Tuesday, April 17, 2012

የትንሣኤው መልእክት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/08/2004
ቅዱስ ጳውሎስ “ፋሲካችሁ ክርስቶስ ታርዶአልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾ አይደለም”(1ቆሮ.5፡8)አለን፡፡ በዚህ ቦታ በክርስቶስ የተሰበከችውን ወንጌል በእርሾ መስሎ ማስተማሩን እናስተውላለን፡፡ ስለዚህም ለእኛ ክርስቲያኖች የሕይወት ዘመናችን በሙሉ የበዓል ቀን ነው፡፡(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ) ቅዱስ ጳውሎስ “በዓል እናድርግ” ሲለን ግን እንደ አይሁድ የዳስ በዓልን ወይም ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበትን ፋሲካቸውን ማለቱ እንዳልሆነ ሁላችንም መረዳቱ አለን፤ አስቀድሜ እንደ ተናገረኩት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሡ ሁሉ የሚበቃ የእግዚአብሔር በግ ክርስቶስ ታርዶአልና በዓልን አድርጉ ሲለን ነው፡፡
 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ራሱን አንድ ጊዜ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ ከጨለማ ወደሚደንቅ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከድሮው አዳማዊው ተፈጥሮ ክርስቶስን ለብሰን ወደምንገኝበት ሰብዕና አሸጋግሮናል፡፡ እነሆ በእርሱ የድኅነት ሥራ ሀገራችን በሰማይ ሆኗል፡፡ ስለዚህም አነጋገራችን፣ አመጋገባችን፤ አለባበሳችን፤አኗኗራችን ሁሉ ተለውጦአል፡፡ ከእንግዲህ ደስታችን በምድራዊው ምግብና መጠጥ አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ቅዱሳን መላእክት መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን መጽናናት ሆኖአል፡፡ ጌታችን ለእኛ ካደረገው ከዚህ ታላቅ ቸርነት በላይ ሌላ ቸርነት አለን? ስለእኛ መዳን ሲል እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ስለእኛ ጭንቅ የሆነ ሕማምን ተቀበለ፣ በሞቱ ሞትን አጥፍቶ እኛን ከሰይጣን ባርነት ነጻ አውጥቶ አዲስ ሕይወትን ሰጠን፡፡ ሰውነታችን ማደሪያው ቤተመንግሥቱ ሆነ፡፡


እኛ በእርሱ አሁን  ነገሥታት ነን፤ ካህናት ነን፤ ነቢያትም  ነን፤ የልዑል ልጆችም ነን፤ በጸጋ አማልክትም ተሰኝተናል፤ ከዚህ የበለጠ ድንቅ የሆነ ሥጦታ ምን አለ?አሁን ክርስቶስን በሚመስል አኗኗር እንኖር ዘንድ ለዚህ የሚያበቃንን መንፈስ ቅዱስንና ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ተቀብለናል፡፡ ስለዚህም በክርስቶስ በተፈጸመልን የማዳን ሥራ አንድ ክርስቲያን በሰማይ ከቅዱሳን መላእክት ጋር አለ፡፡ በምድር ከምድር ፍጥረታት ጋርም ይኖራል፡፡ ከእግዚአብሔርም ጋር በመንበሩ አለ፡፡ ይህ በእውነት ድንቅ ነገር ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን በምድር ነው ሲሉት በሰማያት ይገኛል በሰማያት ነው ሲሉት በምድር ይገኛል፡፡ በመላእክትና በሰዎች ጉባኤ አለ ሲሉትም በኪሩቤል ጀርባ ላይ ከተቀመጠው ጌታው ክርስቶስ ጋር ይገኛል፡፡ ይህ በእውነት እጅግ ድንቅና ግሩም የሆነ ነገር ነው፡፡
 እኒህን ደጋግ ሥጦታዎች በክርስቶስ የተቀበለ ወይም የሚቀበል ሰው ዘመኑ ሁሉ የደስታ ቀን እንዴት አይሆንለት? ስለዚህም ከእኛ መካከል አንድም ሰው ስለድህነቱ ወይም በሌሎች ስለሚቀበለው መከራ ወይም ጠላቱ በእርሱ ላይ ስለሚተነኩላቸው ተንኮሎች ተስፋ አይቁረጥ አይዘንም፡፡ ምክንያቱም አሁን በክርስቶስ እጅ ነው ከእርሱ እጅ ማንም ሊነጥቀው አይቻለውምና፡፡ እንዲህም እንዲሆን ስለኃጢአት ሥርየት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ሠውቶልናልና፡፡
 ቅዱስ ጳውሎስም “በጌታ ደስ ይበላችሁ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ”ይላልና (ፊልጵ.4፡4) በዚህ በዓላችን ቀን ማንም የቆሸሸና ያደፈ ልብስ አይልበስ፤ እንዲህ እንዲሆንም አንፍቀድ፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በትንሣኤ እኛን ወደ ሰማያዊው ተፈጥሮአችና ሀገራችን አሸጋግሮናልና፡፡ አሮጌው ሰዋችን ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎአል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሣና ሕያው እንደሆነ እኛም በአዲስ ሕይወት እየኖርን እኝገኛለን፡፡ እነዚህን በጥምቀት አንዴ ፈጸመናቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስረዳ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደተጠመቅን አታውቁምን?...ካለ በኋላ “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ ጋር አንተባበራለን”(ሮሜ.6፡3-5) ይለናል፡፡ እንዲሁም “ሞትን መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ሞቶአል በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት አንደ ሞታችሁ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆናችሁ ራሳችሁ ቁጠሩ፡፡”(ሮሜ.7፡10-11)ብሎ ይሰብከናል፡፡ስለዚህም በትንሣኤ ሕይወት ከቅዱሳን ነፍሳትና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ማኀበርተኞች ሆነናል፡፡
 የጌታ ትንሣኤ እርሱ ከቤተክርስቲያን ጋር ጋብቻ የፈጸመበት ቀን ነው፡፡ ይህቺ በዓል ክርስቶስ ሰማያዊት ሙሽሪት የሆነችውን ቤተክርስቲያንን ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ እንጽቶ ከጎኑም በፈሰሰው ደሙ ዋጅቶ ወደ አባቱ እልፍኝ ይዞአት የገባበት ታላቅ በዓል ናት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ” አለ፡፡(ኤፌ.4፡8) በፍቅሩ የተማረክነው ቤተክርስቲያን የተባልነውም እኛ ነን፡፡ ስለዚህም ጉዳይ ጌታችን ሲያስረዳ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች” ብሎ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዓል ያለው ይህንን ነው፡፡ ለአንድ ንጉሥ ከልጁ ሰርግ በላይ ምን ደስታ ሊኖረው ይችላል? እግዚአብሔርም ልጆቹ ለሆነው የሰረገው ሰርግ ይህ ትንሣኤው ነው፡፡ እርሱ ልጁን ከእኛ ጋር መንፈሳዊ ጋብቻን እንዲፈጸም አድርጎ ሰርግን ሰረገ በዓሉም ፍጹም መንፈሳዊ ነው፡፡ ስለዚህም በቁጣና በግፍ እርሾ በዓልን አናድርግ፡፡ ከኃጢአት ሥራ ተለይተን በዓልን እናድርግ እንጂ በጨለማ ወደኖርንበት ዘመን ተመልሰን በዝሙት፣ በስካር፣ በዘፈን አይሁን፡፡
በምድራዊው የሰርግ ሥነሥርዐት ላይ እንዲገኝ የተጠራ አንድ ሰው ያደፈና የቆሸሸ ልብስ ለብሶ ቢገኝ ሰርጉ ወደሚፈጸምበት እልፍኝ እንዲገባ እንደማይፈቀድለት እንዲሁ ሰውነቱን ከኃጢአት ያልጠበቀና በፍቅርና በምጽዋት ያልጸና ሰው ወደ ጌታ ሰርግ አይገባም፤ በሩ በላዩ ላይ ተዘግቶ በውጭ ይቀራል እንጂ፡፡ ስለዚህም ይህን ፋሲካችንን አብዝቶ በመመገብና በዘፈን እንዲሁም በስካር ልናሳልፈው አይገባንም፡፡ ከእንግዲህ እኛ ቁጥራችን ከመላእክት ወገን ሆኖአል፡፡ እነርሱ በፍቅርና በንጽሕና ሆነው አምላካቸውን በማመስገን እንደሚኖሩ እኛም ለዚህ ተጠርተናል፡፡ አፍቃሪያችን ክርስቶስ ለዚህ ታላቅ ሕይወት የበቃን እንሆን ዘንድ ማስተዋሉን ያድለን ለዘለዓለሙ አሜን!!!    

1 comment:

  1. በምድራዊው የሰርግ ሥነሥርዐት ላይ እንዲገኝ የተጠራ አንድ ሰው ያደፈና የቆሸሸ ልብስ ለብሶ ቢገኝ ሰርጉ ወደሚፈጸምበት እልፍኝ እንዲገባ እንደማይፈቀድለት እንዲሁ ሰውነቱን ከኃጢአት ያልጠበቀና በፍቅርና በምጽዋት ያልጸና ሰው ወደ ጌታ ሰርግ አይገባም፤ በሩ በላዩ ላይ ተዘግቶ በውጭ ይቀራል እንጂ፡፡ ስለዚህም ይህን ፋሲካችንን አብዝቶ በመመገብና በዘፈን እንዲሁም በስካር ልናሳልፈው አይገባንም፡፡ ከእንግዲህ እኛ ቁጥራችን ከመላእክት ወገን ሆኖአል፡፡ እነርሱ በፍቅርና በንጽሕና ሆነው አምላካቸውን በማመስገን እንደሚኖሩ እኛም ለዚህ ተጠርተናል፡፡ አፍቃሪያችን ክርስቶስ ለዚህ ታላቅ ሕይወት የበቃን እንሆን ዘንድ ማስተዋሉን ያድለን ለዘለዓለሙ አሜን!!!

    ReplyDelete