄን ግርማና መልክ የያዝክ ወዳጄ ቅዱስ ገብርኤል ሆይ! እኔም በውስጤ ስለተፈጸመው ተዋሕዶ ምሥጢር እጹብ እጹብ ከማለት ባለፈ በቃላት ልነግርህና ልተረጉምልህ አይቻለኝም ብላ አልመለሰችልህምን? በእርግጥም ይህ እጅግ ግሩምና ድንቅ የሆነ ተዋሕዶ ነውና፡፡ ጌታችን ሆይ ቃላት በማይገልጡት እጅግ ጥልቅና በአንተ ዘንድ ባለው የባሕርይ መገለጫ በሆነው ፍቅርህ፣ እንዲሁ ለዘለዓለም ወደኸናልና ባሕርያችንን አምላክ በማድረግ ሰው ሆነህ በሥጋ ተገለጥክ፡፡ ስለዚህ አንተ እኛን እንዲህ እንደወደድከን እንዲሁ እኛም ለዘለዓለም እንወድሃለን እንገዛልሃለን፡፡ ክብርና ምስጋና ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!    

No comments:

Post a Comment